የፍሬወይኒ ጠበሳ!

 ባለጋሜው እንትና፣  ሰው የላከልህን መስፈንጠሪያ (ሊንክ) ሁሉ ዐይንህን ሳታሽ፣ ባልበላ አንጀትህ ክሊክ እያደረክ መክፈት የምታቆመው መቼ ነው? የእንትን ድረ ገጽም ቢሆን እኮ መጠንቀቅ አለብህ! ጌታዬ፣ ድረ ገጾች (መስፈንጠሪያዎች) የቫይረስ ማራቢያና የስለላ ወጥመዶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ስንት ጊዜ ሰምተሃል? ስትነዳ ቸኩለህ፣ ስትስፈነጠር ቸኩለህ፣ ስትበላ ቸኩለህ…ለእንትንም ቸኩለህ እንዴት ትዘልቀዋለህ? “ክሊክ አርግ ረጋ ብለህ…” ተብሎ እስኪዘፈን የምትጠራጠራቸውን መስፈንጠሪያውች አስቅድመህ በዚህ ድረ ገጽ እርዳታ አብጠርጥራቸው።    ሊንክ ስካን (Link Scan)   መቶ በመቶ ማረጋጋጫ ባይሰጥህም፣ አዲስ ገርል ፍሬንድህን ለመጀመሪያ ቀን እንዳሳየኸው ጓደኛህ በጥቅሻ አረንጓዴ ወይም ቀይ መብራት ያሳይኸል። ከዚያ አገባብህን መወስን ያንተ ጉዳይ ነው።

እንኮዬ፣ የምታውቂውም ሆነ የማታውቂው ሰው አንድ ሰነድ/ዶክመንት  ላከልሽ እንበል። መላላክ ያለ ነው። ዶክመንቱን ማየት ፈለግሽ እንበል። አንቺ እኮ አታፍሪም ቀጥታ ትከፍቺው ይሆናል! ለመክፈት ምን አስቸኮለሽ?! ቫይረስ ቢኖረውስ? አምና አፕዴት ያደረግሽው ጸረ ቫይረስ ይከላከልልኛል ብለሽ ባልሆነ?! በይ በዛው አንቲ ቫይረሱን አፕዴት አድርጊው። ለማንኛውም ዶክመንቱ ካጠራጠርሽ በቀላሉና በነጻ ማረጋገጥ ትችያለሽ። ይህን ቫይረስ ቶታል (VirusTotal) የተባለ ድረ ገጽ ተጠቀሚ። ፋይሉን ለድረ ገጹ ስጪው፣ እርሱ ልብሱን አውልቆ ብልቱን ፈትሾ ጊዜያዊ ውጤቱን ወዲያው ያሳውቅሻል። ውለታ እንዳይበዛብሽ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚስጡ ሌሎች ምንጮችን መፈለጉን ላንቺ ትቼዋለሁ።

“ገልቱው ኢንሳ በሐኪንግ ቲም የስለላ ወጥመድ ተጠቅሞ ሳይሰልለኝ አይቀርም” ብሎ እንቅልፍ ያጣም ይኖራል። ወገኛ!​ ​ቢሆንም ሽቅርቅሯ ሻምበል አታረገውም አይባልም።  መጀመሪያ “ፍሬወይኒ” ኢሜል ልካልህ ከሆነ እርሱን አጣራ።  ፍሬወይኒ የምትባል የድሮ ቺክ ብትኖርህ እንኳን አትመን።  የአክስትሽ ልጅ ስሟ ፍሬወይኒ ቢሆንም ተመልሰሽ የኢሜይል አድራሻውን አረጋግጪ። ፍሬወይኒዎች ይቅርታ፣ ሽቅርቅሩ ኢንሳ ነው ያሳሳተን።

ለማንኛውም “በሐኪንግ ቲም ሶፍትዌር ተሰልለን ይሆናል” ብለው ሐሳብ የገባቸውን ሰዎች ትንሽ ልርዳቸው ያለ ወገን መጥቷል፣ ሩክ ሴኲሪቲ (Rook Security)  ይባላል። ዜድኔት (ZDNet) እንደጻፈለት ከሆነ የሩክ ሴኲሪቲ “መፍትሔ-ሐክቲም” ጥሩ ጅማሮ ነው። ሩክ ሴኲሪቲ የሐኪንግ ቲም ማርከሻውን የቀመመው በቅርቡ ይፋ ከሆኑት የሐኪንግ ቲም ዶሴዎች በመነሳት ነው። ክትባት እንዴት እንደሚሰራ የረሳችሁ የሃይስኩል ደብተራችሁ አገላብጡ።ሩክ ሴኲሪቲ ቀልድም ይችልበታል፤ የሐኪንግ ቲም ማርከሻውን “ሚላኖ” ሲል ሰይሞታል። ሩክ ሴኲሪቲ ያቀረባቸው ሶፍትዌሮች ኮምፒውተራችን በሐኪንግ ቲም በተሠራ ጦር መወጋት አለመወጋቱን ያረጋግጣሉ ተብሏል። ጦሩን ማን እንደወረወረብህ ማረጋግጥ ያንተ ፋንታ ነው፣ ጦሩ ቂጥህ ላይ እንደተተከል ወይም ለጥቂት ስቶህ እንዳለፈ ከተነገረህ አነሰህ እንዴ?! ወሬም ውለታ አላበዛብህም፣ ይህን የሩክ ሴኲሪቲ ገጽ  ጎብኝ  (ክሊክ ለማድረግ አትቸኩል!)

“ሐኪንግ ቲም” የተባለው ድርጅት የመረጃ ቋቱ ከተሰበርና ለፀሐይ ከተጋለጠ በኋላ ለጥቂት ቀናት ወሬው ሁሉ እሱ ሆኖ ነበር። ብዙዎች ነገሩን ለመዘንጋትና ወደ ቀድሞው ጥንቃቄም እውቀትም ወደሌለበት የኢንተርኔት አጠቃቀማቸው ለመመለስ ከሰዓታት በላይ አልፈጀባቸውም። አንዳንዶች ደግሞ ሐኪንግ ቲምም ሆነ ኢንሳ የስለላ አቅማቸውን የተነጠቁ መስሏቸው መዘናጋት ጀምረው ይሆናል። ሰዉ ግን ለመዘናጋት ለምን ይቸኩላል? “ኢንሳም ሆነ ሌላ ሰላይ እኔን አይፈልገኝም” ብሎ ራሱን የሚያሞኝስ ይጠፋል? የኢንተርኔት ማኅበራዊ ትስስር ወደ ስለላ ወጥመድነት ተቀይሮ የስለላ መሣሪያ እንደሚሆን የማይጠርጠር ጅል ቢዘናጋ አይፈረድበትም።

“ሃይ ፕሮፋይል ታርጌት” ነኝ ካልክ አንተን ለመጥለፍ ሲባል የአንድሮይድ አፕ እንደሚፈጠር ጭምር ይነግርሃል፤ የሐኪንግ ቲምን ገመና እየተነተነ ያለው ሰው። አንተ የምትወደው ነገር ይጠናል፣ ከእርሱ ጋራ የተገናኝ አፕ ይፈጠርናበጉግል ፕሌይ ይለቀቃል፤ በማስታወቂያ እና አንት ልታገኛቸው በምትችላቸው መንገዶች ስል አፑ እንድታውቅ ይደረጋል። ዒላማ ያልሆነው ሕዝበ አዳም አፑን ቢጠቀም ባይጠቀም ሐኪንግ ቲም ጉዳዩ አይደለም። ልክ አንተ አፑን ስትጭን ግን ስልክህና ግንኙነቶችህ ያንተ እንዳልሆኑ ቁጠረው። እነፍሪቲ (ኢንሳ) እዚህ ደርጃ መድረሳቸው አልተረጋገጠም።

ደግነቱ አበሻ በእጁ ካልዳሰሰ ለእንትን አይከፍልም አሉ፤ እንጂማ የአሽሊ ማዲሰን (Ashley Madison)​ ድረ ገጽ በሐከሮች መሰበርም ስጋት የሚሆንበት አይጠፋም ነበር። የቺቺኒያን ጎብኚዎች ስም ዝርዝር ሐክ የሚያደርግና አደባባይ የሚያሰጣ እስኪመጣ ዘና ብላችሁ ሒዱ…ዛሬ ሰው ሁሉ ሒያጅ ነው…በየአቅጣጫው። በአሽሊ ማዲሰን በኩል የሔድክ አበሻ ካለህ ግን ከወዲሁ ንስሐ አባትህን አግኝተህ ላለፈውም ለሚመጣውም የሚሆን ኑዛዜ ፈጽም። መካና መዲናን ካልተሳለምክ ብዙ ጊዜ የለህም። እኔ የምመክርህ በዓለም ላይ ብዙ ስመ ሞክሼዎች እንዳሉህ እንድታስወራ ነው። ሐከሮቹ በአሽሊ ማዲሰን በኩል የወሰለቱትን ሰዎች ስም ዝርዝር ለንፋስ እንሰጠዋለን እያሉ እያስፈራሩ ነው። የፉገራ ኢሜይል አድራሻ ስለተጠቀምክ የምትተርፍ መስሎህ እንዳትዘናጋ። ሰዎቹ የባንክ አክውንትህን መርጃ ነው የሚለቁት። ይኼኔ እኮ በሚስትህ ካርድ ከፍለህ ይሆናል! በለው! ደግነቱ…ደግነቱ… አበሻ ካልዳሰሰ አይከፍልም።
​ ​
ወይ ጊዜ፣ በነጻነት መወስለት እንኳን አልተቻለም እኮ!

ያገሬ ሰው እንኳን ለአብሮ ሂያጅ ደላላ፣ የሞት መድሃኒትም ኦንላይን መግዛት አይችልም። ወይ ሞላጫ ድሃ ነው አለዚያ ጌቶቹ ኦንላይን እንዲገበያይ አልፈቀዱለትም።

ፍሬወይኒዬን ለቀቅ፣ ሴኲሪቲ ሴቲንግን ጠበቅ!

(ቸሩ ችርችሩ)