Temesgen Desalegn Credit-Melody Sundberg
Temesgen Desalegn Credit-Melody Sundberg

ዋዜማ ራዲዮ- “ሕዝብን በመንግሥት ላይ በማነሳሳትና የተዛባ መረጃን በማሰራጨት” ወንጀል “ጥፋተኛ” ኾኖ በመገኘቱ የ3ዓመት እስር የተፈረደበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አሁንም የሚገኝበት አድራሻ ሊረጋገጥ  አልቻለም፡፡ ላለፉት አንድ ዓመት ተኩል ዝዋይ ማረሚያ ቤት  በእስር ላይ የከረመው ተመስገን ከሕዳር 28 ጀምሮ በዚያ ማረሚያ ቤት እንደማይገኝ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ለተከታታይ ቀናት ምላሽ እንዲሰጥ የተጠየቀው የዝዋይ ማረሚያ ቤት “ተመስገን እኛ ዘንድ የለም፣ አትድከሙ” ሲለን ቆይቶቷል ይላል ታናሽ ወንድሙ፡፡ ኾኖም ሰኞ ዕለት የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ተመስገን  እዚያው ዝዋይ እንደሚገኝ አንድ ስማቸውን መግለጽ የማይሹ መኮንን ጠቅሶ  ዘገባ ሠርቶ ነበር፡፡ ይህን ዘገባ ተከትለው ማክሰኞ ወደ ዝዋይ ያቀኑት ቤተሰቦቹ ግን አሁንም ስለመኖሩ እርግጠኛ ሊኾኑ አልቻሉም፡፡ “አለምም የለምም አይሉንም፤ አሁን ያለበትን እርግጡን አድራሻ የሚያውቅ ሰው አላገኘንም” ሲሉ ለተመስገን የቀድሞ ሥራ ባልደረቦች እንደገለጹላቸው ዋዜማ ተረድታለች፡፡

በከፍተኛ ጭንቀት ላይ የሚገኙት ቤተሰቦቹ ላለፉት ሰባት ቀናት የአገሪቱን ዋና ዋና ማረሚያ ቤቶች እየዞሩ ልጃቸውን ሲያፈላልጉ የከረሙ ሲኾን አየሁት የሚል አንድም ሹም አጥተናል ብለዋል፡፡

ታናሽ ወንድሙ ከትናንት በስቲያ የመንግሥት አቃቤ ሕግ የኾኑትን ሚኒስትር ጌታቸው አምባዬን ቢሯቸው አግኝቶ የወንድሙን መጥፋት ገልጾላቸዋል ሲሉ ለቤተሰቡ ቅርብ የኾኑ ወዳጆቹ የነገሩን ሲኾን፣ ኾኖም ሚኒስትሩ አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡትም ተብሏል፡፡ ያለበትን አጣርተን እናሳውቃለን የሚል አጭር መልስ ሰጥተውት አሰናብተውታል ይላል የቤተሰቡ የቅርብ ወዳጅ፡፡

ተመስገን ወደ ሸዋሮቢት ተዛውሮ ይኾናል በሚል ሁለት ጊዜ ወደዚያው ያመሩት ወንድሞቹ እዚያ እንደማይገኝ አረጋግጠው የተመለሱት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነበር፡፡ ቃሊቲና ቂሊንጦ በተመሳሳይ እንደሌላ ተገልጾላቸው ነበር፡፡

ዝዋይ ማረሚያ ቤት ዉስጥ የሚሠሩ ጠባቂዎችን በግል እስከማናገሩ የደረሱ የቤተሰቡ አባላት ምናልባት ተመስገን ጨለማ ቤት ዉስጥ በቅጣት መልክ ተዘግቶበት ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬያቸውን ገልጠውላቸዋል ተብሏል፡፡ ተመስገን በተደጋጋሚ ቅጣት ቤት ዉስጥ ብቻውን በጨለማ ተዘግቶበት እንደሚውል ይህም ተደጋጋሚ ቅጣት እንዲጣልበት የኾነው “ይህን መንግሥት አሞክሮ ለመጠየቅ ሕሊናዬ አይፈቅድም” ካለ በኋላ እንደሆነ የቤተሰቡ የቅርብ ሰዎች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን በአሞክሮ ሊፈታ ይችል የነበረው ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ነበር፡፡  የእስረኛው የቅርብ ወዳጆች እንደሚያምኑት ግን ተመስገን ለአመክሮ አመልክቶ ቢኾን እንኳ አገሪቱ አሁን ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ሊፈታ እንደማይችል በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡

“አሁን ለተፈጠረው ሕዝባዊ አመጽ ምክንያት የርሱ ጽሑፎች እንደሆኑ በጽኑ የሚያምኑ ካድሬዎች ብዙ ናቸው፣ ለርሱ ከፍተኛ ጥላቻ ነው ያላቸው” ይላል በፋክት መጽሔት  ላይ አብሮት የሠራ ባልደረባው፡፡

ተመስገን በዝዋይ እስር ቤት ተደጋጋሚ የጤና መታወክ የደረሰበት ሲኾን በተለይም በወገቡና በአንድ ጆሮው ላይ ከፍ ያለ ስቃይን እንደሚያስተናግድ ቤተሰቦቹ ይናገራሉ፡፡