Redwan Hussien and Getachew Reda ,signing ceremony in Pretoria, South Africa

ዋዜማ – መንግስት እና ህወሓት በዛሬው ዕለት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። ዋዜማ ከመንግሥት ምንጮች እንዳሰባሰበችው ከሆነ ስምምነቱ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናሉ የተባሉ ጉዳዮችን አካቷል። 

በደቡብ አፍሪቃ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት የመንግስትና የሕወሓት የጦር አዛዦች በተኩስ አቁም አፈፃፀም፣ በጦር ስራዊት አሰፋፈር እንዲሁም በትጥቅ መፍታት ጉዳይ ላይ እስከ ነገ እንደሚነጋሩ ይጠበቃል።

የሁለቱ ወገኖች የስምምነት አፈፃፀም የጊዜ ስሌዳና ሌሎች ጉዳዮችን እንደሚከተለው ተመልክተናል።

በከፍተኛ ውጥረትና ክርክር የተካሄደው ውይይት መቋጫ “ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን ከማቆም ውጭ አማራጭ እንደሌላቸው እንደተገነዘቡ የታየበት መደምደሚያ” ነው ተብሏል።

ቁልፍ የስምምነት አጀንዳዎች፦

1. ህወሓት ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ለመፍታት መስማማቱን፦ በስምምነቱ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ በሰላሳ ቀናት ውስጥ ቡድኑ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንደሚፈታ፤ ይህንን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ የሁለቱ ወገን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በ24 ሰዓት ውስጥ አመቺ ቦታ መርጠው ንግግር ያደርጋሉ፤

2. ስምምነቱ በተፈረመ አምስት ቀናት ውስጥ የሁለቱ ወገን ወታደራዊ አመራሮች የትጥቅ ማስፈታት ሂደቱ የሚመራበትን ዝርዝር አፈጻጻም በጋራ በማውጣት ተግባራዊ ሥራዎችን መሥራት ይጀምራሉ፤

3. የሁለቱ ወገን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በተገናኙ አስር ቀናት ውስጥ ህወሓት ያሉትን ሁሉንም የቡድን እና ከባድ መሣሪያዎች ለመከላከያ ሠራዊት ያስረክባል፤

4. ስምምነቱ በተፈረመ ሰባት ቀናት ውስጥ የፌደራል መንግሥት መቀሌን ተረክቦ በከተማው ውስጥ እና ዙሪያ ሁሉንም አይነት የጦር መሣሪያ ያስፈታል፤

5. በአጭር ቀናት ውስጥ አሁን ያለው የህወሓት መዋቅር ፈርሶ የፌደራል መንግሥት የሚመራው የጊዜያዊ አስተዳደር ይቋቋማል። በሚዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥም የትግራይን ሕዝብ የሚወክል አካል ይሳተፋል፤

6. የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከጎረቤት ሀገራት የሚያዋስኑ የድንበር አካባቢዎችን ደኅንነትና ሰላም የሚያረጋግጥ ስምሪት የሚያደርግ ይሆናል። መከላከያ ሠራዊቱ በማንኛውም የትግራይ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ሕግ የማስከበር ስልጣኑን ከህወሓት ሙሉ በሙሉ ይቀበላል። ህወሓት ለተግበራዊነቱ ምንም አይነት እንቅፋት እንደማይፈጥር ተስማምቷል።

7. የሚመሰረተው ጊዜያዊ አስተዳደር በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች የማኅበራዊ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀመሩ ሁኔታዎች ያመቻቻል፤ ተግባራዊነታቸውን ያረጋግጣል።

8. ህወሓት ያለ ፌደራል መንግሥት እውቅና ከማንኛውም የውጭ አካል ጋር ግንኙነት ማድረግ ያቆማል። እንዲህ አይነት ተግባር የሚፈጹ ግለሰቦች ካሉ በሀገሪቱ ሕግ የሚጠየቁ ይሆናል። 

7. የሚመሰረተው ጊዜያዊ አስተዳደር በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች የማኅበራዊ አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀመሩ ሁኔታዎች ያመቻቻል፤ ተግባራዊነታቸውን ያረጋግጣል።

8. ህወሓት ያለ ፌደራል መንግሥት እውቅና ከማንኛውም የውጭ አካል ጋር ግንኙነት ማድረግ ያቆማል። እንዲህ አይነት ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦች ካሉ በሀገሪቱ ሕግ የሚጠየቁ ይሆናል። [ዋዜማ]