ዋዜማ- ባለፉት ሦስት ዓመታት የትምሕርት ስራ እንዳይካሄድ ክልከላ ጥለው የቆዩት የፋኖ ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ያሉ ትምሕርት ቤቶች በአዲሱ ዓመት ስራ እንዲጀምሩ ጥሪ ማድረጋቸውን ከተለያዩ አካባቢዎች ያሰባሰብነው መረጃ ያመለክታል።

ዋዜማ ከተመለከተቻቸው ደብዳቤዎች መረዳት እንደተቻለው፤ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን)  ተቆጣጥሯቸው በቆዩት የክልሉ አካባቢዎች ተቋርጦ የቆየው የትምህርት አሠጣጥ ሂደት እንዲጀመር ለተለያዩ  አደረጃጀቶቹ መመሪያ አስተላልፏል። የታጣቂ ቡድኑ አመራሮች ገደቡን ሙሉ በሙሉ ማንሳታቸውን ለአካባቢው ማህበረሰብና ለመምህራን በማሳወቅ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስመዘግቡ ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛሉ።

ባለፉት ሦስት ዓመታት፣ ታጣቂዎቹ በተቆጣጠሯቸው በርካታ የገጠር አካባቢዎች ትምህርት ተቋርጦ የቆየ ሲሆን፤ በተለይም በጎጃም ዞኖች ከከተሞች ውጪ የሚገኙ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉና በከፊል ለመዘጋት ተገድደዋል፡፡

የፋኖ ታጣቂዎች በቀጠና በተከፋፈለው አደረጃጀታቸው፤ አንዱ ጎራ ሲፈቅድ፤ ሌላው ትምህርት እንዳይሰጥ ሲከለክል የቆየ ቢሆንም፤ በቅርቡ ተፈጥሯል በተባለው ወጥ አደረጃጀት በትምህርት አሠጣጥ ላይ የተጣለውን ገደብ ሙሉ በሙሉ ማንሳታቸውን በአካባቢው ላለው ህብረተሰብ እና ለመምህራን ማሳወቃቸውን ሰምተናል፡፡

በመንግስት በኩል

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሁለት ሳምንታት በፊት ባወጣው የ2019 የትምህርት ዘመን የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፤ የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ 18 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን፤ 2018 ዓ.ም የሚከናወን ሲሆን፤ በመጪው መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም. መደበኛ ትምህርት ለማስጀመር አቅዷል። በመጪው የትምህርት ዘመን ከቅድመ አንደኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ባሉት እርከኖች ከ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል አቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስታውቋል፡፡

ሆኖም፤ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያለው ሁኔታ አሁንም ለመምህራን እና ተማሪዎች ደህንነት አስተማማኝ አለመሆኑን ለዋዜማ አስተያየታቸውን የሰጡ መምህራን ገልጸዋል። እንደ መምህራኑ ገለጻ፤ ታጣቂዎቹ ቀደም ሲል ያደርሱት የነበረውን ዛቻና ማስፈራሪያ ያቆሙ ቢሆንም፤ በርካታ ትምህርት ቤቶች በከፊልና ሙሉ በሙሉ የታጠቁ ኃይሎች ማረፊያ (ካምፕ) በመሆናቸው የደኅንነት ስጋት ፈጥረዋል።

ከደኅንነት ስጋቱ በተጨማሪ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት በወታደራዊ ሰፈርነት (ካምፕ) ያገለገሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸው፣ የሕብረተሰቡ የኑሮ አቅም መዳከም እና ግጭቱ ያስከተለው የሥነ-ልቦና ጫና ተማሪዎች በአፋጣኝ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት መሆናቸውን ጠቅሠዋል። የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ በሰሜኑ ጦርነትና በክልሉ ላለፉት ሶስት አመታት በቀጠለው ግጭት ሳቢያ፤ ከ6 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው መግለጹ ይታወሳል።

የባከኑ ዓመታት

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከአንድ አመት በፊት ባወጣው ሪፖርት መሰረት፤ በክልሉ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ በአማካይ ሦስት ሚሊዮን ገደማ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል፡፡

በ2016 የትምህርት ዘመን፤ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲያቋርጡ፤ ከእነዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑት ትምህርት ያልጀመሩ ህጻናት ናቸው፡፡ 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ትምህርታቸውን በግጭቱ ምክንያት ያቋረጡ ናቸው።

በ2017 የትምህርት ዘመን፤ ከ7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ የቻሉት 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወይም 40 በመቶ ያህሉ ብቻ ነው።

በ2018 የትምህርት ዘመን፤ ከ7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ 3 ነጥብ 96 ሚሊዮን (46.2 በመቶ) ያህሉ ብቻ ትምህርታቸውን መከታተል ችለዋል፡፡

መምህራኑ አጽንኦት ሰጥተው እንዳመለከቱት፤ የመማር ማስተማር ሂደቱን ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ የታጣቂዎቹ ክልከላውን ማንሳት ብቻ በቂ ባለመሆኑ፤ ትምህርት ቤቶችን ከጦር መሣሪያና ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ነፃ ማድረግ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሐምሌ እና ነሐሴ ፤2018 ዓ.ም ያወጣቸው ተከታታይ   ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት፤ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ9 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት በተለያዩ ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት ትምህርት ለማቋረጥ ተገድደዋል። ይሁን እንጂ ግጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ በቀጠለባቸው የአማራ ክልል ጎጃም፣ ጎንደር እና ወሎ አካባቢዎች ውስጥ በሚገኙ ገጠራማ ቀበሌዎች መሰረተ ልማቶች በመውደማቸውና ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምክንያት፤ በሀገሪቱ ከተፈናቀሉ ሕፃናት መካከል ግማሽ ያህሉ የሚገኙት በአማራ ክልል መሆኑን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ [ዋዜማ]