በቀጣዮቹ ወራት አዳዲስ የተሽከርካሪ ባለቤትነት፣ የሪል ስቴት፣ የትምባሆና አልኮል ቀረጥ ይጣላል

ዋዜማ- የኢትዮጵያ መንግሥት በ2019 በጀት ዓመት 5 ቢሊዮን ዶላር አዲስ የውጪ ብድር ለመውሰድ ማቀዱንና እ.ኤ.አ ከሐምሌ ወር 2026 ጀምሮ አዳዲስ የታክስ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን ዋዜማ የተመለከተችው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) 5ኛው የግምገማ ሪፖርት ሰነድ ይፋ አድርጓል።

ተቋሙ በዚህ ሳምንት ባወጣው ባለ 132 ገጽ የፖሊሲ ትግበራ ክትትል ሪፖርት እንዳመለከተው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሁለት ዓመታት በፊት፤ተግባራዊ ማድረግ የጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ከተቀመጠው እቅድ በላይ በሆነ አፈጻጸም በስኬት እያከናወነ ይገኛል። 

መንግስት የማሻሻያ ፖሊሲውን ለማስፈጸም ከተጠቀሰው አጠቃላይ የብድር መጠን ውስጥ አብዛኛው ከባለብዙ ወገን አበዳሪዎች የሚገኝና ዝቅተኛ ወለድ የሚከፈልበት ቢሆንም፤ ለንግድ ብድር ግን ልዩ ሁኔታ መፈጠሩን ይጠቅሳል፡፡

አብዛኛው ብድር የሃገሪቱን የዕዳ ጫና በማያባብስ መልኩ በረጅም ጊዜ የሚከፈልና ዝቅተኛ ወለድ ያለው ሲሆን፤ የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ ብቻ የ9 መቶ 50 ሚሊዮን ዶላር የንግድ ብድር እንዲወሰድ በአይ ኤም ኤፍ ኃላፊዎች ከስምምነት መደረሱን ይጠቅሳል፡፡ 

መንግሥት ከአይ ኤም ኤፍ ጋር በገባው የ4 ዓመታት ፕሮግራም ውስጥ ምንም ዓይነት የንግድ ብድር ላለመውሰድ ቃል ቢገባም፤ ለኮይሻ ግድብ ግንባታ ልዩ ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡

ከተለያዩ አለማቀፍ አበዳሪዎች ጋር ለረጅም ጊዜያት ሲካሄድ የነበረውን የእዳ ሽግሽግ ድርድርን በሚመለከትም፤ መንግሥት የዩሮ ቦንድን ጨምሮ ከሁሉም የውጭ አበዳሪዎች ጋር እስከ መጪው ታህሳስ 2026 ድረስ ስምምነት ላይ ለመድረስ አቅዷል። ይህ የዕዳ ሽግሽግ (Debt Restructuring) ሲጠናቀቅ፤ ለውጭ ዕዳ ክፍያ የሚወጣውን የመንግሥት ከፍተኛ በጀት ለመቀነስ እንደሚያስችል ገልጧል፡፡  

በቀጣዮቹ ወራት የሚጣሉት የታክስ አይነቶች

እንደ አይ ኤም ኤፍ የግምገማ ሪፖርት፤የኢትዮጵያ መንግሥት የውጪ ምንዛሪን ሙሉ በሙሉ በገበያ እንዲወሰን ካደረገ ወዲህ ባሉት ጊዜያት ፤ ተቋሙ ከታክስ እንዲሰበሰብ ካቀደው የገቢ መጠን ተጨማሪ 30 ቢሊየን ብር ተሰብስቧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ከታክስ የሚገኘውን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግና ማንኛውንም ድጎማ ለማንሳት ቃል መግባቱን የጠቆመው የገንዘብ ተቋሙ ሪፖርት፤ በቀጣዮቹ ወራት ይተገበራሉ ያላቸውን ቁልፍ እርምጃዎች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

ከእነዚህም መካከል የነዳጅ ድጎማ አንዱ ሲሆን፤ በ2019 በጀት ዓመት የነዳጅ ድጎማ ሙሉ በሙሉ ተነስቶ፤ ዋጋው በገበያ እንዲወሰን ይደረጋል። ነዳጅ ላይ ከሚጣሉ የታክስ አይነቶች በድምሩ 176 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 93 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT)፣ 80 ቢሊዮን ብር ከኤክሳይስ ታክስ  እንዲሁም 3 ቢሊዮን ብር ቀጥተኛ ካልሆነ የሃገር ውስጥ ታክስ የሚሰበሰብ ይሆናል። የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ኢንተርፕራይዝን የካፒታል አቅም በ286 ቢሊዮን ብር በማሳደግ በነዳጅ ምርቶች ላይ ከሚጣሉ ታክሶች የሚሰበሰበው ገቢ በሙሉ በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ ግምጃ ቤት ገቢ ሲደረግ፤ ኢንተርፕራይዙ የተፈቀደለትን ተጨማሪ ካፒታል በመጠቀም፤ የነዳጅ ግዥ ክፍያዎችን በቀጥታ ለአቅራቢዎች መክፈል ወደ ሚያስችለው የግዢ ስርአት እንዲገባ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡

ለኢንቨስትመንት ማበረታቻ ተብለው ይሰጡ የነበሩ የታክስ ነፃ መብቶችም ወደ መደበኛ ታክስ የሚቀየሩ ሲሆን፤ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) በጋራ በሚዘረጉት የአሰራር ስርአት፤ እስከ ታህሣሥ 2019 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ በአልኮል፣ በትምባሆና ሌሎች ምርቶች ላይ አዲስ የኤክሳይስ ታክስ ተመን ይወጣል፡፡

ሌላው የሚጣለው የታክስ አይነት የተሽከርካሪ ባለንብረትነት ታክስ ነው፡፡ ይህ ታክስ የሃገሪቱን ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 0.2 በመቶ ያህል ተጨማሪ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የግብር አወሳሰን ውሳኔውን እስከ ታህሣሥ 2019 ዓ.ም. ድረስ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያቀርብ ሲሆን፤ የፌደራልና የክልል መንግሥታት የትኛውን የተሽከርካሪ ግብር እንደሚሰበስቡ ይወስናሉ።

ከሪል ስቴትና የንብረት ታክስም በተመሳሳይ መልኩ፤ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 0.3 በመቶ ታክስ ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን፣ ለዚህም በትላልቅ ከተሞች የንብረት ዋጋ ትመናና የምዝገባ ሰነድ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶችም ትርፋማነት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚደረግ ሲሆን፤ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ያለትርፍ የሚሰሯቸው ሥራዎች ካሉ በመንግሥት በጀት እንዲያካክሱት ይደረጋል፡፡  

ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶች

መንግሥትና አይኤምኤፍ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ10.2 በመቶ እያደገ በመሆኑ የሚሰበሰበው ታክስም ከዚያው ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ማደግ እንዳለበት ይስማማሉ። ይሁን እንጂ የዚህ ዓይነቱ ሰፊ የታክስና የዋጋ ማስተካከያ ጫና በሕዝቡና በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ሪፖርቱ በዝርዝር አላስቀመጠም።

አይኤምኤፍ ለፖሊሲዎቹ ትግበራ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን ሁኔታዎች በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን፤ በአገር ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶች መባባስ ወይም በጎረቤት አገራት ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመረጋጋቶች ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡

በዓለም አቀፍ የገበያ ሁኔታዎችና በጸጥታ ችግሮች ምክንያት በገቢና ወጪ ንግድ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ የአቅርቦት ተግዳሮቶችም በተመሳሳይ መልኩ በስጋትነት ተቀምጠዋል፡፡[ዋዜማ]