ዋዜማ- ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገውን የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤትን ተከትሎ በሚመሰርተው መንግስት ውስጥ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ለአዲስ ተሿሚዎች ለመስጠት መወሰኑን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።
የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን ውሳኔያቸውን በሚንስትር እንዲሁም ሚንስትር ዲኤታ ቦታዎች ላይ እየሠሩ ለሚገኙ ተሿሚዎች ማሳወቃቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ ረዘም ላሉ ዓመታት በአመራርነት ያገለገሉ ተሿሚዎች ራሳቸውን ለሌላ ተልዕኮ እንዲያዘጋጁ እንደተነገራቸው ጠቁመዋል። ይህም በሚንስትር እንዲሁም በሚንስትር ዲኤታነት እያገለገሉ ከሚገኙ ተሿሚዎች መካከል በአምባሳደርነት የሚሾሙ እንደሚኖሩ ጠቋሚ መሆኑን ሰምተናል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ሚንስትሮችንና ሚንስትር ዲኤታዎችን በሰበሰቡበት መድረክ “ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ለውጥ ይደረጋል” ሲሉ መናገራቸውን የገለጡልን ምንጫችን፤ ከዚህ ውሳኔያቸው በኋላ ከሚንስትሮች እና ሚንስትር ዲኤታዎች ጋር ለቀናት ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ነግረውናል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአምስት ዓመታት በፊት ካቢኔያቸውን ባዋቀሩበት ወቅት፤ ከ22ቱ የሚንስትርነት ቦታዎች መካከል ሦስቱን ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በአሁኑ የካቢኔ ምርጫም የሚንስትርነት ሹመት የሚሰጣቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የሚኖሩበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ምንጮች ነግረውናል። ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የፓርቲዎች አመራሮች፤ ከሹመት ጋር በተያያዘ እስካሁን ለፓርቲያቸው የቀረበ ጥያቄ አለመኖሩን የገለጹ ቢሆንም፤ ሹመት እንደሚሰጣቸው ቃል እንደተገባላቸው የሚገልጡ የፓርቲ አመራሮች መኖራቸውን ሰምተናል።
እየተካሄዱ ያሉ ስብሰባዎች
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሚንስትሮችን ለብቻ፤ ሚንስትር ዲኤታዎችንም ለብቻ ሰብስበው ማነጋገራቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ በስብሰባዎቹ ያለፉት ዓመታትን ከመገምገም ባለፈ አዲስ የተዘጋጁ ሰነዶች ቀርበው ውይይት እየተካሄደባቸው ነው። በስብሰባዎቹ ከሚቀርቡ ሰነዶች ባሻገር፤ የቡድን ውይይቶች እየተካሄዱ መሆናቸውንም ሰምተናል። ሚንስትሮች ስብሰባ ማድረግ ከጀመሩ ሁለተኛ ሳምንት ያስቆጠሩ ሲሆን በዚህኛው ሳምንት የተጀመረው የሚንስትር ዲኤታዎች ስብሰባ ደግሞ ስልክ ይዞ መግባት የተከለከለበት መሆኑን አውቀናል። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተካሄደ እንደሆነ የተነገረለት ይህ ስብሰባ ለተጨማሪ ቀናት እንደሚቀጥልም ምንጮች ጠቁመዋል።
የፓርቲዎች ጉዳይ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በነበሩ ጊዜያት ብልጽግና ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ንግግር አድርጎ እንደነበር የገለጡልን ምንጮች፤ በንግግሮቹ ከፓርላማ እና የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች ወንበር የዘለለና ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ቦታዎችን ያካተተ ድርድር አለመካሄዱን ጠቁመዋል። ከአምስት ዓመታት በፊት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ያገኟቸው ሹመቶች ከፓርቲዎች ይልቅ ተሿሚዎችን በቀጥታ በማነጋገር የተሰጡ መሆናቸውን ያስታወሱት ምንጫችን፤ በቀጣይ ጊዜያት ይሰጣሉ ተብለው የሚጠበቁ ሹመቶችን አስመልክቶ እስካሁን ለፓርቲዎች የቀረበ ይፋዊ ጥያቄ አለመኖሩን ገልጠውልናል።
የሥራ ጊዜያቸውን እያጠናቀቁ በሚገኙት የፌደራል መንግስት፣ የክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ካቢኔዎች ውስጥ ቦታ ካላገኙ ፓርቲዎች መካከል፤ በቀጣይነት በሚዋቀሩ ካቢኔዎች ውስጥ “እንካተት” የሚል ጥያቄ ያቀረቡ መኖራቸውንም ሰምተናል። ለዋዜማ መረጃ የሰጡ የአንድ ክልላዊ ፓርቲ አመራር፤ የፓርቲያቸው አባላት በካቢኔ ውስጥ ቦታ ተሰጥቷቸው እንዲሠሩ ፍላጎትና ተነሳሽነት እንዳላቸው ለብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ማሳወቃቸውን አረጋግጠውልናል። ይሁንና ከቃል ማሳወቂያ ባሻገር ለገዢው ፓርቲ በደብዳቤ ጥያቄ አለማቅረባቸውን አመራሩ አክለው ገልጠዋል።
በክልሎች ያለው እንቅስቃሴ
ከፌደራል መንግስት ባሻገር በክልሎችም ከመንግስት ምስረታ ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የገለጡ የዋዜማ ምንጭ፤ በሥራ ላይ ከሚገኙ አመራሮች መካከል ከምርጫ ጋር በተያያዘ በቂ ሥራ አልሠሩም በሚል ከሥራቸው የታገዱ መኖራቸውን ገልጠውልናል። ከምርጫ ቅስቀሳ እንዲሁም ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም በሚል ከተገመገሙና ከሥራ እንዲታገዱ ከተደረጉ አመራሮች መካከል፤ በቀጣይ በሚቋቋሙ ካቢኔዎች ውስጥ እንደማይካተቱ የተነገራቸው እንደሚገኙበትም ሰምተናል።
ከሙስና ጋር በተያያዘ እየተካሄዱ በሚገኙ ዘመቻዎች ተጠያቂ የሚደረጉ አመራሮች እንደሚኖሩ የገለጡልን ምንጫችን፤ ከምርጫ በኋላ በተደረጉ ግምገማዎች መሰረት የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ነግረውናል። [ዋዜማ]
