ዋዜማ- አኮቦ ወርቅ በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ አሁን እየሠራበት ካለው ሰገሌ ፕሮጀክት አጠገብ ተጨማሪ 1,200 ኪሎ ሜትር እስኩዌር የወርቅ መሬት ጠይቆ ምላሽ ከመንግሥት እየጠበቀ መሆኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታወቀ፡፡

ማስፋፊያ የጠየቀበት አካባቢ ጊሎ በመባል የሚታወቅ ሲሆን እዚያው በዲማ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን፣ በአካቦ ወንዝ፣ በደቡብ ሱዳንና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚዋሰን የአኙዋክ ዞን ነው፡፡

አኮቦ ወርቅ የኖርዌይ ኩባንያ ሲሆን ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በኩል የ6.5 በመቶ ባለአክሲዮን ነው፡፡ በተጨማሪም አኮቦ ወርቅ ኢትኖ ማይኒንግ (ETNO – Ethiopia & Norway) የሚባል ሌላ የወርቅ ማውጫ ድርጅት በኢትዮጵያ ያለው መሆኑን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡

የአኮቦ ተቀጥላ የሆነው ኢትኖማይኒንግ የሚያንቀሳቅሰውን የሰገሌ የወርቅ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሁለት ዓመታት በፊት በዲማ ተገኝተው ማስመረቃቸው ይታወሳል፡፡

ስራውን ለማቀላጠፍ የገንዘብ ዕጥረት እንደገጠመው የገለፀው ኩባንያው እስከ ባለፈው ወር ድረስ (February 2026) ድርጅቱ 80 ኪሎ ግራም ወርቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቅረቡን አትቷል፡፡

አኮቦ ወርቅ ያጋጠመውን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት ሲል ወደፊት በወርቅ የሚከፈል 392 ሚሊዮን የስዊድን ክሮነር (42 ሚሊዮን ዶላር) ሞኒታሪ ሜታልስ (Monetary Metals) ከሚባል ድርጅት መበደሩን ገልጿል፡፡

የሚከፈለውም ወርቅ 269 ኪሎ ግራም ነው፡፡ ክፍያው የሚያልቀው በሚቀጥለው ዓመት በፈረንጆች (June 2027) ሲሆን በዓመት የ22 በመቶ ወለድ አለው፡፡ ብድሩ ተከፍሎ እስኪያልቅ አበዳሪው ሞኒታሪ ሜታልስን 3 በመቶ በመያዝ በአኮቦ ወርቅ ቦርድ ውስጥም አንድ ታዛቢ ያስቀምጣል፡፡ 

ኦክስፋምን ጨምሮ በርካታየመብት ተሟጋች ድርጅቶች የትልልቅ ወርቅ አውጪ ኩባንያዎች መስፋፋት በጋምቤላ የደን መመናመን፣ የሜርኩሪና ሌሎች መርዛማ ኬሚካሎች በከፍተኛ መጠን መስፋፋት፣ የአፈርና ውሃማ አካላት መበከልና የአነስተኛ ወርቅ አውጪዎች ከመሬታቸው መገፋት አሳሳቢ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ 

በዲማ ወረዳ ከአንድ ቶን አፈር የሚገኘው ወርቅ ከ23 ግራም በላይ በመሆኑና በዓለም ከፍተኛ የሚያስብለው በመሆኑ ሌሎች ትላልቅ የወርቅ ድርጅቶች ኬፊ (Kefi Gold)፣ አላይድ (Allied) ወርቅና ሌሎችም ዓይናቸውን ጋምቤላ ላይ ጥለዋል፡፡ [ዋዜማ]