Konso protest-FILE
Konso protest-FILE

(ዋዜማ)-በኮንሶ በተቀሰቀሰ ግጭት ሁለት ሰዎች ተገድለው ሶስት በፀና ቆሰሉ። ላለፉት ሰባት ወራት የዞን ይገባናል ጥያቄ አንስተው የደቡብ ክልል መስተዳድር እና የፌደራል መንግስትን ሲያፋጥጡ የቆዩት ኮንሶዎች በአፀፋው እየደረሰባቸው ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱን የአካባቢው ተወላጆች ይናገራሉ። የኮንሶዎችን ጥያቄ በህግ አግባብ መፍታት የተሳነው የክልሉ መንግስት ወደ አካባቢው ልዩ ኃይል በማሰማራት ተቃውሞውን ሊያዳፍነው እየሞከረ እንደሆነ ተወላጆቹ ይገልጻሉ።

በትናንትናው ዕለት መጋቢት 4 በደባና ቀበሌ የልዩ ኃይሉ አባላት የወሰዱት እርምጃ የዚሁ መገለጫ እንደሆነ ያስረዳሉ። የልዩ ኃይሉ አባላት ትናንት ረፋድ ላይ መጀመሪያ ያመሩት ዶካቱ ወደ ተሰኘች መንደር እንደነበር የሚገልፁት ተወላጆቹ የአካባቢውን ነዋሪ ወጥቶ በኃይል እንዲገጥማቸው ቢያስፈራሩም በሽማግሌዎች ልመና ወደ መጡበት ተመልሰዋል ይላሉ። ከቀትር በኋላ ሰባት ሰዓት ገደማ ደባና ወደ ተሰኘች ሌላ መንደር በመሄድ እና በቀበሌው አስተዳደር ፅህፈት ቤት በመስፈር የአካባቢውን ነዋሪዎች መተናኮል እንደጀመሩ ተወላጆቹ ያስረዳሉ። በዚህም ፋንታዬ ጊዩርጊስ የተባሉ የ42 ዓመት ጎልማሳ ከልዩ ኃይል አባላት በተተኮሰ ጥይት ተመትተው መገደላቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል። ከእርሳቸው በተጨማሪ አንድ ግለሰብ እንደዚሁ ሲገደል ሶስቱ ደግሞ በፀና መቁሰላቸውንም ይገልጻሉ።

በኮንሶ ለወራት በዘለቀው የነዋሪዎቹና የልዩ ኃይል ፍጥጫ ምክንያት ትምህርት ቤቶች እና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ ዝግ ሆነዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኮንሶ ወረዳ እና የአካባቢው ባለስልጣናት ለግምገማ ተጠርተው ወደ ክልሉ መቀመጫ ሀዋሳ ቅዳሜ መጋቢት 3 ሄደዋል። የሰሞኑ የኮንሶ ውጥረት የተቀሰቀሰው የአካባቢው ባህላዊ መሪ የሆኑት ካላ ገዛኸኝ ወልደዳዊት መታሰርን ተከትሎ ነው። ካላ ገዛኸኝ በታሰሩበት አርባ ምንጭ በኮንሶ ሰዎች እና በወንድማቸው መጎብኘታቸውን ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። በኮንሶ ወዝግብ ዙሪያ ዝርዝር መረጃ ከዚህ ሪፖርት ያገኛሉ፣ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑት http://wazemaradio.com/?p=1767