ዋዜማ- ሐምሌ 08 ቀን፤ 2018 ዓ.ም  በተካሄደ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት የተጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ፤ በስምንት አጀንዳዎች ዙሪያ ይመክራል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን 4 ሺሕ እንደሚደርሱ የገለጻቸው ተመካካሪዎች በስምንቱ አጀንዳዎች ዙሪያ ለመመካከር ወደ ስምንት ቡድኖች (የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን) ይከፋፈላሉ። እነዚህ ስምንት ቡድኖች በዕጣ በሚመደብላቸው አንድ አጀንዳ ላይ ብቻ ተመካክረው የመፍትሄ ምክረ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ይጠበቃል። ይህ ምክረ ሀሳብ ወደ ቀጣዩ ሂደት ለማለፍ  በቡድኑ በሚካሄድ የምድጽ አሰጣጥ 75 በመቶ ድምጽ ማግኘት እንደሚገባው ዋዜማ የተመለከተችውና ተመካካሪዎች ለሦስት ቀናት የምክክር ሂደቱን በተመለከተ በዓደዋ ድል መታሰቢያ በተሰጣቸው ማብራሪያ ላይ የቀረበ ሰነድ ያመላክታል

የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን ድምጽ አሰጣጥ

በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንዲመካከር የሚመሠረተውና 500 አባላት የሚኖሩት ቡድን፤ ለ10 ከዛም ለአራት አነስተኛ ቡድኖች ተከፍሎ ምክክር ካደረገ በኋላ፤ ለተወያየበት አጀንዳ የመፍትሄ ምክረ ሀሳብ ያዘጋጃል። ይህ የመፍትሄ ምክረ ሀሳብ በቡድኑ 75 በመቶ አባላት የድጋፍ ድምጽ ካገኘ ወደ ቀጣዩ ሂደት ይሸጋገራል። በምክረ ሀሳቡ ዙሪያ የሚሰጠው ድምጽ ከ75 በመቶ የሚያንስ ከሆነ ደግሞ “የስምምነት ግብረ ኃይል” በሚል የሚቋቋም አደረጃጀት ጣልቃ ይገባል።

የስምምነት ግብረ ኃይል ሚና

የሀገር ሽማግሌዎችን እና የምሁራን ፓናልን እንደሚያካትት በኮሚሽኑ የተነገረለት ይህ ግብረ ኃይል፤ በሥራ ቡድን ደረጃ 75 በመቶ ድምጽ ማግኘት ያልቻለው የአጀንዳ የመፍትሄ ሀሳብ ማስተካከያዎች እንዲደረጉበትና የሥራ ቡድኑ አባላት ዳግም ድምጽ እንዲሰጡበት የማድረግ ሚና አለው። ምክረ ሀሳቡ በዚህ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት የቡድኑን አባላት 70 በመቶ ድምጽ ማግኘት ከቻለ (በልዩ አብላጫ ድምጽ) ወደ ቀጣዩ ሂደት እንዲያልፍ ይደረጋል። የስምምነት ግብረ ኃይል ጣልቃ ገብቶ በተካሄደው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት 70 በመቶ ድምጽ ማግኘት ያልቻለ ምክረ ሀሳብ ውድቅ ይደረጋል።

የክልል ተወካዮች ጉባኤ

ይህ ጉባኤ እያንዳንዱ ክልልና የከተማ አስተዳደር 14 ተወካዮችን የፌደራል መንግስት ደግሞ 15 ተወካዮችን የሚያቀርቡበት በድምሩም 211 አባላት ያሉት ነው። የክልልና የከተማ አስተዳደሮች 14 መቀመጫዎቻቸውን ለክልል መንግስት ተወካዮች (4)፣ ለፓርቲዎች (4)፣ ለሃይማኖታዊ ተቋማት (1)፣ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች (2)፣ ለሲቪል ማህበረሰብ ጥምረት (1)፣ ለሴቶች (1)፣ ለወጣቶች (1) ያከፋፍላሉ። የፌደራል መንግስትም የተሰጠውን 15 መቀመጫ ለፌደራል መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች (5)፣ ለሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች (4)፣ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት (2)፣ ለሴቶች ፌደሬሽን (1)፣ ለሴቶች ጥምረት (1)፣ ለአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን (1)፣ ለወጣቶች (1) ያከፋፍላል።  

በሥራ ቡድን ደረጃ የሚፈለገውን 70 በመቶ የድጋፍ መጠን ማግኘት ያልቻሉ ጉዳዮች፣ የማንነት ወይም የህልውና አደጋን የሚመለከቱ ጉዳዮች እንዲሁም ቢያንስ ሦስት ክልሎች በጉባኤው እንዲታዩ ጥያቄ የሚያቀርቡባቸው ጉዳዮች በዚህ ጉባኤ ይታያሉ። እነዚህ ጉዳዮች በጉባኤው ከታዩ በኋላ በሚከናወን የድምጽ አሰጣጥ ሂደት 70 በመቶ የድጋፍ ድምጽ ማግኘት ከቻሉ ወደ ቀጣዩ ሂደት ያልፋሉ። በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ከ40 በመቶ በታች ድምጽ የሚያገኙ ጉዳዮች ውድቅ ይደረጋሉ።

በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ከ40 እስከ 69.9 በመቶ ድምጽ የሚያገኙ ጉዳዮች በስምምነት ግብረ ኃይል ጣልቃ ገብነት ውይይትና ማሻሻያ ተደርጎባቸው እንደገና ድምጽ እንዲሰጥባቸው ይደረጋል። በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ 70 በመቶ ድምጽ የሚያገኙ ጉዳዮች ወደ ቀጣዩ ሂደት የሚሸጋገሩ ሲሆን፤ ከ70 በመቶ በታች የሆነ ድምጽ የሚያገኙ ጉዳዮች ደግሞ ውድቅ ይደረጋሉ።

የጋራ ማረጋገጫ ሥርዓት

ይህ ሥርዓት  በተለያዩ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቶች ያለፉና ተገቢውን ድጋፍ ያገኙ ውሳኔዎችን፣ ምክረ ሀሳቦችን እና  ረቂቆችን ለማጣጣም በሚል የተዘረጋ ነው። ከእያንዳንዱ የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን 15 አባላትን (በድምሩ 120) የሚይዝና የምሁራን ፓናል አባላትን የሚያካትት ነው። 

በዚህ ሥርዓት ሁሉም የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች ውሳኔ ያሳለፉባቸው ሰነዶች ግምገማ የሚደረግባቸው ሲሆን፤ እርስ በእርሳቸው የሚገናኙ ጉዳዮች ትኩረት እንደሚደረግባቸው ሰነዱ ይጠቁማል። በሰነዶች መካከል ያሉ ልዩነቶችን መለየትና “የተጣጣመ” ረቂቅ ለርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች ማቅረብ የሥርዓቱ ኃላፊነት ነው።

የጋራ ማረጋገጫ ሥርዓቱ የሚያዘጋጀው “የተጣጣመ ረቂቅ” ለርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች ይቀርባል። በርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን (የሥራ ቡድን) ተቃውሞ የሚያጋጥመው ረቂቅ በሥራ ቡድኑና በጋራ ማረጋገጫ ቡድኑ መካከል ውይይት ይደረግበታል። በውይይቱ ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ የጋራ ስምምነት ግብረ ኃይል ጣልቃ ይገባል። 

በጋራ ማረጋገጫ ሥርዓት የጸደቁ ምክረ ሀሳቦች

በጋራ ማረጋገጫ ሥርዓት የቀረቡና ወደ ርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖችተመልሰው ድጋፍ ያገኙ ምክረ ሀሳቦች ለጠቅላላ ጉባኤ ከመቅረባቸው በፊት ለክልል ተወካዮች ጉባኤ እንዲቀርቡ ይደረጋል። ጉባኤው በሚያካሂደው የድምጽ አሰጣት ሂደት 70 በመቶ ድምጽ ማግኘት የሚችሉ ውሳኔዎችና ምክረ ሀሳቦች ለሀገራዊ ምክክር ጠቅላላ ጉባኤ ይመራሉ።

70 በመቶ ድምጽ ማግኘት ያልቻሉ ውሳኔዎች ዳግም ወደ ጋራ ማረጋገጫ ቡድን እንዲመለሱ ይደረጋሉ። ቡድኑ የሚያሻሽለው ምክረ ሀሳብ ዳግም ወደ ክልል ተወካዮች ጉባኤው ይመራል። ጉባኤው 70 በመቶ ድምጽ የሚሰጠው የተሻሻለ ምክረ ሀሳብ ወደ ጠቅላላ ጉባኤ የሚመራ ሲሆን፤ ከ70 በመቶ በታች ድምጽ ያገኘ ምክረ ሀሳብ ዳግም ውድቅ ይደረጋል።

ጠቅላላ ጉባኤ

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የመጨረሻው ሂደት ጠቅላላ ጉባኤ ነው። ሁሉንም አስፈላጊ ሂደቶች ያለፉ ውሳኔዎች ለጠቅላላ ጉባኤው ይቀርባሉ። ይሁንና ጠቅላላ ጉባኤው በውሳኔዎች ዙሪያ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ተግባራዊ የማያደርግ ሲሆን፤ ጉባኤተኞች ለውሳኔው ያላቸውን ድጋፍ በጭብጨባ እንዲገልጹ ይደረጋል። ጉባኤተኞች ማብራሪያ የሚጠይቁባቸው ጉዳዮች ደግሞ ማብራሪያ ይቀርብባቸዋል። ለጉባኤው ቀርበው “ጠንካራ ተቃውሞ” የሚያጋጥማቸው ውሳኔዎች ግን ውድቅ ይደረጋሉ። “ጠንካራ ተቃውሞ” በሚል ኮሚሽኑ የገለጸውና ውሳኔዎችን ውድቅ የሚያስደርገው “ሁኔታ” ግን በምን አይነት መለኪያ እንደሚለይ ዋዜማ የተመለከተችው ሰነድ አላመላከተም።

ሕዝበ ውሳኔ

የምክክሩ ተሳታፊዎች “ያልተፈቱ” ያሏቸው ጉዳዮች በሕዝበ ውሳኔ መፍትሄ እንዲያገኙ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ሰነዱ የሚያመላክት ቢሆንም፤ ጥያቄው በምን አግባብ እንደሚቀርብ ግን አያስቀምጥም። በጠቅላላ ጉባኤው “ጠንካራ ተቃውሞ” ያጋጠማቸው ጉዳዮች ወደ ሕዝበ ውሳኔ ሊመሩ የሚችሉበት ዕድል ስለመኖሩም ኮሚሽኑ ገልጧል። [ዋዜማ]