ዋዜማ- የፀጥታ፣ የመልካም አስተዳደርና የውጪ ምንዛሪ ዕጥረት  ችግሮች የውጪ ባለሀብቶችን በበቂ ለመሳብ እንቅፋት እንደሆኑበት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

የውጭ  ጉዳይ ሚንስቴር የ2015 ዓ.ም የስድስት ወራት አቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ የተቋሙ እቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አምባሳደር አለማየሁ ሰዋገኝ እንዳመለከቱት ባለሀብቶች በሀገሪቱ ባለው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ ቅሬታ አላቸው ብለዋል።

በአትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ያፈሰሰሱ  ኩባንያዎች በመልካም አስተዳድር ችግሮች  በተለይም ከመጠን በላይ የሆነ የታክስ ግመታ ፣ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠየቀ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ፤ የጸጥታ ችግሩ በቶሎ ካልተፈታ በቀጣይ አስቸጋሪ ስለሚሆን ምክርቤቱ እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የቅደመ ኢንቨስትመንተ  ጉብኝት አካሂደው ወደ አገራቸው  የሄዱ ኩባንያዎች ተመልሰው ወደ ስራ ለመግባት ሲሞክሩ በኢትዮጵያ ያለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳገዳቸው፣ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሃብቶች ደግሞ ትርፋቸውን በፈለጉት ሰዓት ለመውሰድ አሁንም ባለው የውጭ ምንዛሬ ዕጥረት የተነሳ ባለሃብቶቹን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚጠይቁት ጥያቄ ሆኗል ብለዋል፡፡

የተቋሙ ሪፖርት እንደሚሳው ባለፉት ስድስት ወራት ከዳያስፖራው በህጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት የተላከው የሪሚታንስ ገንዘብ  መጠን 2.34 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በዋና መስሪያቤትና በቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ከሚሰጡ አገልገሎቶች 380 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 379 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በአሜሪካ ዋሽንግተንና በጂቡቲ ከሚገኙ ህንጻዎች የተሰበሰበ ኪራይ 15.7 ሚሊዮን ብር ይገኝበታል፡፡

በ2013 እና 2014 ዓም መሬት እንዲሰጣቸው ጥያቄ ላቀረቡና 27 ቢሊዮን ብር ላስመዘገቡ 223 ዳሰፖራዎች መሬት እንዲሰጣቸው መወሰኑ በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን በተመሳሳይ 40 ቢሊዮን ብር ገንዘብ  ያስመዘገቡ 800 የዳያስፖራ  አባላት በተለያዩ የኢንቨስትምንት ስራዎች ለመሳተፍ ፍላጎት አቅርበው ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡

በ2015 ዓ.ም ግማሽ አመት 45,760 ዜጎች ከሳውዲ አረቢያ እንዲሁም በሌሎች አራት አገራት ይኖሩ የነበሩ ከ5400 በላይ ዜጎች በድምሩ ከ51 ሽህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር ቤት መመለሳቸው ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሻሻያ አዋጂ ፣ የውጭ ግንኙነት ሰራተኞች አስተዳደር ደንብ፣  የክብር ቆንስላ አሿሿም መመሪያ እያዘገጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የተዘጋጀው የክብር ቆንስላ አሿሿም መመሪያ አገሪቱ ያለምንም ክፍያ የምትሾማችውና የክብር ቆንስላ ሆነው የሚሰሩ ግለሰቦች በየሚሲዮኖች ምልመላ እንዲካሂዱ የሚረዳ ነው፡፡

ሪፖርቱን ተከትሎ የቋሚ ኮሚቴው አባላት የዲፐሎማቶችን ሹመትና ተቋሙ ውስጥ ስለሚነሱ ቅሬታዎች በተመለከተ፣ ከጦርነቱ ማግስት ከምዕራባውያኑ ስላለው ግንኑነት፣ ከጎረቤት አገራት ጋር ስለለው የግኝኑነት ሁኔታ፣ የቀይባህርን ፖለቲካና  የወደብ ተጠቃሚነት ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ቀይ ባህር ላይ ያለው ፖለቲካ በተለየም የቀይ ባህር ከውንስል በሚል የተመሰረተውና አራት የኢጋድ አባል አገራት የተካተቱበት ነገር ግን ኢትዮጵያን ያገለለው ይህ ስብስብ ኢትዮጵያ በቀጠናው ካላት መልከዓምድራዊ ቀረቤታ አንጻር ቢያንስ በታዘቢነት አንኳ አባል መሆን እንዴት አልቻለችም በማለት ጠይቀዋል፡፡ 

በሌላ በኩል ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነትና ኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተጠቀመቻቸቸው ያሉ የወደብ በር ስብጥሮች ከሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር በመሆን ሌሎች አማራጭ የውሃ በሮችን ስለማስፋትና ስለመጠቀም የታሰቡ ስራዎች ካሉ አንስተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮነን ለተነሱ ጥቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነነት በቀጣይ ሁኔታዎች ሲስተካካሉ ግንኙነቱን ወደ ተጠቃሚነት ለማሸጋገር እንደሚሰራ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ የወደብ አጠቃቀም ሰፋ ያለው በጂቡቲ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ፤ ከሰሞኑ በነበረው የሚንስትሮች ምክርቤት የስደስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ ሰፊ አገር በመሆኗ እና  ኢኮኖሚዋ እያደገ በመምጣቱ በቀጣይ ወደቦችን ማስፋት ስለሚያስፈለግ የታጁራ ወደብ አሁን ካለው የተሳለጠ አገልግሎትና የተሻለ ዋጋ  በሰፊው ለመጠቀም እሳቤ ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት በተደረገው ጥረት በእያንዳንዷ እንቅስቃሴ ሂደቱን የማጥላላት ዘመቻና  ጉድለት የሚፈልጉ ሃይሎች ፣ የተሰራን መካድና ጭቃ የመቀባት እንዲሁም ከእውነት ያለፉ ሲኖሩ በስራ እያሸነፍን ነው ብለዋል፡፡ 

የቀይ ባህር ካውንስል ኢትዮጵያ በቀጠናው ሊኖራት የሚገባውን ተጠቃሚነት እውቅና ያልሰጠ ዘላቂነትም ጥቅምም ስለማይኖረው ጉዳዩ ሊታይ እንደሚገባ በተደጋጋሚ ስለመናገራቸው እና በኢጋድ በኩል በሚኖር ግንኙነት በዚህ ቀጠና ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ፎረም እና አደረጃጃት ኢትዮጵያን ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን አጠናክረን አንቀጥላለን ብለዋል፡፡ [ዋዜማ]