Abiy Al Sisiዋዜማ ራዲዮ- የሕዳሴው ግድብ የደረሰበትን ምስቅልቅልና ዘረፋ ተከትሎ ግብፅ ከኢትዮጵያና ሱዳን ጋር ስታደረግ የነበረውን የሞት ሽረት ድርድር አቋርጣለች። በግድቡ ተፅዕኖ ዙሪያ ሲሰሩ የነበሩ ጥናቶችም አስታዋሽ አጥተዋል።

ግብጽ እንዲጀመር ስትወተውተው ከነበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሀ አሞላል ድርድር ራሷን ማግለሏል በድርድሩ ተሳታፊ ከነበሩ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ግብጽ ይህንን እርምጃ መውሠዷም ያልተጠበቀና አስገራሚ እንደሆነም ጉዳዪን በቅርበት ከሚያውቁ ሠዎች መረዳት ችለናል። ካይሮ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጀመር አንስቶ ግድቡ በሀገሬ ህልውና ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል መረጃ ለአለም ይፋ እንዲደረግ ስትጥር እንደነበር ይታወቃል።

በዚህም ሳቢያ የግድቡን የውሀ አያያዝና አለቃቀቅ እንዲሁም ግድቡ በአባይ ወንዝ የታችኛው ተፋሠስ ሀገራት ግብጽና ሱዳን ላይ ሊያደርስ የሚችለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖን እንዲያጠኑ የሚመረጡ አለማቀፍ ኩባንያዎች የራሷን ፍላጎት የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር ስትፋለም ቆይታለች።

እነዚህ ሁለት ጥናቶች የአለማቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ባቀረባቸው ምክረ ሀሳቦች መነሻነት እንዲጠኑ ከስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።
በግድቡ ዙርያ ጥናቱን የሚያደርጉት ኩባንያዎች አመታትን ከወሰደ ድርድር በሁዋላ ተለይተው ስራ ከጀመሩ በሁዋላ ግብጽ በመሀል አንድ ሀሳብ እንዳነሳች የዋዜማ ምንጮች ይናገራሉ። እሱም ጥናቱ ይካሄድ ነገር ግን በፍጥነት በግድቡ ውሀ አሞላል ላይ እንደራደር የሚል። ኢትዮጵያና ሱዳንም በግብጽ ሀሳብ ተስማምተው ሶስቱም ሀገራት በየራሳቸው አምስት አምስት በድምሩ 15 ሙያተኞች ያሉበትን የተመራማሪዎች ቡድንን መርጠው በግድቡ የውሀ  አሞላል ላይ መነጋገር ይጀምራሉ። የግድቡ ወሃ አሞላልና አለቃቀቅ ምን መምሠል እንዳለበትም ወደ መስማማት ደረጃ ተቃርበው ነበር።
የውይይት ሂደቱን የሚያውቁ ሠዎች እንደነገሩንም ሶስቱ ሀገራት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሀ መያዝ ከሚጀምርበት የመጀመርያው አመት ጀምሮ በሁለተኛው አመት ምን ያክል ውሀ ይዞ ሌላውን ውሃ መልቀቅ እንዳለበት በቢሊየን ሜትር ኪዩብ እየቆጠሩ ከስምምነት ደርሠው ነበር። ከሁለት ሳምንት በፊት ግን የሶስቱ ሀገራት ሙያተኞች የህዳሴው ግድብ በሶስተኛው አመት መያዝ ስላለበት ውሃ እየተነጋገሩ ባለበት ወቅት የግብጽ ተደራዳሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ መደራደር  አንፈልግም ብለው ስብሰባ አቋርጠው መውጣታቸው ተሰምቷል።

በህዳሴው ግድብ ላይ ሲካሄድ ከነበረው የተፅዕኖ ግምገማ ሁለት ጥናቶች በአቋራጭ ስለ ግድቡ ውሃ አሞላል እንወያይ ስትል የነበረችው ግብጽ እንዴት ራሷካስጀመረችው ድርድር ወጣች የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል።ለዋዜማ ራዲዮ መረጃውን ያደረሱ ባለሙያ እንዳሉት ካይሮ ራሷን ከዚህ ድርድር ባስወጣችበትና የግድቡ የግንባታ ሂደት በእጅጉ ተጓቷል የሚለው መረጃ የወጣበት ጊዜ ተቀራራቢ ነው።

ግብፅ ከድርድሩ ጠቅላ መውጣቷ ይሁን ጊዜያዊ ማፈግፈግ ግልፅ አይደለም። ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው የውሀና መስኖ ልማት ሚኒስቴር ባለሙያ እንደሚገምቱት ግን ግብፅ የሕዳሴው ግድብ ላይ የተፈጠረውን ደንቃራ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ በግድቡ ዙሪያ ስትራቴጂዋን ከልሳ ለመምጣት ጊዜውን መጠቀም ፈልጋ ሊሆን ይችላል።

ዋዜማ ራዲዮ ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንደዘገበችው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀገር በቀል በሆነውና የሀይድሮ ሜካኒካል ስራዎችን እንዲሠራና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችን ውል እንዲያስተዳድር ኮንትራት በተሠጠው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ የብቃት ማነስ ምክንያት መዘግየቱን መዘገቧ ይታወሳል።ከሰሞኑም ሜቴክ ለውሉ የወሰደው ገንዘብና የሠራው ስራ በፍጹም የማይገናኝ መሆኑን ጠቅሠው የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል። ታድያ እነዚህ መረጃዎች ከመሰማታቸው በፊት ኢትዮጵያ በሁለት ተርባይኖች ሀይልን የማመንጨት ዝግጅት እያደረገች ነው  በመባሉ ግብጽ  ሌሎች ጥናቶች ከመጠናቀቃቸው በፊት በውሃ አሞላል ላይ ለመነጋገር ቸኩላ ነበር።

የመረጃ ምንጮቻችን እንዳስረዱን  ቢአርኤል(BRL)  እና አርቴሊያ(Artelia)  በተባሉ የፈረንሳይ ኩባንያዎች እየተሠሩ ያሉት ሁለት ጥናቶች በጥቂቱ ሁለት አመት የሚወስዱ በመሆኑ ኢትዮጵያ ደግሞ ከጥናቶቹ በፊት ከአባይ ግድብ ሀይል ታመነጫለች ብለው በመስጋታቸው  ነበር በውሀ አሞላል ላይ መደራደር የፈለጉት። አሁን ግን ግድቡ  ሀይልን የማመንጨት አቅም ላይ አለመድረሱ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ንግግሮች ሁሉ በመረጋገጡ ግብጽ በውሀ አሞላል ድርድር ላይ ጊዜዋን ማጥፋት እንዳልፈለገች የሚጠቁሙ ፍንጮች አሉ ብለውናል ምንጫችን።

ይሄም ብቻ ሳይሆን ግብጽ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ መንግስታዊ ጫናን ለመፍጠር ስታደርጋቸው የነበረውን እንቅስቃሴ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእጅጉ መቀነሷ ታይቷል።ይህ በራሱ መልካም ቢሆንም  የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ጉዳዩን በቅርበት መከታተል እንዳለበት በጉዳዩ ያገባናል የሚሉ የመንግስት ሀላፊዎች ያሳስባሉ። ምናልባትም በኢትዮጵያ የታየው የመንግስት ለውጥ የምስራቅ አፍሪካን ዲፕሎማሲን የቀየረው በመሆኑና ግብጽም ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት የላቸውም ብላ የምትገናኛቸው ሀገራት አሁን በቀድሞ አቋማቸው ላይ ባለመሆናቸው አዲስ የቀጠና አጋር እየፈለገች ይሆናል። ስለዚህ መንግስት ሱዳንን ጨምሮ ከሀገራት ጋር የነበሩ ግንኙነቶች በየወቅቱ ያሉበትን ሁኔታ ሊፈትሽ ይገባል  ሲሉ ምክር የሚለግሱ ባለሙያዎች አሉ።
በሌላ በኩል በህዳሴው ግድብ ላይ እንዲጠኑ ውል ተይዞላቸው የነበሩ ሁለት ጥናቶችም አሁን በታሰበላቸው ጊዜ እየተከናወኑ አይደለም፣ ስራዬ ብሎ የሚከታተላቸው አካልም የለም። እነዚህ ጥናቶች እንዲፋጠኑም ካይሮ ትፈልግ ነበር።  ግብጽ የግድቡን ውሀ አያያዝና አለቃቀቅ እንዲሁም በአባይ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ የሚያመጣውን ተጽእኖ የሚያጠኑ ኩባንያዎችን በተመለከተ  ዋናውን አጥኚ ከግብፅ ጋር የጥቅም ግንኙነት ባለው ኩባንያ አሠርታ የግድቡን ጎጂነት መረጃ  ለማሠራጨት በጣም ትጥር ነበር።ሆኖም ከበርካታ ድርድር በሁዋላ በኢትዮጵያ ብዙ የሰራው የፈረንሳዩ ቢአር ኤልና የሆላንዱ ዴልታሬዝ ተመርጠዋል።
በኋላም  ዴልታሬዝ የተሠኘው ኩባንያ ከዋናው አጥኚ ቢአርኤል ጋር መስማማት ባለመቻሉ ከውሉ ወጥቶ ሌላኛው የፈረንሳይ ኩባንያ አርቴሊያ ተተክቷል።
በኢትዮጵያ : በሱዳንና ግብጽ እኩል በሚያዋጡት 4.5 ሚሊየን ዩሮ እንዲጠናም በ2009 ውሉ ተፈርሞ ነበር።ሆኖም ግን ግብጽ ጥናቱ ከተቀመጠለት ወሰን በላይ እንዲሄድ ሀሳብ እያቀረበች ሂደቱ ተጓቷል።ለምሳሌ በግድቡ መሠራት ምክንያት ወደታችኛው ተፋሠስ ሀገራት የሚሄድ ውሀ ጥራት ላይ የሚፈጠር ተጽእኖ ሱዳን ላይ ብቻ ነው እንዲጠና ወሰን የተቀመጠለት።ሆኖም ካይሮ የውሀ ጥራት ጥናት እኔም ጋር ይሰራ ብላ ሂደቱን ስታዘገይ ነበር። በሌላ በኩል በጥናቶቹ ውል ውስጥ ያልተካተቱ ነገሮችም እንዲካተቱ ግብጽ ስትወተውት ቆይታለች ።ከዚህ ውስጥ ከሜዲትራኒያን ባህር ጨዋማው ውሀ ሞልቶ ሲመጣ የመሬት ለምነቴን እንዳይጎዳ በአባይ ውሀ ነው ጨዋማነቱን እቀንስ የነበረው የህዳሴው ግድብ ካለ ግን የዚህ ውሀ አቅርቦት ላይ ችግር ስለሚፈጥር ተጽእኖው ይጠናልኝ የሚል ሀሳብ አቅርባለች። ኢትዮጵያ ደግሞ ለባህር መሙላት ተጠያቂው የአየር ንብረት ለውጥ እንጂ የምሠራው ግድብ አይደለምም ስትል ተከራክራ ሀሳቡ ከጥናቱ እንዲወጣ አድርጋለች። ይህን ሁሉ አድካሚ ሂደት ያለፈው ጥናት በአጥኚ ኩባንያዎች የመረጃ አሰባሰሰብ ደረጃ ላይ እያለ ለአጥኚ ኩባንያዎቹ በሚቀርብ ሀሳብ ላይ ሀገራቱ መግባባት አቅቷቸው ስራው ከቆመ ወራት ተቆጥረዋል። እርግጥ የአስገዳጅነት ውጤት እንደሌለው የሚነገረው ጥናቱ ቢጠና ተጠቃሚዋ ግብጽ መሆኗ ይነገራል።ሆኖም ግብጽ ባልተለመደ ሁኔታ ዝም ብላለች። [ዋዜማ ራዲዮ]