ዋዜማ- በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 20ኛ ቀን ውሎ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ይጀመራል ተብሎ የነበረው የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን ምክክር ሳይጀመር ቀርቷል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ሐምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ በስልታዊ ቡድኖች ደረጃ የሚካሄደው ምክክር መጠናቀቁን ገልጸው የነበረ ቢሆንም፤ ኮሚሽኑ እስከ ሐምሌ 29 ቀን ድረስ የስልታዊ ቡድኖች ምክክር እንዲቀጥል መወሰኑን ምንጮች ነግረውናል።
ይሁንና ኮሚሽኑ ቀደም ሲል ይፋ ባደረገው መሰረት ስምንቱ የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች በአጀንዳዎቻቸው ዙርያ በምሁራን ፓናል አማካኝነት ማብራሪያ ቀርቦላቸዋል። ከማብራሪያው በኋላ ግን የስልታዊ ቡድኖችን ምክረ ሀሳብ የሚያጠናቅሩ ተወካዮች ዳግም ምክረ ሀሳብ ወደ ማጠናቀር ሥራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውን ሰምተናል።
ኮሚሽኑ ቅዳሜ ሐምሌ 25 ቀን፤ 2018 ዓ.ም የምክክር ሂደቱን እየመሩ ከሚገኙ አወያዮች ጋር ውይይት ማድረጉን የገለጡልን ምንጮች፤ በውይይቱ ምክክሩ የደረሰበት ደረጃ ከተገመገመ በኋላ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለመሸጋገር ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልጉ መረጋገጡን ጠቁመዋል። ምክክሩ በሁሉም ቡድኖች እኩል እየተራመደ አለመሆኑ በውይይቱ መገለጡንም ዋዜማ ሰምታለች።
በሶስት ደረጃ የተቀመጠው የምክክር ሂደት
ኮሚሽኑ የምክክሩን አጠቃላይ ሂደት አስመልክቶ በውይይቱ ባቀረበው ሪፖርት፤ 16ቱ ስልታዊ ቡድኖች በሶስት ደረጃ የተከፋፈለ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን አስቀምጧል። በመጀመሪያው ደረጃ ላይ የሚገኙ ቡድኖች፤ ኮሚሽኑ ባስቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የምክረ ሀሳብ ቃለ ጉባኤያቸውን አደራጅተው የጨረሱ ናቸው። በሁለተኛው ደረጃ ላይ የሚገኙ ቡድኖች ደግሞ፤ ምክረ ሀሳብ እያጠናቀሩ የሚገኙና ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈጋቸው ሲሆኑ፤ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጡት ደግሞ ምክረ ሀሳብ ከማጠናቀር ይልቅ “አጀንዳ መሰብሰብ” ላይ አተኩረዋል የሚል ወቀሳ የቀረበባቸው መሆናቸውን ሰምተናል። ይህንን መሰረት በማድረግም ሰኞ ሐምሌ 27 ሊጀመር የነበረው የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን ምክክር በሶስት ቀናት ያህል እንዲራዘም መወሰኑን አረጋግጠናል።
አጀንዳ ወደ ማሰባሰብ ተመልሰዋል የተባሉት ቡድኖች
ሦስተኛ ሳምንቱን እያጠናቀቀ በሚገኘው የምክክር ሂደት፤ ወደ ኋላ ተመልሰው አጀንዳ ማሰባሰብ ላይ አተኩረዋል የተባሉት ስልታዊ ቡድኖች፤ ተመካካሪዎችን ወደ ስምምነት የሚያደርሱ ምክረ ሀሳቦችን ከማደራጀት ይልቅ፤ “ዝርዝር” ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገዋል በሚል መገምገማቸውን ምንጮች ነግረውናል። ተመካካሪዎች የወከላቸውን ማህበረሰብ ጥያቄ ለማቅረብ ያደረጉት ጥረት፤ የምክክር ሂደቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ አድርጓል በሚል በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
10 አባላት ባሉት ጥቃቅን ቡድን፣ እንዲሁም 50 አባላት ባሉት ንዑስ ቡድን ደረጃ የተካሄዱ ምክክሮች ተመካካሪዎች መነሳት አለባቸው የሚሏቸውን ጉዳዮች የሚያነሱባቸው እንዲሆኑ ታቅደው የተቀረጹ መሆናቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ 250 አባላት ባሏቸው ስልታዊ ቡድኖች ደረጃ የሚደረገው ምክክር ግን ምክረ ሀሳቦች መጠናቀር የሚጀምሩበት ሂደት እንዲሆን ተደርጎ የተቀረጸ መሆኑን ገልጠዋል። ይሁንና በዚህ ሂደት ምክረ ሀሳቦችን በተፈለገው መንገድ ያላጠናቀሩ ስልታዊ ቡድኖች ጥቂት የማይባሉ መሆናቸው ነው የተነገረው።
በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት እነዚህ ቡድኖች በሦስት ቅናት ውስጥ የአጀንዳ ምክረ ሀሳባቸውን በአግባቡ አጠናቅረው ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ አቅጣጫ ያስቀመጠው ኮሚሽኑ፤ ከእነዚህ ቡድኖች ቀድመው ሥራቸውን ያጠናቀቁ ቡድኖች ተመሳሳዩን ተግባር በማከናወን ምክረ ሀሳባቸውን እንዲከልሱ ማዘዙን ሰምተናል። በዚህም በርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች ደረጃ የሚካሄደው ምክክር ሐሙስ ሐምሌ 30 ቀን እንዲጀመር ተለዋጭ ዕቅድ መያዙን አረጋግጠናል።
ተመካካሪዎችን ለማሳመን የሞከሩ ምሁራን
በምክክር ሂደቱ ውስጥ 80 የሚደርሱ የምሁራን ፓናል አባላት፤ ሙያዊ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ኮሚሽኑ ማሳወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡ መኖራቸው ከአወያዮች ጋር በተካሄደው ውይይት መገለጡን ምንጮች ነግረውናል። ሙያዊ ማብራሪያ ከመስጠት ይልቅ “የሕይወት ታሪካቸውን መግለጥ ላይ ያተኮሩ”፣ ከርዕሰ ጉዳዮች ጋር የተገናኘ ትምህርትና ልምድ የሌላቸው፣ “አቋማቸውን በማብራራት ተመካካሪዎችን ለማሳመን የሞከሩ” እና ሌሎች ክፍተት የተገኘባቸው ምሁራን እንዳሉ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች መግለጣቸውን ሰምተናል። ከተመካካሪዎች እንዲሁም ከአወያዮች መሰሉ ቅሬታ መቅረቡም የተነገረ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ ቅሬታ በቀረብባቸው ምሁራን ላይ እርምጃ ስለመውሰድ አለመውሰዱ አላሳወቀም። ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን ለተመካካሪዎች እንዲሰጥ የተደረገው “ሙያዊ” ማብራሪያ፤ እርምት እንዲወሰድ ማስጠንቀቂያ ከተላለፈ በኋላ የተሰጠ መሆኑን ምንጮች ነግረውናል።
ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አወያዮች
“160 አወያዮችን አሰልጥኜ አሰማርቻለሁ” ያለው ኮሚሽኑ፤ የሥራ ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው በማይሠሩ አወያዮች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ማሳወቁን ምንጮች ገልጸውልናል። ከአወያይነት ሚናቸው ውጭ እንደ ተመካካሪ በምክክር ሂደቱ ለመሳተፍ የሞከሩና፤ ለተመካካሪዎች ምክረ ሀሳብ በማቀበል ያልተገባ ድርጊት የፈጸሙ አወያዮች መኖራቸው በውይይቱ ላይ መነሳቱን የነገሩን ምንጮች፤ መሰሉ ድርጊት በድጋሚ መፈጸሙ ከተረጋገጠ እርምጃ እንደሚወሰድ በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ኮሚሽነሮች ማሳሰባቸውን ገልጠዋል። መሰል ድርጊት ላይ መሳተፋቸው የተረጋገጠባቸው አወያዮች ከምክክር ሂደቱ እንዲወጡ ማድረግን ጨምሮ፤ በሕግ የሚጠየቁበት ሁኔታ እንደሚኖር መነገሩንም ሰምተናል። እስካሁን ባለው ሂደት ግን ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ውጭ እርምጃ የተወሰደበት አወያይ አለመኖሩን ምንጮች አረጋግጠውልናል።
“አንኳር” ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር መመሪያ የተላለፈበት ቃለ ጉባኤ
ስልታዊ ቡድኖች 500 ጉባኤተኞች ለሚሳተፉበት የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን ምክክር የሚያቀርቡት ቃለ ጉባኤ በአንኳር ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር መመሪያ ተላልፏል። ከጥቃቅን ቡድን ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው ምክክር፤ ለመሪ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ እስካሁን በተለያዩ ደረጃዎች የተዘጋጁት ቃለ ጉባኤዎች በኮሚሽኑ ማህደር ውስጥ የሚቀመጡ መሆናቸው ተነግሯል። ለርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን የሚቀርቡ ቃለ ጉባኤዎች በአንኳር ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩና ምክረ ሀሳቦችን በአግባቡ አደራጅተው የያዙ እንዲሆኑ መመሪያ መተላለፉን ምንጮች ነግረውናል። [ዋዜማ ]
