Abreham Belay- Tigray Provisional Administration Head – FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ከቀናት በፊት በመንግስት ድጋፍ ከትግራይ ክልል በየብስ ትራንስፖርት ተጓጉዘው አዲስ አበባ የደረሱት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸውን ለመወሰን ከፌደራሉ መንግስት ምላሽ እየተጠባበቁ ነው።


ባልታሰበና ሚስጥራዊነት ጭምር በነበረው ዝግጅት ከትግራይ ክልል የወጡት የጊዜያዊ አስተዳደር መሪዎች አሁን በአዲስ አበባ በሁለት ቦታዎች በተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ ማረፊያ እንደሚገኙ ዋዜማ አረጋግጣለች።

ቀደም ባሉት ወራት ከጊዜያዊ አስተደደሩ መሪዎች መካከል አንዳንዶች የመንግስትንና የመከላከያን ምስጢሮች ለአማፂው ሕወሓት ያቀብላሉ በሚል በአመራሮቹ መካከል ውጥረት ስፍኖ መሰንበቱ ይታወቃል። ሙስናና ብልሹ አሰራር ስፍኗል በሚልም አመራሩን እስከመበወዝ የደረሰ እርምጃ ተወስዶ ነበር።


ወትሮም እንደነገሩ የሆኑት አመራሮቹ አሁን የቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የአንዳንድ ትግራይ የቀሩ የበታች አመራሮች ደህንነት እንደሚያሰጋቸው እየተናገሩ ነው። በቀጣዮቹ ቀናት ከጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተው ለመነጋገር ውሳኔ እየጠበቁ መሆኑን አመራሮቹ ለዋዜማ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተቋቋመው የሀገር መከላከያ ሰራዊት መቀሌን ከተቆጣጠረና የሕወሓት አመራር ወደ በረሀ ከሸሸ በኋላ ነበር። [ዋዜማ ራዲዮ]