logo SDዋዜማ ራዲዮ-በሀገሪቱ ገፍቶ የመጣውን ፓለቲካዊ ቀውስ ለመፍታት ገዥው ግንባር ከተቀናቃኝ ሀይሎች ጋር ድርድር እንዲቀመጥ ጥያቄ ቀረበለት።
የዲፕሎማቲክ ምንጮች ለዋዜማ እንደገለፁት የመጀመሪያው የድርድር ግብዣ ከጀርመን መንግስት በኩል የቀረበ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ለድርድር ፈቃደኛ ስለመሆኑ ምላሽ አልሰጠም። ለጉዳዩ አፅንኦት ለመስጠት የጀርመኗ መራሒተ መንግስት አንጀላ ማርኬል ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝን አነጋግረው እንደነበር ይታወሳል።

የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ በሀገራዊ ቀውሱ ዙሪያ መንግስት፣ ተቃዋሚ ሀይሎች፣ ሲቪል ማህበረሰብ፣ መገናኛ ብዙሁንና ሁሉም ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ውይይት ማድረግ ችግሩን ለመፍታትና መረጋጋት ለማምጣት ሁነኛ መፍትሄ ነው ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል።
ህብረቱ ባወጣው መግለጫው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብት ይጨፈልቃል፣ ደም ማፋሰስንም ሊያቆም አይችልም ሲል ተችቶታል።

ሌላው የድርድር ግብዣ ከዩናይትድ ስቴትስ በኩል የቀረበ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ከድርድር ይልቅ ተቃዋሚዎች በሀገሪቱ ፖለቲካ የሚሳተፉበትን ዕድል በማመቻቸት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል።
የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ግን ሁሉን አካታች ድርድር ሀገሪቱን ወደተሻለ ጎዳና ስለሚወስዳት ገዥው ግንባር እንዲያስብበት መክሯል።
በኢትዮጵያ በኩል ቀና ምላሽ ባለመገኘቱ ያልተደሰተው በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ጠንካራ ትችት ያዘለ መግለጫ በማውጣት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተቃውሟል።
የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ወርቅነህ ገበየሁ የሚመሩት የልዑካን ቡድን በፊናው በአሜሪካ የአራት ቀናት ጉብኝት ያደረገ ሲሆን HR-128 በመባል  የሚታወቀውንና በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ የሚጠይቅ ረቂቅ አዋጅ ለመቀልበስ ከተለያዩ የአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር መክሯል።
የፀረ ሽብር ትብብሩን እንደመደራደሪያ ያቀረበው የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካን የተለያዩ የኮንግራስ አባላትንና የዋይት ሀውስ የደህንነት ምክር ቤት ስብሳቢን አግኝቶ ማነጋገሩን መረዳት ችለናል። [ተጨማሪ መረጃና ዝርዝሩን ከግርጌ የድምፅ ዘገባውን ይመልከቱት]

https://youtu.be/qjB6noZi2Fk