• ሕግ ተላልፈዋል የተባሉ የሳተላይት ስርጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም ጥረት እየተደረገ ነው

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በቅርቡ ካስተላፋቸው ፕሮግራሞች ውስጥ የሙያ ስነ ምግባር ጉድለት ታይቶባቸዋል ፣ የህገ መንግስት ጥሰትም ተስተውሎባቸዋል ፣ እንዲሁም የብሮድካስት አዋጁን ጥሰዋል በተባሉት ላይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የግብረ መልስ ማስጠንቀቂያ እንደደረሰው ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።


የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የ”ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ ይኑረው እንጂ የሚሰራቸው ስራዎች መላው ኢትዮጵያውያንን መወከሉ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ተግባር ውስጥ ገብቷል የሚሉ ቅሬታዎች ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እንደተነሳበት ሰምተናል።


በተለይ እውቁ የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሀጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በሁዋላ በኢቢሲ የተላለፉ ፕሮግራሞች የማስጠንቂያ ግብረ መልስ ከባለስልጣኑ እንዲላክለት መነሻ እንደሆነ ከደብዳቤው ይዘት መረዳት ችለናል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ግድፈቶች ናቸው የተባሉ የተወሰኑ የፕሮግራም ይዘቶች የተላለፉበት ሰአት ጭምር ተዘርዝረው ከባለስልጣኑ በተላከለት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ውስጥ ተካቷል።

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየተጋበዙ ቃለ መጠይቅ የሚሰጡ “ምሁራን” ሲያነሷቸው የተደመጡ አስተያየቶችም ማስተካከያ እንዲረግባቸው በባልስጣኑ ደብዳቤ በማስጠንቀቂያነት ተገልጿል። 


 የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በመንግስት ለሚታዘዘው ኢቢሲ እንዲህ አይነት ማስተካከያን መጻፉ በራሱ እንደ መልካም ጅምር ይወሰድ እንጂ ባለስልጣኑ ከዚህ ቀደም በፌዴራል መንግስት በማይተዳደሩት ትግራይ ቲቪ እና የህወሀት ልሳን በሆነው ድምጸ ወያኔ ላይ ተመሳሳይ ደብዳቤ ስለተጻፈ አድሏዊ ተቋም ላለመባል ያደረገው ይሁን አይሁን ወደፊት በሚኖሩ ተግባሮቹ የሚወሰን ይሆናል። ሁለቱ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ የቴሌቭዥን ጣብያዎችን ከሳተላይት ወርደው የነበረው በባለስልጣኑ በቀጥታ እንዳልሆነም መገለጹ ይታወሳል። ሁለቱ ጣብያዎች ሳተላይት ላይ የወጡት ከኢቢሲ በውሰት በወሰዱት ፍሪኩዌንሲ ስለሆነ እርምጃው ላይ ሌላ የመንግስት አካልም አንደተሳተፈበት ዋዜማ ተረድታለች።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በተለያየ የህግ ጥሰት ውስጥ ላገኘሁዋቸው በርካታ መገናኛ ብዙሀንም የማስጠንቀቂያ ደብዳቤን ጽፌያለሁ ብሏል። ቻናሎችን የማዘጋት እንቅስቃሴዎችንም ሲያደርግ መቆየቱን ሰምተናል። ቢሆንም ትግራይ ቲቪና ድምጸ ወያኔን ከሳተላይ የማውረዱ ስራ ቢሰራም በሌላ መንገድ ተመልሰዋል።

አሁን እስር ቤት ባለው ጃዋር መሀመድ ይመራ የነበረው የኦሮሞ ሚድያ ኔትወርክ (OMN) ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ መገደል በሁዋላ በቀጥታ ስርጭት ህዝብን በህዝብ  ላይ የሚያነሳሱ መልእክቶችን አስተላልፏል በሚል የአዲስ አበባ ቢሮው እንዲዘጋና ሰራተኞቹም በቁጥጥር ስር ቢውሉም ጣብያው ከውጭ የሚያስተላልፈውን ስርጭት ግን ማስቆም አልተቻለም። ኦኤምኤን እስከ አሁን ስርጭቱን ሲያስተላልፍበት የነበረውን ፍሪኩዌንሲ ቀይሮ እየሰራ መሆኑንም በነባሩ ቻናል ላይ እያስተዋወቀ ነው።


የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ተገቢ ያልሆነ ስራ ሰርተዋል ያላቸውን ጣብያዎች በዘላቂነት ማገድ ያልቻለውም ለጣብያዎቹ ሳተላይት ላይ መግቢያ ፍሪኩዌንሲ የሚሰጧቸው የሌሎች ሀገራት ኩባንያዎች በመሆናቸው ነው። ለዚህም በየሀገራቱ እየሄዱ የሳተላይት አቅራቢ ኩባንያዎቹን ማግባባት ያስፈልጋል። ይህንን ለማሳካት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር እንቅስቃሴ እንደጀመረ ሰምተናል።

በተለይ ኦኤምኤን ያሰራጫቸውን ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ፕሮግራሞችም ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉመው ለሳተላይት አቅራቢ ኩባንያዎቹ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮች ሰምተናል። ይህ ሂደት ፈታኝ ቢሆንም ኩባንያዎቹን የማግባባቱ ስራ በመልካም ሁኔታ ከተከናወነ ውጤት እንደሚያመጣ መንግስት ዕምነት ጥሎበታል። [ዋዜማ ራዲዮ]