Getachew Reda, Representative of TPLF, (Photo by Phill MAGAKOE / AFP)

ዋዜማ- የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሃት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓም ደቡብ አፍሪካ ላይ የደረሱበትን የሰላም ስምምነት አስመልክተው ዝርዝር የጋራ መግለጫ አውጥተዋል። በጋራ መግለጫው ከተካተቱ ዋና ዋና የስምምነቱ ክፍሎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፤

  • የጦር መሳሪያ ተኩስ ድምፅ እና ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም፣
  • የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና ሕገ መንግሥቱን ለማክበር ቁርጠኝነትን ማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያ አንድ መከላከያ ሠራዊት ብቻ እንዳላት እውቅና መስጠት፣
  • መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የሕወሃት ታጣቂዎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና ተመልሰው እንዲዋሃዱ ወይም እንዲቀላቀሉ ማድረግ የሚያስችል ዝርዝር መርሃ ግብር ላይ መስማማት፣
  • የትግራይን ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ቀድሞ ወደነበረበት መመለስን፣ የፖለቲካ ልዩነቶች የሚፈቱበትን ማዕቀፍና ተጠያያቂነትና እርቅ የሚያሰፍን የሽግግር የፍትህ ፖሊሲን ያካተቱ የሽግግር ርምጃዎችን መውሰድ፣
  • የኢትዮጵያ መንግሥት ከረድዔት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለሁሉም ዕርዳታ ፈላጊዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚደርስበትን ሁኔታ እንዲያፋጥን፣ 
  • ሁሉንም የስምምነቱ ክፍሎች በቶሎ ተግባራዊ ለማድረግ፣ ሁሉንም ግጭቶች እና የጥላቻ ንግግሮች ለማቆም፣ የስምምነቱን ተግባራዊነት የሚያጠናክሩ መግለጫዎችን ብቻ ለመስጠት፣
  • መንግሥት መሠረታዊ አገልግሎቶች ለመመለስ እና በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸው ማኅበረሰቦችን መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት ጥረት ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል

ከጋዜጣዊ መግለጫው ተከትሎ የተሰራጨው የስምምነት ሰነድ ደግሞ ተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል። ይህ ስነድ የጋዜጣዊ መግለጫውን ፍሬ ሃሳቦች የሚያብራራና በማዕቀፍ የዘረዘረ ነው። 

ተኩስ አቁም በሚለው ርዕስ ስር

  • አስቸኳይ እና ዘላቂ የተኩስ አቁም ለማድረግ ለማወጅ፣ ሁለቱ ወገኖች ኃይሎቻቸው ከትንኮሳና ከግጭት እንዲታቀቡ ለማድረግ፣
  • ግልጽ እና ስውር የግጭት ድርጊቶችን ማቆም፣ አንዳቸው ለሌላኛቸው ባላንጣ ከሆነ የውጭ ኃይሎች ጋር ትብብር ማቄም፣ ማናቸውንም ፕሮፓጋንዳ እና የጥላቻ ንግግሮች ለማቆም፣
  • የትግራይን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ወደነበረበት መመለስ እና ፖለቲካዊ ንግግሮችን ለመቀጠል፣
  • መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እና የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የፌደራል መንግሥት በመቀሌ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን እንዳለው ለማወቅና መከላከያ ሠራዊት በሰላማዊ እና በተቀናጀ መንገድ መቀሌ እንዲገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ትጥቅ መፍታት፣ ታጣቂ መበተን እና መልሶ ማዋሃድ በሚለው ርዕስ ስር– 

  • ኢትዮጵያ አንድ መከላከያ ሠራዊት ብቻ እንዳላት መቀበል፣ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት የሕወሃት ታጣቂዎች ትጥቅ የሚፈቱበት፣ የሚበተኑበት እና መልሰው የሚዋሃዱበትን መርሃ ግብር ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ ሁለቱ ወገኖች ተስማምተዋል።

የመተማመኛ ርምጃዎች በሚለው ርዕስ ስር- 

  • ሕወሃት ፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል በሚገኙ የፌደራል ተቋማትና የአገሪቱን ዓለማቀፍ ድንበር ለመቆጣጠር ሥልጣኑ እውቅና ለመስጠት፣
  • ሕወሃት በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ከሌላ ጸረ-ሰላም ታጣቂ ቡድን ጋር መተባበር ወይም አብሮ መስራትን ለማቆም፣
  • ሕወሃት የታጣቂ ምልመላ፣ ሥልጠናና ስምሪት ለማቆም ሕገመንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት ከመሞከር ለመቆጠብ ተስማምቷል።
  • ፌደራል መንግሥቱ ደሞ በሕወሃት ተዋጊዎች ላይ ጥቃቱን ለማቆም፣
  • ፌደራል መንግሥቱ ሕወሃትን ከአሸባሪነት መዝገብ ለመፋቅ. ተስማምቷል። [ዋዜማ]