ዋዜማ- በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 14ኛ ቀን ውሎ “ስልታዊ” ቡድኖች የአጀንዳ ምክረ ሀሳባቸውን ሲያደራጁ ውለዋል። በአንድ “ስልታዊ” ቡድን የተሰባሰቡ አምስት “ንዑስ” ቡድኖችን የወከሉ 25 “ተመካካሪዎች” የስልታዊ ቡድኑን ምክረ ሀሳብ እንዲያደራጁ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን፤ ምክረ ሀሳቡን ለ250ዎቹ የቡድኑ አባላት አቅርበው ውይይት ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ሂደት ሐምሌ 21 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ይጀመራል የሚል ዕቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፤ ምክረ ሀሳባቸውን አደራጅተው ያልጨረሱ ቡድኖች ከመኖራቸው ጋር በተያያዘ የአንድ ቀን ጊዜ በመጨመር፤ ሐምሌ 22 ቀን እንዲጀመር መወሰኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ ተናግረዋል።

“ተመካካሪዎች” አማራጭ የመፍትሄ ሀሳቦችን ይዘው እንዲቀርቡ ቢጠየቅም፤ እስካሁን ባለው የምክክር ሂደት፣ አማራጮችን በድምጽ ብልጫ የመለየት ሂደት አልተጀመረም። ኮሚሽኑ ያቋቋመው “የምሁራን ፓናል”፤ የሚቀርቡ አማራጮች ጥቅምና ጉድታቸው “ሳይንሳዊ” በሆነ መንገድ እንዲመዘን የማድረግ ኃላፊነት ያለው መሆኑን የነገሩን ምንጮች፤ “ስልታዊ” ቡድኖች 500 ተመካካሪዎችን ለሚይዘው የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን የሚያቀርቡት የምክረ ሀሳብ “ቃለ ጉባኤ” የመፍትሄ አማራጮችን ሳይንሳዊ ትንተና የሚያካትት ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

የብሔር ፌደራሊዝምን ለማስቀጠል “የቆረጡ” ተመካካሪዎች

“በመንግስት አደረጃጀት እና ቅርጽ” አጀንዳ ውስጥ በተካተተው “የመንግስት አደረጃጀት፣ አስተዳደር ሥርዓት ዓይነት” ንዑስ አጀንዳ ተመካካሪዎች “ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነ የመንግስት ስርዓትን” እንዲለዩ አማራጮች እንደቀረቡላቸው መዘገባችን ይታወሳል። በስልታዊ ቡድኖች ደረጃ በተካሄዱ ምክረ ሀሳብ የማጠናቀር ሂደቶች፤ ፌደራላዊ የመንግስት ሥርዓትን ለማስቀጠል የቀረበው አማራጭ ሚዛን መድፋቱን የገለጹልን የዋዜማ ምንጮች፤ በሥራ ላይ ያለው “የብሔር ፌደራሊዝም” ድክመቶቹ እንዲሻሻሉ ተደርጎ ይቀጥል የሚል ሀሳብ ያቀረቡ ተመካካሪዎች በርካታ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ከብሔር ፌደራሊዝም በተጨማሪ “ጂኦግራፊያዊ” ፌደራሊዝም እንደ አማራጭ የቀረበ ቢሆንም፤ የብሔር ፌደራሊዝም ላይ የተስተዋሉ “ውስንነቶችን በመቅረፍ ሥርዓቱን ማስቀጠል” የሚለው  አማራጭ ሚዛን ስለመድፋቱ ሰምተናል። ይህንን አማራጭ የደገፉ ተመካካሪዎች፤ በርካታ የብሔርና የማንነት ጥያቄዎች ባሉበት አውድ ውስጥ፣ የመንግስት ሥርዓት ለውጥ ማምጣት “ችግሩን ማባባስ ነው” የሚሉ አስተያየቶችን መሰንዘራቸውን ሰምተናል። ይህ የፌደራሊዝም ሥርዓት ከማሻሻያዎች ጋር እንዲቀጥል ምክረ ሀሳብ የሚያቀርበው አማራጭ የጎላ ድጋፍ ቢያገኝም፤ የክልሎች አደረጃጀት ላይ ግን የተለየ ዘዴ እንዲቀየስ መጠየቁን ምንጮች ገልጠዋል።

መልክዓ ምድርን መሠረት ያደረገ የክልሎች አደረጃጀት

የብሔር ፌደራሊዝም የሚነሱበትን “ድክመቶች” ለማስተካከል እንደ አማራጭ ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል “የክልሎች አደረጃጀት ማሻሻያ” አንዱ መሆኑን የገለጡልን ምንጮች፤ ብሔርን መሰረት ካደረገ የክልሎች አደረጃጀት በመውጣት፤ መልክዓ ምድራዊ አመቺነት፣ ኢኮኖሚያዊ አመቺነት፣ የሕዝብ ብዛትና ሌሎች መመዘኛዎችን ታሳቢ ያደረገ የክልሎች አደረጃጀት ተግባራዊ እንዲደረግ መጠየቁን ጠቁመዋል። 

የብልጽግና ፓርቲን “አቋም” የተቃረነው ምክረ ሀሳብ

ብልጽግና ፓርቲ “ፕሬዝዳንታዊ” የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ እንዲደረግ የቀረበውን አማራጭ እንደሚመርጥ፤ በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ አባላትም ይህንን አቋም መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ እንዲያደረጉ አቅጣጫ መስጠቱን ዋዜማ መዘገቧ ይታወሳል። በዚህ አጀንዳ ላይ “ምክክር” እያደረጉ ባሉ “ስልታዊ” ቡድኖች ጎልቶ የወጣው አማራጭ ግን፤ “ፓርላመንታዊ” የመንግስት አስተዳደር ስርዓትን ማስቀጠል የሚለው መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። 

ጥያቄ የቀረበባቸው “መሪ” ጥያቄዎች

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለ”ምክክር” ሂደቱ መነሻ እንዲሆኑ በሚል በሰነድ አዘጋጅቶ ለተመካካሪዎች ያቀረባቸው “መሪ” ጥያቄዎች፤ አንዳንድ አጀንዳዎችን በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ የማያስችሉ ሆነው መገኘታቸውን ምንጮች ገልጠዋል። “በቂ አማራጮችን ያላቀረቡ”፣ “መነሳት ያለባቸውን ጉዳዮች የዘነጉ”፣ “አንኳር ጉዳዮችን አድበስብሰው ያለፉ” መሪ ጥያቄዎች መኖራቸውን ያነሱ “ተመካካሪዎች”፤ ጉዳዩን አስመልክቶ ለአወያዮች ጥያቄ ማቅረባቸውን ሰምተናል። ለንዑስ ቡድኖች በቀረቡ አጀንዳዎች ዙሪያ መነሳት ያለባቸው ነገር ግን መሪ ጥያቄ ያልተዘጋጀላቸው ጉዳዮች፤ የምክክር ቃለ ጉባኤዎች ላይ እንዲካተቱ አቅጣጫ የሰጡ “አወያዮች” መኖራቸውን የገለጡት የዋዜማ ምንጮች፤ እነዚህ ጉዳዮች በመጨረሻው የምክረ ሀሳብ ሰነድ ላይ መካተት መቻል አለመቻላቸው ግን ማረጋገጫ የተገኘለት ጉዳይ አለመሆኑን ጠቁመዋል። 

ትክክለኛ የተመካካሪዎች ቁጥር ያልታወቀበት ምክክር

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ሐምሌ 18 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የተጠቃለለውን የተመካካሪዎች ቁጥር “ከሁለት ቀናት በኋላ” እናሳውቃለን ብለው የነበረ ቢሆንም፤ ሐምሌ 21 ቀን፣ 2018 ቀን በሰጡት መግለጫም ትክክለኛ የተመካካሪዎችን ቁጥር ሳያሳውቁ ቀርተዋል።  3 ሺሕ 800 የሚደርሱ ተመካካሪዎች የተገኙባቸው የምክክር ቀናት እንደነበሩ የገለጡት ዋና ኮሚሽነሩ፤ “እስካሁን ያለው የተመካካሪዎች ቁጥር ከ4 ሺሕ አይበልጥም” ከማለት ውጭ ትክክለኛውን የተመካካሪዎች ቁጥር ይፋ አላደረጉም። ኮሚሽኑ የምክክር ሂደቱን ለመምራት ባዘጋጀው መመሪያ፤ በርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ተመካካሪዎች ቁጥር ከ500 ሊበልጥ እንደማይችል ያስቀመጠ ሲሆን፤  ይህ ድንጋጌ የአጠቃላይ ተመካካሪዎች ቁጥር ከ4 ሺሕ መብለጥ እንደማይችል የሚያመላክት ነው።

የመጨረሻ ውሳኔ ያልተላለፈበት የክልል ተወካዮች ጉባኤ

በምክክር ሂደቱ ከፍተኛ ሚና ያለውና የ12ቱን ክልሎች፣ የሁለቱን የከተማ አስተዳደሮችና የፌደራል ባለድርሻዎችን የሚያቅፈው የክልል ተወካዮች ጉባኤ ጉዳይ አሁንም የመጨረሻ ውሳኔ እንዳልተላለፈበት ምንጮች ነግረውናል። ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የውክልና ጥያቄ የቀረበበት ይህ ምክር ቤት፤ “ምን ያህል አባላት ይኖሩታል?”፣ “የትኞቹ ባለድርሻ አካላት ይወከሉበታል?” የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ያሉበት ሲሆን፤ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮችም የመጨረሻ ውሳኔያቸውን እስካሁን ይፋ አላደረጉም። በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት የሰጡት ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ፤ ምርጫው የሚካሄድበት ቀን ሲደርስ መረጃ እንደሚሰጡ ከመናገር ውጭ ዝርዝር መረጃ ሳያቀርቡ ቀርተዋል። የጉባኤው አባላት፤ በቀጣዩ ሳምንት የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች ጥቅል ምክረ ሀሳቦችን ማደራጀት ከመጀመራቸው በፊት ይመረጣሉ ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ትክክለኛውን ቀን ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል። የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በጉባኤው ለመወከል ጥያቄ ማቅረባቸውን የገልጡልን ምንጮች፤ ኮሚሽኑ በጥያቄዎቹ ዙሪያ ያስተላለፈውን ውሳኔ አለማሳወቁን ጠቁመዋል።  [ዋዜማ]