ዋዜማ ራዲዮ- የቀድሞው የደህንነትና መረጃ ሰራተኛ ጌታቸው ዋለልኝ በዘመነ ሕወሓት ከተከሰሰበት ወንጀል ነፃ ተብሎ ተሰናብቶ ነበር። አሁን ቀድሞ ውድቅ ተደርጎ የነበረው ክስ እንደአዲስ ተቀስቅሶ ጌታቸው ዋለልኝ ዘጠኝ አመት ተፈርዶበታል።


ጌታቸው በደህንነትና መረጃ አገልግሎት ሀላፊነቱ ወቅት ሙስናን ለመዋጋት ባደረገው ጥረት በሕወሓት ባለስልጣናት የግድያ ሙከራን ጨምሮ እስርና እንግልትን አሳልፏል።

ጌታቸው ዋለልኝ የታሰረው ባለፈው ሳምንት ሀሙስ ሲሆን ሁኔታውም ግራ አጋቢ እንደሆነባቸው ከቤተሰቦቹ መረዳት ችለናል።


ጌታቸው በብሄራዊ የመረጃ እና የደህንነት አገልግሎት ለአመታት በኢኮኖሚ ደህንነት ላይ የሰራ ሲሆን በ2010 አ.ም “ለግብረ አበሮቹ የአንጎላ ዜግነት የሚያሳይ መታወቂያና ፓስፖርት በማዘጋጀት : ለኤምባሲ ስራ ነው በሚል የሞባይል ቀፎዎችን ወደ ሀገር በተጭበረበረ መንገድ አስገብቶ እንዲከፋፈል አድርጓል ” በሚል ተከሶ ነበር።ክሱንም እስር ቤት ሆኖ ይከታተል ተብሎ ከአመት በላይ እስር ቤት ቆይቷል።


ሆኖም በጌታቸው ዋለልኝ ላይ የተነሳው ክስና የተፈጸመው እስር በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ የነበረውን እና በደህንት መስሪያ ቤቱ ድጋፍ የሚደረግለት ሀገር አቀፍ የኢኮኖሚ ሻጥር እየተከታተለ ስላጋለጠ እንደነበር ከሁለት አመት በፊት በዋዜማ ራዲዮ የተሰራው ምርመራ ቀመስ ሪፖርት ማጋለጡም ይታወሳል።

የጌታቸው ዋለልኝ ክስ እውነትም በኢኮኖሚ ላይ ያሉ ብልሽቶችን ስላጋለጠ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ በዋስ በእስር የተለቀቀ ሲሆን ትንሽ ወራት ቆየት ብሎም : ሰኔ 5, 2011 አ.ም የተመሰረተበትን ክስ ውጭ ሆኖ መከራከርም አያስፈልገውም ተብሎ ነጻ መሆኑም በጽሁፍ ተገልጾለታል።


ሆኖም ጌታቸው ዋለልኝ ከሀገራዊ ለውጡም በሁዋላ በደህንነትና ጸጥታ ተቋማት ላይ ላዩን ለውጥ ተደረገ እንጂ መሰረታዊ ለውጥ አልመጣም ፣ ሀገሪቱንም ዋጋ እያስከፈላት ያለው በደህንነትና ጸጥታ ተቋማት በቂ ስራ ባለመስራታቸው ነው በሚል በራሱ የሶሻል ሚዲያ ገጽ ላይ ትችቶችን በማቅረብ ይታወቃል።

በፌስቡክና መሰል ገጾቹ ላይም የሀገሪቱ የሰላም ጠንቅ የሆኑት ” ህወሀትና ኦነግ ሸኔ” የደህንነትና ጸጥታ ተቋማት ውስጥ ያሉ ሀላፊዎች ድጋፍ ነበራቸው በሚልም ትችት በማቅረብ ይታወቃል።


ጌታቸው ዋለልኝ ሐሙስ ጥር 14 ቀን 2013 አ.ም በቁጥጥር ስር መዋሉን ከቤተሰቦቹ መረዳት ችለናል። ጌታቸው ዋለልኝ በቁጥጥር ስር የዋለው ቀድሞ ነጻ የተባለበት ጉዳይ ላይ ይግባኝ በመጠየቅ በቂ ምስክሮች ተገኝተዋል በሚል ዘጠኝ አመት ተፈርዶበታል በሚል መሆኑንም ነው የሰማነው።

ግለሰቡ እዚሁ አዲስ አበባ እያለ መጥሪያ ደርሶት ሊከራከር ሲገባው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ የወንጀል ችሎት ዘጠኝ አመት ሲፈረድበት አለማወቁ ግራ አጋቢ ነው ። ይህም ብቻ ሳይሆን ጌታቸው ዋለልኝ በቁጥጥር ስር የዋለው ቀድሞ ነጻ በተባለበት ክስ ታግዶበት የነበረውን ንብረት ጉዳይ ለመከታተል ልደታ ፍርድ ቤት በተገኘበት መሆኑንም ነው መረዳት የቻልነው። [ዋዜማ ራዲዮ]