ዋዜማ- ዛሬ በአዲስ አበባ የተጀመረው ብሔራዊ ምክክር በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ የተደበላለቁ ምላሾችን እያስተናገደ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መግባባትን ለመፍጠር ታሪካዊ ዕድል ይዞ ይመጣል የተባለለት የብሔራዊ ምክክር ጉባኤ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የፖለቲካ እና ወታደራዊ ባለስልጣናትን፣ የአፍሪካ ህብረት እና የኢጋድ ተወካዮችን፣ ከተለያዩ አለማቀፍ ተቋማት የተወከሉ ተጋባዥ እንግዶችን እንዲሁም ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ‹‹ተመካካሪዎች›› በተገኙበት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ በይፋ ተጀምሯል፡፡ የጉባኤውን መጀመር ተከትሎ በገዢው እንዲሁም በተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የተደበላለቁ እና የተቃረኑ አቋሞች እየተንጸባረቁ ይገኛሉ።

ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ ጠንከር ያሉ ማስጠንቀቂያዎችን አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት በባለቤትነት ታስተዳድረው የነበረውን የቀይ ባህር በር ያጣችው በጠላቶች ጥንካሬ ሳይሆን በውስጥ ድክመትና በፖለቲካዊ ሸፍጥ መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹ሀገሪቱ ስትዳከም ጣልቃ ለመግባት የሚያደፍጡና እርስ በርስ ስንጣላ ጥይትና ብር የሚያቀብሉ ኃይሎች አሉ›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዜጎች ምንም ዓይነት የውስጥ ልዩነት ቢኖራቸውም በውይይት መፍታት እንደሚችሉና ለሌሎች ኃይሎች ጥቅም ሲሉ ብሔራዊ ጥቅማቸውን አሳልፈው መስጠት እንደማይገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ ይህ የመንግሥት ጥሪና የተጀመረው የምክክር ሂደት በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። 

ምክክሩን የተቃወሙት የፖለቲካ ሃይሎች

ጊዜያዊ አስተዳደሩን አፍርሶ፤ ስልጣን በሃይል የተቆናጠጠው ህወሓት፤ ዳግም ያቋቋመው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት እየተካሄደ ያለውን ሀገራዊ የምክክር ሂደት ሙሉ በሙሉ ውድቅ በማድረግ፤ በሂደቱ እንደማይሳተፍ አስታውቋል። የትግራይ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ፤ መድረኩ የትግራይ ሕዝብ የሚጋፈጣቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች መመለስ እንዳልቻለ ጠቅሶ፣ የክልሉ መንግሥትም ሆነ የትግራይ ሕዝብ በዚህ ሂደት ውስጥ አልተወከሉም ብሏል። በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ቁልፍ ድንጋጌዎችን ተግባራዊ አላደረገም ሲል አስተዳደሩ ቅሬታውን አቅርቧል።

በተመሳሳይ መልኩ ተቃውሞውን ያሰማው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በበኩሉ፤ ሂደቱ የሀገርን ቀውስ ለመፍታት ሳይሆን፤ ‹‹የከሸፈውን የብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካዊ ቅቡልነት ለመግዛትና ዕድሜ ለማራዘም የተዘጋጀ መድረክ ነው›› ሲል አጣጥሎታል። በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው ግጭት እና አጠቃላይ ያልተረጋጋ ሁኔታ፤ ‹‹ሂደቱ ከመሠረቱ ስሁትና አግላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው›› ያለው ኢሕአፓ፤ የፖለቲካ እስረኞች ሳይፈቱና ጦርነቶች ሳይቆሙ የሚደረግ ምክክር የሀገር መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ገልጿል።

በተቃራኒ መልኩ፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ የሆነው ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ሂደቱን በታላቅ ደስታና ተስፋ ተቀብሎታል። ነእፓ ይህ መድረክ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን ለማቀራረብና ጠንካራ ማኅበራዊ ውል ለመመሥረት የሚያስችል ‹‹ታሪካዊ ዕድል›› መሆኑን ገልጿል። ፓርቲው የሀሳብ ልዩነቶችን በኃይል የመፍታት የድሮ ባህልን በማስወገድ በውይይትና በድርድር የሚመራ ሥርዓት እንዲገነባ መላው ሕዝብና የፖለቲካ ልሂቃን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

የትኞቹ ሚድያዎች በመክፈቻው ታደሙ?

ለበርካታ ጊዜያት መጠነ-ሰፊ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየውን ሃገራዊ ምክክር የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር እንዲዘግቡ የተፈቀደላቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ብቻ ሲሆኑ፤ የግል መገናኛ ብዙሃን ምክክሩን ለመዘገብ የሚያስችላቸውን ‹‹ባጅ›› ቢወስዱም፤ የመክፈቻ መርሃ-ግብሩን እንዲዘግቡ አልተፈቀደላቸውም፡፡ ከነገ ጀምሮ ባሉት የምክክር መድረኮች ላይ ግን፤ ሃላፊነቱ የተሰጠው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ‹‹የግል መገናኛ ብዙሃን ተገኝተው መዘገብ ይችላሉ›› የሚል ፍቃድ ከሰጠ፤ የሚዘግቡበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ዋዜማ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ለማረጋገጥ ችላለች፡፡ [ዋዜማ]