ዋዜማ- ሁለት ወር ገደማ ለቀረው 7ኛው ጠቅላላ ሀገር አቀፍ ምርጫ፣ የሲቪል ሰርቪስ (የመንግስት) ሰራተኞች “በግዳጅ” የመራጭነት ካርድ እንዲያወጡ እየተገደዱ መሆኑን ዋዜማ ባደረገቸው ክትትል ተረድታለች፡፡
በፌደራል፣ በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ የምርጫ ካርድ እንዲያወጡ በገዢው ብልፅግና ፓርቲ በኩል እቅድ ወጥቶ እየተፈፀመ መሆኑን ካሰባሰብነው መረጃ ተገንዝበናል።
ምንም እንኳን እቅዱ ከገዥው ብልጽግና ፓርቲ ቢሆንም፣ የሚፈጸመው በየደረጃው ባሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኩል መሆኑን ያነጋገርናቸው አራት መካከለኛና ከፍተኛ የፓርቲ መዋቅር አስተባባሪዎች አረጋግጠውልናል፡፡ የመራጮች ምዝገባ ከመጀመሩ አስቀድሞ በየደረጃው ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በወረደው አቅጣጫ፣ መሠረት እቅዱ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች በአስገዳጅ ሁኔታ በቀነ ገደብ የምርጫ ካድር እንዲያወጡ አቅጣጫ መቀመጡን ዋዜማ የተመለከተችው የውስጥ ማስታወሻ ያመላክታል፡፡ ዋዜማ ከተመለከተቻቸው የውስጥ ማስታወሻዎች መካከል ለአንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የተላለፈው መልዕክት፣ አስገዳጅነቱን ለማመላከት “ጥብቅ ማስታወቂያ” በሚል የተገለጸ ነው፡፡
በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ በተላለፉ “ጥብቅ” ማሳሳቢያ አዘል ማስታወቂያዎች፣ ሁሉም ሠራተኞች የምርጫ ካርድ አውጥተው ለሚሰሩበት ተቋም ተጠሪዎች የማሳወቅ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ሠራተኞች በተቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት የምርጫ ካድር ካወጡ በኋላ፣ የመራጭ መለያ ቁጥራቸውን በየመሥሪያ ቤቱ ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአለቆቻቸው አስገዳጅ ጫና የምርጫ ካርድ ማውጣታቸውን ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የፌደራል መንግሥት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ገልጠዋል፡፡ ሠራተኞች የመራጮች ምዝገባ ከተጀመረበት የካቲት 28፣ 2018፣ ዓ፣ም ጀምሮ በሁለት ቀን ውስጥ በአመዛኙ ተመዝግበዋል ተብሏል፡፡
በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ የምርጫ ካርድ አውጥተው መለያ ቁጥራቸውን ያላስመዘገቡ ሠራተኞች፣ ለብቻቸው ሰብሰሰባ ተጠርተው ጫና እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል፡፡ የምርጫ ካርድ አውጥተው መለያ ቁጥራቸውን ያላስመዘገቡ ሠራተኞች፣ “አስቸኳይ የሰብሰባ” የተጠሩበትን ማስታወሻም ዋዜማ ተመልክታለች፡፡
ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች የመራጭነት መለያ ማውጣታቸውን ለመስሪያቤታቸው ተጠሪዎች የመለያ ቁጥራቸውን ማሰመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁኔታውን ለዋዜማ ካስረዱት የዚሁ ተግባር አስፈጻሚዎች መካከል አንዱ፣ በሚሰሩበት ትምህርት ቤት በአስገዳጅ ሁኔታ ሁሉንም መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ምርጫ ካርድ እንዲያወጡ በማድረግ ሪፖርት ማቅረባቸውን አረጋግጠውልናል፡፡
ሠራተኛውን የመራጭነት መለያ የማስወጣት አቅጣጫ የወረደው የመራጮች መዝግባ ከመጀመሩ አስቀድሞ መሆኑን ዋዜማ የደረሳት የአንድ ስብሰባ ድምጽ ቅጅ ያመላክታል፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሕዝባዊ መንግሥት ስለማጽናትና ስለ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በሚያትት ስብብሰባ፣ ሠራተኛው ምርጫ ካርድ ማውጣት የዜግነት ግዴታ እንዳለበት የሚያትት ማብራሪያ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣ አዋጅ ቁጥር 1394/2017 መሠረት፣ ዜጎች ምርጫ ካርድ እንዲያወጡ የመቀስቀስ ኃላፊነት የተሰጠው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው፡፡ ቦርዱም ቢሆን፣ በአዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የግንዛቤ ትምህርት ከመስጠት የዘለለ ዜጎች በአስገዳጅ ሁኔታ የምርጫ ካርድ እንዲያወጡ ማስገድ አይችልም፡፡
ዜጎች ምርጫ ካርድ እንዲያወጡ በቅድመ ሁኔታ የማስገደድ አካሄድ መኖሩን ጥቆማ እንደደረሰው የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ ጠቁመዋል፡፡ ሰብሳቢዋ የመራጮች መዝግባን አስመለክቶ መጋቢት 4፣ 2018፣ ዓ፣ም በሰጡት መግለጫ፣ ዜጎችን በመሰረታዊ አግልግሎቶች ጭምር የማስገደድ እንቅስቃሴ መኖሩን መረጃ ደርሶናል ብለዋል፡፡
የመራጮች መዝግባ ከመጀመሩ አስቀድሞ “በየሰው ቤት እየተሄደ” የምርጫ ካርድ የማስወጣት ቅስቀሳ መደረጉን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡ በምርጫ አዋጁ መሠረት የመራጮች ትምህርት የሚሰጠው ቦርዱ ወይም ፈቃድ የሰጠው ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ብቻ ናቸው፡፡
ማንኛውም ዜጋ ለመራጭነት የሚያበቃውን ካርድ የማውጣት ነጻ ፈቃድ እንጂ ግዴታ እንደሌለበትም ተናግረዋል፡፡ ቦርዱ የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ፣ ዜጎች የመራጭነት ካርድ እንዲያወጡ ማስገድድ፣ ጫና የመፍጠርና ቅስቀሳ መቆም እንዳለበት ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቃቸውን ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል፡፡ [ዋዜማ]
