• Young Oromo Protestors SM
    Young Oromo Protestors SM

    “የኦሮሚያ ክልል በ18 ዞኖች እና በ342 ወረዳዎች የተከፋፈለ ሲሆን ሰመጉ በ33 ወረዳዎች ብቻ ባደረገው የመስክ ምርመራ ባገኘው ውጤት መሰረት 103 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 57 ሰዎች በጥይት የመቁሰል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል”

(ዋዜማ)-የቀድሞው ኢሰመጉ ያሁኑ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) በሀገሪቱ በተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ
በየጊዜው የሚያወጣቸው ልዩ ሪፖርቶች በጉዳዩ ዙሪያ በሚሰሩ ተቋማት ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጣቸው ናቸው

የአሜሪካ መንግስት በስቴት ዲፓርትመንት በኩል በየዓመቱ ለንባብ የሚያበቃቸው ጠንካራ እና ተቺ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ሪፖርቶች የሚመረኮዙት የሰመጉን መግለጫዎች ነው በሚል በመንግስት ዘንድ ጥርስ ከተነከሰበት ቆየ። ሰመጉ ከተመሰረተበት ከ1984 ጀምሮ አንድ ሁለት እያለ ሪፖርት ማውጣት ከጀመረ 140ኛው ላይ ደርሷል። ዛሬ መጋቢት 5 በፅህፈት ቤቱ በተሰበሰቡ ዲፕሎማቶች እና ጋዜጠኞች ፊት የተሰራጨው ልዩ ሪፖርት ሙሉ ትኩረቱንያደረገው ከህዳር ወር 2008 ዓ ም ጀምሮ የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንንበመቃወም በተለያዩ አካባቢዎች እየተደረጉ ባሉ ሰላማዊ ሰልፎች እና እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎች ላይ ነው።

በሰላሳ አራት ገፅ የተዘጋጀው ሪፖርት በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰውን የሰው እና የንብረት ጉዳት እና የምርመራ
ስራው እንዴት እንደተከናወኑ የሚያሳዩ ዝርዝሮችን በፎቶግራፍ ጭምር አስደግፎ የያዘ ነው።
“የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች ላይ በወሰዷቸው ከመጠን ያለፉ የኃይል እርምጃዎች የበርካታዜጎች ሕይወት ጠፍቷል” ይላል ሪፖርቱ በመግቢያው። “በርካታ ሰዎች በጥይት ተመትተው የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በርካታ ሰዎች ታስረዋል፣ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች የደረሱበት አይታወቅም፣ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከተለ ከባድ የንብረት ውድመት ደርሷል።”

በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ሰፊ አካባቢን ቢያካልልም ሰመጉ ባለው ውሱን አቅም ምክንያት ባለሙያዎቹን በመላክ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ማከናወን የቻለው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ብቻ ነው። የኦሮሚያ ክልል በ18 ዞኖች እና በ342 ወረዳዎች የተከፋፈለ ሲሆን ሰመጉ በ33 ወረዳዎች ብቻ ባደረገው የመስክ ምርመራ ባገኘው ውጤት መሰረት 103 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 57 ሰዎች በጥይት የመቁሰል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በ22 ሰዎች ላይ ማሰቃየት እና ድብደባ መፈፀሙን፣ 84 ሰዎች መታሰራቸውን እንደዚሁም 12 ሰዎች የደረሱበት ወይም ያሉበት አለመታወቁን ሪፖርቱ በዝርዝር ያስቀምጣል።

ግድያዎቹም ሆኑ ሌሎቹ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች አንድ የምርመራ ዘገባ ሊያሟላቸው በሚገባቸው መሰረታዊ መረጃዎች ዳብረው ቀርበዋል። በሪፖርቱ የተገደሉ እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ስም፣ ዕድሜ፣ የመኖሪያ አድራሻ፣ ሁነቱ የተከሰተበት ቦታ እና ሰዓት እስከ ተቀበሩበት ቦታ ድረስ በተብራራ ሁኔታ ተቀምጠዋል። አብዛኞቹ ሟቾች ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች፣ ተማሪዎች እና አዳጊዎች ናቸው። የግድያ ፈፃሚዎቹን ማንነት በተመለከተ ከአንድ ሁለት ቦታ በስተቀር በጥቅሉ በታጠቁ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች፣ የመከላከያ ሰራዊት፣ የአጋአዚ ጦር አባላት፣ የፌደራል/ ኦሮሚያ ፖሊስ አባላት በማለት ብቻ ይገልፃቸዋል።

ሰመጉ በጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የገዳዩቹን ማንነት በሪፖርቱ ያለመግለጹ ጉዳይ ተነስቶ ነበር። የሰመጉ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቁምላቸው ዳኜ ለጥያቄው በሰጡት መልስ የደርጊቱን ፈፃሚዎች ቢያውቁም “ከዳኝነት በፊት እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር” መብታቸውን ለመጠበቅ ሲባል በሪፖርቱ አለመካተቱን አስረድተዋል። “እከሌ እከሌን ገድሏል ብለን ልናወጣ አንችልም” ይላሉ አቶ ቁምላቸው። “ለሚመለከተው ለሚመረምር አካል ለማቅረብ ግን ዝግጁ ነን” ሲሉ እንደ ሁልጊዜውም ከፍትህ አካላትም ሆነ ከሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር ለመተባበር ያላቸውንት ፍላጎት ገልጸዋል።

አቶ ቁምላቸው ይህን ቢሉም ሰመጉ ያለው መረጃ ላይ ተመስርተው ሲያብራሩ ብዙዎቹ ግድያዎች የተፈፀሙት ከሰላማዊ ሰልፉ በኋላ መሆኑን፣ አንዳንዶቹ ግድያዎች የተፈፁሙት ከፖሊስ ጣቢያ ፊት እንደሆነ እና አንዳንዶቹ ሟቾች ከቤት ተወስደው እንደሆነ እና ፈጻሚዎቹም የመንግስት ሰዎች መሆናቸውን ሳይጠቁሙ አላለፉም። አንዳንዶቹ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ከግድያው በኋላ ከአካባቢያቸው በክልሉ ውስጥ ወዳለ ሌላ ቦታ መዛወራቸውን አስረድተዋል።

የሰመጉ ሪፖርት በኦሮሚያ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ዙሪያ ለሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች የተሟላም ባይሆን ውስን ምላሾችን ይሰጣል። በተቃውሞው ዙሪያ የታጣውን የገለልተኛ አካል ማጣራትም በፈር ቀዳጅነት ያከናወነ ነው። ከደረሰው ጉዳት ተሻግሮም መንስኤውን ለመፈተሽ የሞከረ ነው።

“መንግስት የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን በማርቀቅ ሂደት ዜጎችን በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ
ገጠርና ከተማ ነዋሪዎችን ባለማሳተፉ፣ ረቂቅ ሰነዱንም እስከዛሬ ለህዝብ ይፋ ባለማድረጉ የብዙ ዜጎችን ሕይወት ለቀጠፈውና የአካልና የንብረት ጉዳት ላስከተለው ቀውስ ምክንያት ሆኗል” ይላል ሪፖርቱ ስለ ተቃውሞው መንስኤ ሲያብራራ። “ረቂቅ ማስተር ፕላኑ ለባለሙያዎችና ለሌሎችም ባለድርሻ አካላት ቀርቦ ግልፅ ውይይት፣ ክርክር እና ትችት ሊደረግበት ሲገባ ለዓመታት በምሥጢር መያዙና ይዘቱም ለዜጎች አለመገለፁ ለጥርጣሬ፣ ለውዥንብርና ደም ላፋሰሰ ግጭት መንስዔ ሆኗል።”

ሙሉ መግለጫውን እነሆ https://www.luminpdf.com/viewer/wi7239WPq8DwhMWsa