Tom Malinowski
Tom Malinowski

ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያን እየጎበኘ ያለው የአሜሪካ መንግስት ልዑካን ቡድን ከመንግስትና ከተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች ጋር በወቅታዊ የሀገሪቱ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ይዞታ ጉዳይ ላይ ውይይት አደረገ።
የአሜሪካ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ሀላፊ ቶም ማልናዋስኪና የህዝብ ዲፕሎማሲ ምክትል ሀላፊ ብሩስ ዋርተን የተካተቱበት የልዑካን ቡድን ከጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያምደሳለኝና ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ባደረገው ውይይት በኢትዮጵያ ከዕለት ዕለት እየተባባሰ በመጣው የመብት ጥሰት ላይ የተሰማውን ቅሬታ አቅርቧል።

በፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችና ሌሎች ዜጎች ላይ የመፈፀመው እስራትና ግፍ የአሜሪካንን መንግስት እያሳሰበው መምጣቱን የልዑካን ቡድኑ ተናግሯል። የዶ/ር መረራና አቶ በቀለ ገርባ የእስር ጉዳይም በውይይቱ ተነስቶ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግስት እንደተለመደው ባለፉት ወራት የነበረውን ተቃውሞ “የሽብር ተግባር ነበር” ካለ በኋላ “የኢትዮጵያ ጠላቶችና የውጪ ሀይሎች በሀገር ቤት የተነሳውን “ተገቢ ቅሬታና ጥያቄ” ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የወሰዱበት ነበር”  ሲል ተከራክሯል።
አሜሪካ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና መብታቸው እንዲከበር ያላትን ፍላጎት የተናገረች ሲሆን ከኢትዮጵያ በኩል ማቅማማት መታየቱን ውይይቱን የተከታተሉ የዋዜማ ምንጭ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም የአሜሪካ መንግስት የጉዞ ማስጠንቀቂያ በማውጣቱ መንግስታቸው የተሰማውን ቅሬታ የገለፁ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የሀገሪቱ ሁኔታ ወደ ነበረበት “ሰላም” ተመልሷል ብለዋል።
የአሜሪካ የልዑካን ቡድን ከስድስት የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች ጋርም ተገናኝቶ ውይይት አድርጓል። ከመድረክ ፓርቲ ፕ/ር በየነ ጵጥሮስ፣ ከኢዴፓ ፓርቲ አቶ ሳህሉ ባዬ፣ ከሰማያዊ ፓርቲ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ ከአረና ፓርቲ አቶ ገብሩ አስራት፣ ከመኢአ ፓርቲ አቶ አሰፋ ሀብተ ወልድና ከኦፌኮ የፓርቲውን ተወካይ አነጋግረዋል። ውይይቱ በአመዛኙ በሀገሪቱ የፖለቲካ ቀውስና በፖለቲካ እስረኞች ዙሪያ ያተኮረ ነበር።