ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የእነ ጃዋር ሞሀመድን የህክምና ጉዳይ በተመለከተ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ህግን እና ስርዓትን የተከተለ አይደለም በማለት ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ ሰሚ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ይግባኝ ብሏል::

በሽብር እና ሌሎች ወንጀሎች ክስ የተመስርተባቸው ጃዋር ሞሀመድ፣ በቀለ ገርባ እና ሌሎች በመዝገቡ የተካተቱ ተከሰሾች ባሉበት የፌደራል ማረምያ ቤት የረሀብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ 20 ቀን እንዳለፋቸው ጠበቆቻቸው ይናገራሉ፡፡

ይህን ተከትሎ ላጋጠማቸው የጤና እክል የግል ህክምና ለማግኘት አቤቱታ ቢያቀርቡም በህጉ መሰረት ባሉበት ማረሚያ ቤት ህክምና እንዲያገኙና ከማረምያ ቤቱ አቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ወደ ፌደራል ጦርሀይሎች ሆስፒታል ተወስደው እንዲታከሙ የካቲት 2 ቀን 2013 ዓም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር፡፡

ሆኖም ተከሳሾች “መንግስት ባስቀመጣቸው ባለሞያዎች እና በመንግስት ሆስፒታል ለመታከም እምነቱ የለንም” በማለት እና የጤና ሁኔታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ መድረሱን በማከል በድጋሜ የካቲት 8 ቀን አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ቀድሞ የሰጠውን ትዕዛዝ በመሻር አቤቱታውን ተቀብሎ ተከሰሾቹ በአፋጣኝ የግል ሆስፒታል ህክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ይህን የተቃወመው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግም ህግን እና ስርዓትን የተከተለ ትዕዛዝ አይደለም በማለት ዛሬ ከሰዓት ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታውን አቅርቧል፡፡

በአቤቱታውም ማረሚያ ቤቶች በተቋቋሙበት አዋጅ መሰረት ማንኛውም ተከሳሽ ቅድሚያ ህክምና የሚያኘው በማረሚያ ቤቱ ሲሆን ከአቅም በላይ ከሆነ ወደ ጦር ሀይሎች ሆስፒታል ይወሰዳል እንደሚል አስታውሷል፡፡ የስር ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም የካቲት 2 ሲሰየም አግባብ ያለው ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም የካቲት 8 ያስተላለፈውን “በግል ሆስፒታል ይታከሙ” የሚል ትዕዛዝ ከመስጠቱ በፊት ግን ቀድሞ የሰጠው ትዕዛዝ መፈፀም አለመፈፀሙን መመርመር፣ ካልተፈፀመም ለምን ብሎ መጠየቅ ይገባው ነበር፤ ይህ ትክክለኛ ትዕዛዝ ስላልሆነ ይታገድልን በማለት ይግባኝ ብሏል፡፡

የይግባኝ አቤቱታው የደረሰው ችሎትም ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]