Tsedenya GebreMarkos
Tsedenya GebreMarkos

(ዋዜማ)- ይህ ዓመት ለጸደኒያ ገብረማርቆስ ስኬታማ ነበር፡፡ በሶስት የተለያዩ ውድድሮች በሽልማት ስትንበሸበሽ ዓመቱ ገና እንኳ አልተጋመሰም፡፡ አሁን ደግሞ አዲሱን አልበሟን ለሙዚቃ አፍቃሪያን ለማድረስ ተፍ ተፍ እያለች ነው፡፡ “የፍቅር ግርማ” የሚል ስያሜ ያለው አልበሟ ለፋሲካ ይወጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ አልበሞች ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ነው፡፡

የጸደኒያ አዲስ አልበም 11 ዘፈኖችን ያካተተ ሲሆን በእንግሊዘኛ ከተዜመው አንድ ዘፈን በስተቀር ሙሉ ለሙሉ በአማርኛ ቋንቋ የቀረበ ነው፡፡ ከዘፈኖቹ ውስጥ የዘጠኝ ያህሉን ዜማ ራሷ ጸደኒያ የደረሰችው ሲሆን በሁለቱ ላይ ደግሞ ተሳትፎ አድርጋለች፡፡

ከእንግሊዘኛው ዘፈን በስተቀር ሁሉንም ዘፈኖች ያቀናበረው “ህመሜ” የተሰኘውን ተወዳጅ ነጠላ ዜማዋን ያቀናበረው አቤል ጳውሎስ ነው። ጥቁር አሜሪካዊው ኬ አለን የእንግሊዘኛውን ድርሻ ወስዷል።

የአብዛኞቹ ዘፈኖች ግጥም ደራሲ አንጋፋው ይልማ ገብረአብ ሲሆን ለሙዚቃ ስራ አዲስ የሆነው ፋሲል ከበደ ሶስት ግጥሞችን አዋጥቷል፡፡ ጸሀፌ ተውኔት እና ገጣሚ ጌትነት እንየው አንድ ስራ አበርክቷል፡፡

ጸደኒያ ለውድድር የላከቻቸውን ዘፈኖች በአልበሟ ቦታ ሰጥታቸዋለች፡፡ በ2007 ዓ.ም አህጉር አቀፍ ለሆነው “አፍሪማ የሙዚቃ ውድድር የተሳተፈችበት እና በ”Best African Contemporary” ዘርፍ ያሳጫት “የፍቅር ግርማ” የተሰኘው ዘፈን እንዲያውም የአልበሟ መጠሪያ የመሆን ዕድል አግኝቷል፡፡

በ2008 ዓ.ም በተካሄዱት የ“አፍሪማ”፣ የ“ለዛ” የአድማጮች ምርጫ እና የ“ጉማ” የፊልም አዋርድ ሽልማቶችን የሰበሰበቸበት “የት ብዬ” የተሰኘው ዘፈን ሌላው ተመራጭ ዘፈን ሆኗል፡፡ በገጣሚ ዮሃንስ ሞላ የተጻፈው “የት ብዬ” ግሩም ዘነበ እና መሰረት መብራቴ ለተወኑበት “ሃርየት” ለተሰኘው ፊልም ማጀቢያነት የተዘፈነ ነበር፡፡

ጸደኒያ ከዘፈኖቿ ጭብጥ ባሻገር አልበሟ በአንድ ነገር ላይ እንዲያተኩር የምትፈልግ አትመስልም፡፡ አልበሟ ከሬጌ እስከ ብሉዝ፣ ከጃዝ እስከ ችክችካ ባሉ ዘፈኖች የተሞላ ነው፡፡ ከክራር እስከ ሊድ እና ቤዝ ጊታር፣ ከፒያኖ እስከ ማሲንቆ እና ዋሽንት የሙዚቃ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

Tsedenya GebreMarkos
Tsedenya GebreMarkos

“የሁሉም ነገር ድብልቅ ነው” ትላለች ጸደኒያ ስለ አልበሟ አወቃቀር ለዋዜማ ስትናገር፡፡ “ብዙ ኤሌክትሮኒክ አይደለም። አኩስቲክ መሳሪያዎች በብዛት ተጠቅሜያለሁ። ኦርጋኒክ ነው ማለት ያቻላል።”

በተቃራኒው የዘፈን ጭብጦቿ በአንድ ነገር ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ ሚካ እና ኖዋ ለተሰኙት የአምስት ዓመት መንትያ ልጆቿ የዘፈነችው ዘፈን እንኳ በዋና ጭብጧ ማዕቀፍ ውስጥ የሚወድቅ ነው፡፡

“እኔ ሁሌም ፍቅር ላይ ነው የማተኩረው” ትላለች ጸደኒያ የጭብጥ ምርጫዋን ስታስረዳ፡፡ “ለመንታ ልጆቼ የዘፈንኩት ዘፈን በፍቅር ውስጥ የሚጠቃለል ነው— በእናትነት ፍቅር፡፡”

ከዓመት በፊት የተቋረጠውና በሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ይቀርብ የነበረው የሬድዮ ፕሮግራሟ እንኳ ስለ ፍቅር የሚወራበት እንደነበር የሚያስታውሱ በጸደኒያ ዋና ጭብጥ እምብዛም ላይደነቁ ይችላሉ። የምትዘፍናቸውን ዘፈኖች የግጥም ሀሳብ በመስጠት ማሰራቷ አልበሟ በምትፈልገው ጉዳይ እንዲሽከረከር አድርጎታል።

“ቢሰጠኝ” የተሰኘው አልበሟ ከወጣ 12 ዓመት በኋላ በአዲስ ስራ የመጣቸው ጸደኒያ የአሁኑ አልበሟ በዕድሜ ከፍ ብላ የሰራችው በመሆኑ “መብሰል” ይታይበታል ትላለች። የራሷን ዜማዎች መስራቷ እና በቅንብር እና ግጥም ስራ መሳተፏ አዲሱን አልበሟን ከድሮው የሚለየው እንደሆነ ታብራራለች።