PHOTO Credit AFP

ዋዜማ ራዲዮ- ከሁለት አመት በፊት 10ኛ የፌደራል ክልል ሆኖ በሕዝበ ውሳኔ የተቋቋመው የሲዳማ ብሄራዊ ክልል በያዝነው 2014  ዓመት የዞን የአስተዳደር መዋቅር መዘርጋት እንደማይችል አስታወቀ።

ዞን ማዋቀር ከወጪ ጋር የሚያያዝና የራሱን በጀት የሚፈልግ በመሆኑ፣ የሚመደቡ አመራሮች ፣ ባለሙያ፣ ተሽከረካሪዎች እና ሎሎች ውጪዎችን በመቀነስ ፣ ቅድሚያ በጣም ወሳኝ ለሆኑ ለህዝብ አገልግሎት የሚውሉ የልማት ስራዎችን መስራት እንደመረጠ ክልሉ ይናገራል። የሲዳማ ክልል ባለፈው ዓመትም የዞን አደረጃጀቱን ይዘረጋል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

የዞን አስተዳደር ማዋቀር እንዲዘገይ ቢደረግም በሂደት የዞን መዋቅር የሚዘረጋበት አካሄድ ላይ ውይይት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ የኮምዩኒኬሽን ፅ/ቤት/ሃላፊ አቶ ፊልጶስ ናሆም ለዋዜማ ተናግረዋል ።

በሲዳማ ክልላዊ መንግስት  ህገ መንግስት እንደተቀመጠው፣ ክልሉ  በፈለገው ጊዜ የዞን እና የወረዳ መዋቅሮች እንደሚያቋቁም ደንግጓል። በዚህም መሰረት በሲዳማ ከአምስት ያልበለጠ  ዞን ሊዋቀር እንደሚችል መቀመጡን አቶ ፊሊጶስ  ነግረውናል።

በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፌደራሊዝም መምህር ሰለሞን ንጉሴ (ዶ/ር) እንደሚሉት ከሆነ ሲዳማ የዞን መወቅሮችን ለመትከል መዘግየቱና እንደ መንገድ፣ ጤና ኬላ እና ትምህርት ቤት ያሉ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ቅድሚያ መስጠቱ  መልካም ነው።  ምናልባትም  ለሌሎች ክልሎች በአርአያነት የሚወሰድ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

እንደ አቶ ፊልጶስ ከሆነ ሲዳማ ራሱን የቻለ ክልል ሲሆን “ኑሯችን ይለወጣል” የሚጠብቁ የክልሉ ተወላጆች መኖራቸውንና ቅድሚያ የሚሰጠውም የክልሉን መስረታዊ የልማት ችግሮች ማቃለል መሆኑን አስረድተዋል።

ለአብነትም  በ2013 ዓ.ም በመንግስት ብቻ  1.5 ቢሊየን ብር  ካፒታል በጀት ተይዞ መንገድ፣ ጤና ኬላዎች፣ የንፁህ ውሃ አቅርቦት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

የፀጥታ ሁኔታን በተመለከት  ክልሉ 1,100 የደቡብ ብሄር ብሄረሰብ ክልል ውስጥ የነበሩ የሲዳማ ክልል ተወላጆችን ጨምሮ ዘንድሮ ደግሞ  1,000 የሚደርሱ አዲስ የልዩ ኋይል አባላትን ማስመረቁን ፣ ነባር  ፖሊስን ሳይጨምር  በድምሩ 2,100 የሚደርሱ አባላት እንዳሉት ነግረውናል።  [ዋዜማ ራዲዮ]