Daniel Bekele (PhD) head of EHRC-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በየአመቱ ሚያዚያ 23 ቀን የሚከበረውን ዓለማቀፍ የላብ አደሮች ቀን አስመልከቶ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የሰራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ ተመን ክፍያ ወለል የሚወስነውን ቦርድ በአስቸኳይ እንዲቋቋም ጠየቀ፡፡

ኮሚሽኑ ቅዳሜ ሚያዚያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም አመሻሹ ላይ ባወጣው መግለጫ በ2012 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክርቤተ ጽድቆ ወደ ስራ የገባው የዝቅተኛ ደመወዝ ተመን፣ እንዲሁም የሰራተኛ ማህበራት መቋቋምን የሚመለከቱ ህግጋት የተካተተበትን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ እንደመልካም ጅምር እንደሚወስደው በመግለጽ በቀጣይ በአዋጁ መሰረት እንዲቋቋም የሚፈቅደውን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ በአስቸኳይ እንዲቋቋም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ጸድቆ ወደ ስራ የገባው የአሰሪና ሰራተኞች አዋጅ ቦርድ ጉዳዩን በሚከታተለው ሚንስትር  ወይም አግባብ ባለው ባለስልጣን የሚሰየሙ አንድ ሰብሳቢ፤ ስለአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ብቃትና ልምድ ያላቸው ሁለት ባለሙያዎች፣ ከአሠሪ ማኅበራት የሚወከሉ ሁለት አባላት፤ ከሠራተኞች ማኅበራት የሚወከሉ ሁለት አባላት እና ከአሠሪዎችና ከሠራተኞች ማኅበራት የሚወከሉ አንድ አንድ ተተኪ አባላት የሚኖሩት የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ እንደሚቋቋም ደንግጓል፡፡

አዋጁ ለሚቋቋመው ቦርድ በስራ ላይ የሚነሱ የሥራ ክርክሮችን ማየት፣ ተከራካሪዎችን የማስታረቅ፣ ትዕዛዝና ውሣኔ የመስጠት፤በማናቸውም የሥራ ቦታ ወይም ድርጅት በሥራ ጊዜ በመግባት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን የመሰብሰብና ምስክሮችን የመስማት ወይም ሠነዶች እንዲቀርቡ የማድረግ ወይም በድርጅቱ ውስጥ በማናቸውም ሰው ይዞታ ስር የሚገኙ ሌሎች ዕቃዎችን የመመልከትና በርካታ ሃላፊነቶችን ይሰጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በ2012 ዓ.ም ለበርካታ ወራት ካካሄደው የክትትል ስራ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ትላልቅ ኢንዳስተሪያል ፓርኮች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች የሚከፈላቸው የክፍያ መጠን መሰረታዊ የኑሮ ደረጃን ለማሟላት በቂ አለመሆኑን እንዳረጋገጠ ገልጿል፡፡

የተለያዩ ጥናቶች መካዳሄቸውን በመጥቀስ በኢትዮጵያ ካሉ ተቀጣሪዎች ውስጥ ቢያንስ ግማሽ የሚሆኑት በድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ በክትትል ስራው የተገኘው ግኝት እንደሚያመላክት ያሳየው የኮሚሽኑ መግላጫ ከዚህ ውስጥ 18 በመቶ የሚሆኑት የከፋ ድህነት ውስጥ እና 31 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ መካከለኛ ደረጃ በሚባል ድህነት ውስጥ  እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

ላለፉት ሶስት አመታት የቀጠለውና ዘንድሮም የታየው ዋጋ ግሽበት 35 በመቶ መድረሱን በመግለጽ ይህ እየተባባሰ ከመጣው የዋጋ ንረት፣ በአለማቀፍ ደረጃ  ከታየው የሸቀጦች የዋጋ መናር፣ የጸጥታ ችግር፣ ድርቅና ፍልስት ጋር ተደማምሮ የምግብ ነክ ሸቀጣቀጦች ዋጋ እንዳሻቀበ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ  ለሰራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ አለመደረጉ ሁኔታውን እንዳባባሰው  ኮሚሽኑ በመግጫው አትቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የኢትዮጵያ ሰራኞች ማህበርና የሌሎች ማህበራት የዝቅተኛ ደመወዝ  ወለል እንዲወሰን የሚያነሱትን ሃሳብ እንደሚደግፍ በመግለጽ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን መወሰን ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖሩ ሰራተኞች ሁሉንም ችግራቸውን ባይፈታም የተስተካከለ የኑሮ ደረጃን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ከሆኑ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ጋር ተዳምሮ የሚወሰደው እርምጃ ወሳኝ እንደሚሆን ዋና ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ በመግለጫው አመላክተዋል፡፡

በየአመቱ የሚከበረው የሰራኞች ቀን  በ2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለ47 ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]