FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በበረራ አገልግሎቱ በአፍሪካ በቀዳሚነቱ  የሚታወቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መስጠት የሚችለውን አጠቃላይ የበረራ አገልግሎት አቅሙን ወደ 70 በመቶ እንዳወረደበት ዋዜማ ተረድታለች።

የወረርሽኙ ሥርጭት በዓለማቀፍ ደረጃ መስፋፋቱን ተከትሎ፣ በርካታ አየር መንገዶች የበረራ መዳረሻቸውን በመቀነስ ከግማሽ በታች በሆነ አቅማቸው ሲበሩ ቆይተዋል። በመጀመሪያም ለኮሮና ተዋህሲ መከላከያና መቆጣጠሪያ መሳሪዎችን እና ዘግየት ብሎ ደሞ ለበሽታው መከላከያ ክትባቶችን በጭነት አውሮፕላኖቹ ለተለያዩ አገራት በማሰራጨት እየሰራ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድም አሁንም በሙሉ አቅሙ የበረራ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ለዋዜማ የገለጹት የኩባንያው የኮርፖሬት ኮሚዩንኬሽን ማኔጀር ዓሊ መሐመድ ናቸው፡፡

በዚህም የተነሳ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት አየር መንገዱ ወደነበሩት መዳረሻዎች ሲያደርጋቸው የነበሩትን በረራዎች ቁጥር በመቀነሱ፣ በትላልቅ አውሮፕላኖች ሲደረጉ የነበሩትን በረራዎች በትናንሽ አውሮፕላኖች ለመብረር እንደተገደደ እና ባጠቃላይ የሁሉም አውሮፕላኖች ወንበር ተደማምሮ በወር ውስጥ በረራ ይደረጋል ተብሎ ከሚታሰበው አኳያ በሚጠበቅበት ልክ እየበረረ እንዳልሆነ ሃላፊው አክለው ገልጸዋል፡፡

የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተበት በመጀመሪያዎቹ ወራት አየር መንገዱ አሁን እየሰጠ ካለው የበረራ አገልግሎት አቅም በታች ሲሰጥ እንደነበር የገለጹት ዓሊ፣ በቀጣይ ጊዜያት ወደ ሙሉ አቅሙ ለመመለስ የሚችልበት ዕድል ከወረርሽኙ ሥርጭት  ጋር እንደሚያያዝ ጠቁመዋል፡፡

አየር መንገዱ ከሦስት ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ 149 መንገደኞችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ የበረራ ቁጥሩ ET302 የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኑ መከስከሱን ተከትሎ፣ ከመጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከበረራ አግዶት የነበረውን የቦይንግ ማክስ አውሮፕላን በአገር ውስጥ የሙከራ በረራ ካደረገ በኋላ ወደ ሙሉ በረራ መመለሱን የገለጸው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር፡፡

ባሁኑ ወቅት አራት የቦይንግ 737 አውሮፕላኖች ያሉት ኩባንያው፣ 25 ተመሳሳይ አውሮፕላኖችን ወደ በረራ ለማስገባት ገና የግዥ ትዕዛዝ ላይ እንደሆነ ዓሊ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ ካዘዛቸው ቦይንግ 737 አውሮፕላኖች መካከል የተወሰኑትን በተያዘው የፈረንጆቹ 2022 ዓ.ም ላይ እንደሚረከብ የገለጹት ማኔጀሩ፣ ምን ያህሉ አውሮፕላኖች በተያዘው የፈረንጆች ዓመት እንደሚገቡ ግን ካሁኑ በርግጠኝነት መናገር አይቻልም ብለዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]