Tom Malinowski
Tom Malinowski
  • የኢትዮዽያ ባለስልጣናት በሪፖርቱ ላይ ከአሜሪካ ጋር ውይይት አድርገዋል
  • የኦሮሚያው የመብት ጥሰት በቂ ሽፋን አላገኘም የሚል ቅሬታ ቀርቦበታል
  • በኤርትራ የከፋ ደረጃ የደረሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፀማል

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በየዓመቱ የሚያወጣው “የሰብዓዊ መብት ሪፖርት” ረቡዕ ሚያዝያ 5 ቀን 2008 ዓ.ም ይፋ ተደርጓል፡፡ በየዓመቱ መውጣት ከጀመረ አርባኛ ዓመቱን የደፈነው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት በ199 ሀገራት ያሉ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን ይዳስሳል፡፡ በ40 ገጾች የተካተተው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግምገማ በቀደሙት ዓመታት እንደተለመደው ከግድያ እስከ ዘፈቀደ እስር ባሉ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ትርክቶች የተሞላ ነው፡፡

ምንጮች ለዋዜማ እንደተናገሩት በቅርቡ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በአዲስ አበባ ስብሰባ ተቀምጠው የነበሩት የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቶም ማሊኖዎስኪ ከተወያዩባቸው ጉዳዩች ውስጥ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቱ ይዘት አንዱ እንደነበር ነው።

የጎርጎርሳያውያንን አቆጣጠር ተመርኮዞ የተዘጋጀው ሪፖርት እ.ኤ.አ በ2015 የተከሰቱ ሁነቶችን ብቻ ያካተተ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መገባደጃ ላይ በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ እስካሁንም ድረስ ያላባራው ተቃውሞ በተብራራ ሁኔታ በሪፖርቱ እንዳይካተት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይሁንና ከሪፖርቱ ሰባት ዋና ዋና ክፍሎች በተወሰኑቱ ስለ ተቃውሞው እና ተያይዞ ስለተከሰቱት  የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እዚያም እዚያም ለመጠቃቀስ ተሞክሯል፡፡   

ስለተፈጸሙ ግድያዎች በሚያትተው የሪፖርቱ የመጀመሪያ ክፍል ላይ ህዳር 9 ቀን 2008 ዓ.ም በተማሪዎች አማካኝነት በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ ግጭት አምርቶ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት ከመጠን ያለፈ እርምጃ ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች እና የፖሊስ አባላት መገደላቸውን ይገልጻል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ያለ ህግ አግባብ እና በዘፈቀደ መታሰራቸውን ያስረዳል፡፡ ተቃውሞው እና ግጭቱ መቀጠሉንም ያስረዳል፡፡

በሪፖርቱ አጭር ማጠቃለያ ቅድሚያ የተሰጠው እና በሌሎችም ክፍሎች ሰፊ ሽፋን የተሰጠው የግንቦት 2007 ምርጫ ከግድያ ጋርም ተያይዞ ተነስቷል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ዋቢ የሚያደርገው ሪፖርቱ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ይገልጻል፡፡ በምርጫው ገዢው ፓርቲ እና አጋሮቹ 547ቱን የፓርላማ መቀመጫዎችን ሙሉ ለሙሉ ማሸነፋቸውን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ መንግስት በወሰዳቸው እቀባዎች የድምጽ አሰጣጡን በነጻነት የመታዘብ እንቅስቃሴ ክፉኛ ገድቦታል ይላል፡፡

ከምርጫው በፊት የነበረው ሁኔታ ነጻ እና ገለልተኛ ምርጫ ለማካሄድ የሚያመች እንዳልነበር የሚያስረዳው ሪፖርቱ መንግስት የተቃዋሚ ዕጩዎች እና ደጋፊዎችን ማስፈራራትን ጨምሮ ሌሎችንም ኢ-ፍትሃዊ ታክቲኮች ይጠቀም እንደነበር ያብራራል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የሲቪል ባለስልጣናት በጸጥታ ኃይሎች ላይ ቁጥጥር ያላቸው ቢሆንም በገጠር ያሉ ፖሊሶች፣ የአካባቢ ሚሊሽያዎች እና የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ አንዳንድ ጊዜ በገዛ ፍቃዳቸው እንደሚንቀሳቀሱ ይገልጻል፡፡

“የጸጥታ ኃይሎች ተግባራቸውን የሚያከናውኑ ቢሆኑም አጥፊዎች ለህግ ያለመቅረባቸው ሁኔታ ስር የሰደደ ችግር ነው፡፡ በፌደራል ፖሊስ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ለመመርመር ተግባር ላይ የዋሉ ዘዴዎች ምንነት አይታወቅም” ይላል ሪፖርቱ፡፡ “በአካባቢ የጸጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ እንደ የዘፈቀደ እስር እና በዜጎች ላይ የሚደርሱ ድብደባዎች ዓይነት የመብት ጥሰቶች ላይ የሚደረጉ ምርመራዎችን ውጤት መንግስት በይፋ ሲገልጽ እምብዛም አይስተዋልም፡፡”     

ሪፖርቱ በጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱ እርምጃዎችን በቁጥር አስደግፎ አስቀምጧል፡፡ ከምርጫው ጥቂት ቀናት በኋላ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በሀመር ወረዳ ነዋሪዎች እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት 48 ሰዎች መሞታቸውን ያስረዳል፡፡ በሰኔ ወር መጀመሪያ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ጭልጋ ወረዳ የምርጫውን ውጤት በመቃወም በወጡ የቅማንት ተወላጆች ላይ የጸጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውንም ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡     

እንደ ሪፖርቱ ገለጻ ከግድያ በመለስ በሀገሪቱ ከፍተኛ ከሆኑ የሰብዓዊ መብት ችግሮች መካከል በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች እንደዚሁም ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ማዋከብ እና ማስፈራራት ይገኝበታል፡፡ የጸጥታ ኃይሎች በእስረኞች ላይ ይፈጽሟቸዋል የሚባሉ ማሰቃየት፣ ድብደባ፣ ማዋከብ  እና ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ እንደዚሁም ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ክሶች ከከፍተኛ ችግሮች መካከል ተመድበዋል፡፡ በማረሚያ ቤቶች እና በእስረኛ ማቆያ ቤቶች የሚታየው ሁኔታ እጅግ የከፋ እና አንዳንዴም ለህይወት አስጊ እንደሆነ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

የሪፖርቱ አዘጋጆች ሌሎች የሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ችግሮች ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ካላቸው የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች አንጻር በመተንተን ፈትሸዋል፡፡ ችግሮቹን የሰው ልጅን ክብር መጠበቅ፣ የሲቪል መብቶች እና ነጻነቶች ከበሬታ፣ የፖለቲካ መብት አከባበር እንደዚሁም ሙስና እና በመንግሥት ውስጥ የግልጽነት አለመኖር በሚሉ ዋና ክፍሎች ስር ዘርዝረዋቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት የሚካሄድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራን በተመለከተ የመንግሥት አመለካከት፣   አድልዎ፣ ማኅበራዊ ጥቃት እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እንደዚሁም የሠራተኛ መብቶች በሚሉ ሌሎቹ የሪፖርቱ ዋና ክፍሎችም ያሉትን ችግሮች ዳስሰዋል፡፡

“በዚህ ሪፖርት ላይ ተዘርዝረው የሚታዩት ተደጋጋሚ መጥፎ ምሳሌዎች መሰረታዊ ነጻነቶችን ለማስረጽ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ለማገዝ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመዝገብ እና ተጠያቂነትን ለማሳደግ የሳለፍነውን ውሳኔ ይበልጥ የሚያጠናክር ነው” ይላሉ የዓመታዊው ሪፖርት ባለቤት የሆነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትን የሚመሩት ጆን ኬሪ፡፡ “በየትኛውም ሀገር ያሉ ህዝቦች ነጻ መሆን እና ህይወታቸውን እንዳሻቸው መምራት ይፈልጋሉ፡፡ መሰረታዊ መብቶቻቸውን እና ክብራቸውን ከተነፈጉ ግን ከሶሪያ እስከ ስሪላንካ፣ ከበርማ እስከ ናይጄሪያ እንዳየነው ለሚፈልጉት ነገር ከመቆም ወደ ኋላ አይሉም፡፡”    

“አንዳንድ መንግስታት በነጻነት እና መረጋጋት መካከል የሚያቀርቡት ምርጫ የሀሰት ነው፡፡ ነጻነት ለዘላቂ መረጋጋት መሰረቱ ነውና” ይላሉ ሴክረተሪ ኬሪ ከሪፖርቱ ጋር በተያያዘው የመቅድም መልዕክታቸው፡፡

ሴክረተሪ ኬሪ የኢትዮጵያን ጨምሮ ሪፖርቱ የዳሰሳቸው ሀገራትን የሰብዓዊ መብት ሰነድ ለኮንግረስ የማስገባት ግዴታ በህግ ተጥሎባቸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከአሜሪካ እርዳታ በሚቀበሉ እና በተባበሩት መንግስታት አባል ሀገራት ላይ የሚያዘጋጀውን ዓመታዊ ሪፖርት ለኮንግረስ እንዲያስረክብ የሚያስገድዱት የውጭ እርዳታ እና የንግድ ህጎች የጸደቁት እ.ኤ.አ በ1961 እና በ1974 ነው፡፡

ከሁለተኛው ህግ መጽደቅ ሁለት ዓመት በኋላ ኮንግረስ ያወጣው ሌላ ህግ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሰብዓዊ መብት አስተባባሪ እንዲኖር ደንግጎ ነበር፡፡ በስተኋላ ላይ የአስተባባሪው ስልጣን ወደ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ደረጃ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ይኸው ህግ አሜሪካ በውጭ እና የንግድ ፖሊሲዎቿ መሰረት ከሀገራት ጋር የምታደርገው ግንኙነት የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን እና የሠራተኛ መብቶችን ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ዓመታዊው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ደግሞ ለግምገማው ሁነኛ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገልግል ከአሜሪካ መንግስት የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በኦሮሚያ የተከሰተውን አመፅ ተከትሎ የተፈፀመው የመብት ጥሰትና ግድያ በሪፖርቱ በቂ ትኩረት አላገኘም የሚል  ከኦሮሞ የመብት ተሟጋቾች ትችት ቀርቦበታል። ሪፖርቱ የፈረንጆቹን 2015 ዓ.ም ብቻ የሸፈነ በመሆኑ ያለፉት አራት  ወራትን ዝርዝር በዚህ ሪፖርቱ አላካተተም።

“እነዚህ [ዓመታዊ] ሪፖርቶች ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ፣ ዲፕሎማሲን ለማካሄድ፣ እርዳታ እና ስልጠና ለመስጠት እና ከመንግስት ጋር የተያያዙ ማናቸውንም አቅርቦቶች ለመመደብ በምንጭነት ይጠቅማሉ” ይላል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኦፊሴሊያዊ ድረ ገጽ፡፡ “ሪፖርቶቹ የአሜሪካ መንግስት ከቡድኖች ጋር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው የሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ ለሚያደርገው ትብብር እንደ መሰረት ሆነው ያገልግላሉ፡፡”

Eritrea President Isaias Afeworki
Eritrea President Isaias Afeworki

ኤርትራ

ይህንን የተረዳ የሚመስለው ኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱን ሪፖርት ላይ ላዩን የሚያጣጥለው ቢመስልም የሚሰነዘርበት ትችት እንደሚቆጠቁጠው በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳይቷል፡፡በሚቆጣጠራቸው እና መንግስት ዘመም በሆኑ ብዙሃን መገናኛዎች አማካኝነት የማስተባበያ አንዳንዴም ነቀፌታ ያዘለ የመልስ ምት በተደጋጋሚ ሲሰጥ ተስተውሏል፡፡ ሲለው ደግሞ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” የሚለውን ብሂል የተከተለ ይመስል በራሱ ሀገር ላይ የቀረበውን እያጣጣለ በኤርትራ ላይ የወጣውን ሪፖርት “እዩልኝ፣ ስሙልኝ” እያለ ያስተጋባል፡፡  

ኤርትራን አስመልክቶ በ2015ቱ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት የቀረበው መረጃ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በጥሰቶች የተሞላ ነው፡፡ ባለ 26 ገጹ የኤርትራ ሪፖርት አገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ማንኛውም ዓይነት ድርጊቶች ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ዘንድ ለመድረስ ሩቅ መሆናቸውን ማመልከቻ ነው፡፡ በአመዛኙ የዛሬ ዓመት እና ከዚያም በፊት የወጡ ሪፖርቶች በድጋሚ በዘንድሮው ሪፖርት ተካትተዋል፡፡

 ለየትኛውም መንግስታዊ ላልሆነ ወገን ዝግ በሆነችው ኤርትራ መረጃ ለማግኘት እንደ ተባበሩት መንግስታት አጣሪ ኮሚሽን ያሉ ውስን ድርጅቶች ላይ ሙጥኝ ማለት ግድ ይላል፡፡ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቱም አጣሪ ኮሚሽኑን ዋቢ አድርጎ ኤርትራ በዜጎቿ ላይ የነጻ እርምጃ (shoot-to-kill) አሁንም እንደምታካሄድ ይገልጻል፡፡ ከ22 ዓመታት በፊት ሉዓላዊነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮ በአምባገንን ስርዓት ውስጥ በፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ቁጥጥር ስር መሆኗን ያስታውሳል፡፡ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ዜጎቿ በመንግስት ኃይሎች በዘፈቀደ የሚገደሉባት፣ ክስ ሳይመሰረትባቸው የሚታሰሩባት፣ የሚሰቃዩባት፣ የሚደበደቡባት እና የሚዋከቡባት እንደሆነች መቀጠሏንም ያስረዳል፡፡