ዋዜማ- የኦሮሚያ ክልል መሬት ቢሮ ለተለያዩ ሐይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች የሚውሉና ሕጋዊ የባለቤትነት የይዞታ ማረጋገጫ ሠነድ ወይም ካርታ እና ፕላን ለሌላቸው የከተማ መሬቶች፣ የሕጋዊነት ማረጋገጫ ሠነድ ሊሰጥ መሆኑን ዋዜማ ሠምታለች። 

የክልሉ መሬት ቢሮ ለ23ቱ ከተማ አሥተዳደሮች እና ለ21ዱ የዞን የመሬት መምሪያዎች ሥራ ላይ እንዲውል አጽድቆ የላከውን የአፈጻጸም መመሪያ ዋዜማ ተመልክታለች። መመሪያው በውስጡ ካካተቻቸው እና ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሠነድ እንዲሰጣቸው ቢሮው ከወሰነው የከተማ መሬቶች መካከል ለጋራ ጥቅም የሚውሉና እንደ ጥምቀት፣ ዋቄፈና እንዲሁም ኢሬቻን የመሳሰሉ ሐይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘት ያላቸው ሕዝባዊ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩባቸው መሬቶች ይገኙበታል። 

በተጨማሪም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት፣ የእንሰሳት ማደለቢያና እርባታ፣ በወጣቶች፣ በሴቶች በመምህራን፣ በከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም በሌሎች ሰዎች ተይዘው ያሉ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሕጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሠነድ ከሚሰጣቸወ መካከል መሆናቸውን ዋዜማ ከመመሪያው ተመልክታልች። 

እነዚህ አካላት ሕጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሠነድ የሚሰጣቸው የክልሉ መንግሥት ያስቀመጠውን መስፈርት ካሟሉ ብቻ ነው ሲል መመሪያው ደንግጓል። ከመስፈርቶቹ መካከል መሬቱ የክልሉ መንግሥት የከተማ መሬት ሊዝ አዋጅ ካጸደቀበት ከጥር 24፣ 2005 ዓ፣ም በፊት አገልግሎት ሲሰጥ ከነበረ፣ መሬቱ ቋሚ ንብረት በላዩ ላይ ካለ ወይም አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ መሬቱን ለማሥተዳደር ሕጋዊ ፈቃድ ያለው ወይም ኃላፊነት መውሰድ የሚችል አካል ካለ እንዲሁም ከከተማ ፕላን ጋር የሚጣጣም ከሆነ ብቻ ሕጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሠነድ ይሰጠዋል ሲል መመሪያው ያዛል። 

በተጨማሪም ከ 2001 ዓ፣ም በፊት በተለያዩ ዓመታት ቢያንስ 3 ጊዜ የከተማ የቤት ግብር እና የመሬት ኪራይ የተከፈለበት ደረሰኝ ማቅረብ የሚችል፣ ከ 2001 ዓ፣ም በፊት በተለያዩ ዓመታት ቢያንስ 3 ጊዜ እንደ ስልክ፣ መብራት እና ውሃን የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት የክፍያ ቢል ወይም ደረሰኝ ማቅረብ የሚችል ሠነዱ ይሰጠዋል ሲል በመመሪያው ላይ ሰፍሯል። 

የይዞታው ስፋት መሬቱ እየሰጠ ካለው አገልግሎት አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ከሆነና የመሬት ብክነት እያስከተለ መሆኑ ከተረጋገጠ መሬቱ ተለክቶ የሚተርፈው መሬት ለሌላ አገልግሎት እንዲውል እንደሚደረግ ዋዜማ የተመከለተችው መመሪያ ደንግጓል። 

መመሪያው ሕጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሠነድ የሌላቸው ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች እና የሲቪክ ማኅበራት የሚስተናገዱበትን መንገድ የዘረዘረ ሲሆን፣ መስፈርቱን አሟልተው የተገኙ ድርጅቶች የባለቤትነት ማረጋገጫ ሠነዱ የእነዚሁ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ተቋማት ጉዳይ በሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም በኩል ተላልፎ እንደሚሰጥ መመሪያ ያትታል። 

መመሪያው ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሠነድ የሌላቸው የሐይማኖት ተቋማት ሕጋዊ ሠነድ የሚያገኙበትን መንገድ ያስቀመጠ ሲሆን፣ የሐይማኖት ተቋሙ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ከሆነ፣ የታደሰ የምዝገባ ፈቃድ ያለው ከሆነ፣ መንፈሳዊ አገልግሎት እየሰጠ ከሆነ፣ የሐይማኖቱ ተከታዮች ያሉት መሆኑን ከከተማ አሥተዳደር ወይም ከቀበሌ የመንግሥት መዋቅር የድጋፍ ደብዳቤ አጽፎ ማቅርብ ከቻለ ሕጋዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሠነድ እንደሚያገኝ በመመሪያው ላይ ሰፍሯል።

ለሐይማኖት ተቋማቱ ሕጋዊ የሚደረግላቸው ይዞታ የሐይማኖት ተቋሙ ከታነጸበት ስፍራ እስከ ውጭ አጥር ድረስ ብቻ ያለው መሬት መሆኑን መመሪያ ያዛል። በተጨማሪም የከተማ መረዳጃ እድሮች ሕጋዊ ሠነድ የሚያገኙበትን መንገድ መመሪያው ያስቀመጠ ሲሆን፣ የመረዳጃ እድሩ መሬቱን እያሥተዳደረ ስለመሆኑ ከከተማ አሥተዳደር ወይም ከቀበሌ የመንግሥት መዋቅር የድጋፍ ደብዳቤ አጽፎ ማቅረብ መቻል እንደሚኖርበት ደንግጓል። የመረዳጃ እድሩ የያዘው መሬት ከከተማው ፕላን ጋር የማይጣጣም ከሆነ ካሳ በመስጠት ቤቱ የሚፈርስ ሲሆን፣ ሌላ ተለዋጭ መሬት ሊሰጥ የሚችልበት አግባብ ሊኖር እንደሚችል ዋዜማ ከመመሪያው ተመልክታለች። 

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ በክልሉ ያሉ ሕገወጥ ወይም በተለምዶ “ጨረቃ ቤት” ተብለው የሚታወቁ ካርታ እና ፕላን የሌላቸው የግለሠብ መኖሪያ ቤቶችን ባሉበት ሕጋዊ ሊያደርግ እና የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ሊሰጥ መሆኑን ዋዜማ ከሳምንታት በፊት መዘገቧ ይታወሳል። ሆኖም እነዚህን ሕገ ወጥ ቤቶች ሕጋዊ የማድረግ ሥራ ሸገር፣ አዳማ እና ቢሾፍቱ ከተሞችን እንደማያካትት በወቅቱ ዘግበናል። [ዋዜማ]