Photo-Tesfalem Woldyes-FILE

ዋዜማ- ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (RSF) በየዓመቱ ይፋ በሚያደርገው መረጃ የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት የአገራት ደረጃ “ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከነበረችበት 114ኛ ወደ 130ኛ” ደረጃ ማሽቆልቆሏን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በአለም ላይ ካሉ አገራት በጋዜጠኞች “በነፃነት የመዘገብ መብት”ና የመገናኛ ብዙሀን ነፃነት ከሚሰጡ አገራት ውስጥ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ምድብ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ከሶስት ዓመት በፊት ከፍተኛ መሻሻል አሳይታበት ከነበረው ደረጃ ቀስ በቀስ አፋኝ ወደሚባሉት ሀገሮች ተርታ እየተመለሰች መሆኑንም ሪፖርቱ መስክሯል።

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በአዲስ አበባ ሲከበር ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ምክር ቤት በበኩሉ በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ ለጋዜጠኞች አስፈሪ እየሆነ መምጣቱንና መንግስት ለሚዲያ ነፃነት መከበር ከዚህ ቀደም የገባውን ቃል እንዲያከብር ጠይቋል።

ጋዜጠኞች   በስራ ባሉበት ጊዜ በመንግስት የፀጥታ አካላት ያለ አግባብ እንዲታሰሩና እንዲንገላቱ እየተደረጉ በመሆኑ ይህም  አዲሱ የመገናኛ ብዙሀን አዋጅ የሚፃረር መሆኑን  የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀን ምክር ቤት ሰብሳቢ አማረ አረጋዊ ገልፀዋል ።

የመገናኛ  ብዙሀን አዋጁ  ጋዜጠኞች በስራ ላይ ባሉበት ጊዜ መታሰር እንደሌለባቸውና በጥፋት  ቢከሰሱም እንኳ በስራቸው ላይ ሁነው ክሳቸውን መከታተል እንዲችሉ የተደነገገ መሆኑ ይታወቃል።

 አማረ  እንደሚሉት  ” አሁን ላይ በጋዜጠኞች እየደረሰ ያለው ውክብያ ስራቸውን በነፃነት እንዳይሰሩ የሚያደርግ መሆኑንና በህገመንግስቱ የተሰጣቸው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት  የሚጥስ ነው” ብለዋል ።

በመንግስት የፀጥታ አካላት  በኩል በሰበብ አስባቡ እየተደረገ ያለው አፈናና ድብደባ ሚድያው በነፃነት የመዘገብ፣ የመንቀሳቀስ፣ የማሰብ ነፃነትን የሚጥስ መሆኑንና  እንዲህ ያለው ተግባር ከቅርብ ጊዜ ወዲህም  እየተባባሰ መምጣቱን መገናኛ ብዙሀን ምክር ቤት ገልጿል ። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋዜጠኞች ላይ እየተስተዋለ ያለውን አፈናና የሰብአዊ መብት ጥሰት በተለይም ሴት ጋዜጠኞች ወደ ዘርፉ እንዳይመጡ እንቅፋት እየሆነ መጥቷል ሲል ምክር ቤቱ አስታውቋል ።

በተመሳሳይ መገናኛ ብዙሃን መረጃዎች በሚያስተላልፉቀት ጊዜ  ከሀሰተኛ ዜና፣ ከጥላቻ ንግግር ፣ ከብሔርና ሀይማኖት ወገንተኝነት ነፃ እንዲሆኑ ከመቸውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት ሊሰሩበት የሚገባ መሆኑን ተረድተው ጋዜጠኞች ለሰብአዊ መብቶች መከበር ዘብ መቆም እንዳለባቸው የምክር ቤቱ ሰብሳቢ  አማረ አረጋዊ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በጎጥና በብሔር የተደራጁ መገናኛ ብዙሀን ወደ መደበኛውን የጋዜጠኝነት መርህ ተከትለው እንዲሰሩ በአገር ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ ጠይቋል። [ዋዜማ]