• ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ድጋሚ ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ተዘጋጅቷል

ዋዜማ- የዎላይት ዞን የክልልነት ጥያቄ ሕገመንግስቱን  ተከትሎ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘም ያለው የዎላይታ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ  ግንባር ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሊወስደው ነው፡፡

ሕገመንግስቱን የጣሰ ውሳኔ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በመወሰኑ የተነሳ በዞኑ ሕዝቡ ያላመነበት ሕዝበ ውሳኔ ተደርጓል ያለው ፓርቲው በዚህም የተነሳ የአገሪቱ ገንዘብ እና ጉልበት እንዲባክን  ሆናል ሲሉ የግንባሩ ሊቀመንበር ጎበዜ ጉአ ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡

የዎላይታ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር  ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ፓርቲዎች ጋር በመሆን ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ የተወሰነበትን አግባብ ወደ ፍርድ ቤት ብቻ ሳይሆን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕግ ጉዳዮች እና የሕገ መንግስት ጉዳይ አጣሪ ፍርድ ቤት ድረስ  እንዲወሰድ በፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ተወስኗል፡፡

ጉዳዩን በቅርቡ ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድም ከሕግ ባለሙያዎች ጋር እየሰሩ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

ፓርቲው በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወሰነውን ውሳኔ ላይ ያለውን ቅሬታ እና የይግባኝ አቤቱታ ሦስት ጊዜ በደብዳቤ ጠይቆ ምላሽ እንዳላገኘም አስታውቋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ከደቡብ ክልል የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ በድጋሚ እንዲካሄድ የወሰነውን የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔን ሰኔ 12 እንደሚያካሂድ ሐሙስ ሚያዚያ 26  2015 ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ምክክር ላይ ተናግሯል። 

በወላይታ፣ ጋሞ፣ ኮንሶ፣ ጎፋ፣ ጌዲኦና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም በአማሮ፣ ባስኬቶ፣ ደራሼ፣ አሌ እና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ሕዝበ ውሳኔ የተካሄደው ጥር 29 /2015 ነበር። 

ቦርዱ የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ “የሕግ ጥሰቶች ተፈጽመውበታል” በማለት ውጤቱን ሲሰርዝ፣ ቀሪዎቹ በአብላጫ ድምጽ አዲሱን ክልል ለማቋቋም የሰጡትን ድምጽ ግን አፅድቋል።

በድጋሜ እንዲካሄድ የተወሰነውን የዎላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔን በተመለከተ ሐሙስ በተደረገው የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ የተገኙት የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ  ሊቀመንበር አማኑኤል ሞጊሳ ከሕግ ጥሰቱ ጋር በተያያዘ ሲናገሩ 

‘’የሕግ ጥሰቱ የተጀመረው  የምርጫው ምዝገባ ላይ ሳይሆን የሪፈረንደም ውሳኔው ተሸሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብን ፍላጎት ያላካተተ አማራጭ ካመጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው ብሎ ቢወስደው የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም የመንግስት አመራሮችም ለዚህ መጠየቅ አለባቸው ፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ….. የዜጎችን መብት ሊያስከበር የተቋቋመ ተቋም ይህንን በመጣሱ መጠየቅ አለበት፡፡ …… ስለዚህ ይህ ሕዝበ ውሳኔ በሕግ ሊታገድ ይገባል  የሚል ሀሳብ አለኝ ‘’ብለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ተወካይ የሕዝበ ውሳኔው  ሕግ የተጣሰው  በፌዴሪሽን ምክር ቤት ነው፡፡ የወላይታ  ሕዝቦች የክልልነት ጥያቄን ሕገመንግስታዊ ነው፡፡ ስለዚህ ሕጉ የተጣሰው በዜጎች ብቻ ሳይሆን በፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በራሱ በምርጫ ቦርድ ጭምር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጥ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔ አድርጉ ብሎ ሲልክልን አይ አናደርግም የምንልበት ስልጣን የለንም ፡፡ተሰፍሮ ከተሰጠን ስልጣን ውጪ አንወጣም ተሰፍሮ የተሰጠንንም ስልጣን በአግባቡ ከመጠቀም ወደ ኃላ አንልም ብሏል፡፡ [ዋዜማ]