ዋዜማ- ከሁለት አመታት በላይ የተካሄደውን ጦርነት ከቋጨው የፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ከሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ከቀውስ ያልወጣው የትግራይ ክልል ፤ ያጋጠመውፖለቲካዊ ቀውስ በክልሉ ውስጥ በርካታ ፖለቲካዊ አንጃዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከ2016 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ጀምሮ በአሉባልታ ደረጃ የነበረው በሕወሓት ውስጥ ክፍፍል ተፈጠረ የመባሉ ጉዳይ በዚያው አመት ነሃሴ ወር ላይ የተካሄደውን 14ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ተከትሎ በይፋ ወጥቷል፡፡ 

የድርጅቱ ሊቀ-መንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመሩት ቡድን እና በወቅቱ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት ቡድን በየፊናቸው በሚድያ ፕሮፓጋንዳ ከታገዘ የቃላት ጦርነት አንስቶ፤ በኋላም አመራሮቹ የክልሉ ‹‹የማይነቀነቅ ምሰሶ›› በማለት የሚኮሩበትን የትግራይ ተዋጊ ሃይል እስከመሰንጠቅ የደረሰ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ 

የጸጥታ ሃይሉ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች (ከኮር በላይ በመባል የሚጠሩት) ጥር 15 ቀን፤ 2017 ዓ.ም ባደረጉት ስብሰባ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራውን ጊዜያዊ አስተዳደር በማውገዝ፤ በግልጽ ለህወሓት ያላቸውን ውግና ሲገልጹ ባለከፍተኛ ማዕረግ ጀነራሎችን ጨምሮ ብዛት ያላቸው ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ሕወሓትን የሚደግፉት የሠራዊቱ አመራሮች ጄነራል ገብረ እግዚአብሄር በየነን ጨምሮ ሌሎች መኮንኖችን ማገዳቸው ይታወሳል። 

ውሳኔው በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩትን ስምረት ፓርቲ ጨምሮ በክልሉ ውስጥ በርካታ የፖለቲካ ሃይሎች እንዲፈጠሩ፣ በጎጥ እና አካባቢ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ፣ ሃይልን ማእከል ያደረገ የዞን ፣ ወረዳ እና ከተማ አመራሮች ለውጥ እንዲሁም ውሳኔው በተሰጠበት እለት ስብሰባውን ረግጠው የወጡት ከፍተኛ መኮንኖች ከትግራይ ሃይሎች የተገነጠለ እና ራሱን ‹‹የሓራ መሬት›› ወይም ‹‹ነጻ መሬት ታጋዮች›› በማለት የሚጠራውን ታጣቂ ሃይል እንዲያቋቁሙ በር ከፍቷል፡፡ 

ይኸው ‹‹የሓራ መሬት››  ታጣቂ ሃይል የአፋር ክልልን ከትግራይ ጋር በሚያዋስኑት አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብና ደቡብ ምስራቅ ትግራይ ዞኖች ድንበር አካባቢዎች  ይንቀሳቀሳሉ፡፡ 

የሓራ መሬት ታጣቂዎችን የሚመራው ማንነው?

ብ/ጄነራል ገብረ-እግዚአብሄር በየነ (ወዲ አንጥሩ) ጥር 15 ቀን፤ 2017 ዓ.ም የተደረገውን የከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እና የጦር ግንባር አዛዦች ስብሰባ ረግጠው ከወጡት መኮንኖች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ከ4 ወራት በኋላ ግን በፓርቲ የማይታዘዝ የራሳቸውን ሰራዊት ለመፍጠር በአፋር እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢ መውረዳቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

በክልሉ በተፈጠረው ሁኔታ ቅሬታ የነበራቸው የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የዞን እና ወረዳ አመራሮች፣ በትግራይ ሃይል ውስጥ በአመራርነት እንዲሁም በተራ የሰራዊት አባልነት ደረጃ ላይ የነበሩ ወታደሮች እንዲሁም ሌሎችም ወጣቶች ጀነራሉን በመከተል ከመሰባሰብ ባለፈ በአፋር የሚንቀሳቀሰው እና እኝሁ ጀነራል በበላይነት የሚመሩት ታጣቂ ሃይል አባል ሆነዋል፡፡

ታጣቂ ሃይሉን በበላይነት የሚመሩት ብ/ጄነራል ገብረ-እግዚአብሄር በየነ (ወዲ አንጥሩ)፣  እንደሆኑ እሳቸውና የቀድሞው የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ በተደጋጋሚ ቢናገሩም፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩትና በርካታ የቀድሞ የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላትን ያቀፈው ስምረት ፓርቲ የታጣቂ ሃይሉ ፖለቲካዊ ክንፍ እንደሆነ በተደጋጋሚ ስሙ ይነሳል፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳም ሆኑ ምክትሎቻቸው ፓርቲው የሚመራው ወታደራዊ ሃይል እንደሌለ በመግለጽ መረጃውን ውድቅ አድርገውታል። 

ታጣቂ ሃይሉ በአፋር ክልል ነፍጥ አንግቦ የሚንቀሳቀስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል ያለውን ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲሁም ህወሃትን ለማስወገድ እንደሚታገል ቢገለጽም፤ የታጣቂ ሃይሉ አመራሮች ግን ወታደራዊ መንግስት የመመስረት ፍላጎት እንደሌላቸው እና በክልሉ ውስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ለመፍጠር እንደሚታገሉ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ከ3 ወራት በፊት በደቡብ ትግራይ ዞን ወጀራት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንዲሁም በአፋር መጋሌ ወረዳ ከትግራይ ሃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ከሁለቱም ወገን በኩል የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮም ጥቃት ተከፍቶብኛል ሲል ክስ አቅርቦ ነበር፡፡

ቡድኑ በፌደራል መንግስት ይደገፋል?  

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና ህወሃት ይኸው በአፋር የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ሃይል  ጌታቸው ረዳ በሚመሩት ስምረት ፓርቲ  እንደሚመራና የፌደራል መንግስት በገንዘብ እና በጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደሚያደረግለት በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል። 

“የፌደራሉ መንግስት የትግራይ ተወላጆችን እርስ በርስ ለማጋጨት በማሰብ ታጣቂ ሃይሉን እየደገፈ መሆኑን እናውቃለን፣ አሁንም በራችን ለሰላም ክፍት ነው ፣ ወደ ትግራይ ተመለሱ” የሚሉ ጥሪዎችንም ሲያስተላልፉ ቆይተዋል። 

ሆኖም ታጣቂ ሃይሉ የፌደራሉ መንግስት የሚያደርግለት አንዳችም ድጋፍ እንደሌለ በመጥቀስ፤ በክልሉ ውስጥ ሁሉን ያማከለ ፖለቲካዊ ተሳትፎ እስከሚፈጠር ድረስ ትግሉን እንደሚቀጥል ይናገራል። 

በአንዳንዶች  ታጣቂ ሃይሉ በፌደራሉ መንግስት ይደገፋል የሚል መደምደሚያ ላይ የተደረሰው ጣቂው ቡድን ነፍጥ አንግቦ በጎረቤት ክልል አፋር ያለችግር መንቀሳቀሱ እንደሆነ የሚገልፁት የክልሉ አመራሮች፤  “ለሰላማዊ ዜጎች ስጋት የሚሆንን ታጣቂ ሃይል ከለላ መስጠት ብዙ ትርጉም አለው” ሲሉም ይደመጣሉ። 

ስምረትና የሓራ ታጣቂዎች 

ስምረት ፓርቲ ከጀርባ የታጣቂ ቡድኑን ይመራል የሚል የበረታ አስተያየት ይቀርብበታል። ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የቀድሞው የደቡብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃብቱ ኪሮስ በአሁኑ ወቅት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚደንት ናቸው። የስምረት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር “የሓራ መሬት ታጣቂዎችን አደራጅታችሁ ፣ ድጋፍ ታደርጋላችሁ ይባላል የርስዎ አስተያየት ምንድነው?  ብለን ጠይቀናቸው ነበር። “አሁን በጥሩ ቁመና ላይ እንገኛለን፣ በአሁኑ ወቅት የፌደራል መንግስት የሚያደርግልን አንዳችም ድጋፍ የለም፤ ድጋፍ የሚያደርጉልን በሃገር ውስጥና በውጪ ያሉ የትግሉ ደጋፊዎች ናቸው፣ እስካሁንም ወደ 3 ሚሊየን ብር ገደማ ድጋፍ አድርገውልናል” ብለዋል።  

“እኛ ያሉት ስምረት ፓርቲም የትጥቅ ትግሉ አካል ነው እንደማለት ይሆን?” በሚል ከዋዜማ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፤ “የትግሉን አላማ እንደግፋለን እንጂ ፓርቲያችን የሚመራው ሰራዊት የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። [ዋዜማ]