ዋዜማ ራዲዮ- የሕዳሴውን ግድብ ውሀ ለመሙላት ተይዞ የነበረውን ዕቅድ ኢትዮጵያ ለማዘግየት ተስማምታለች በሚል ከግብፅ ፕሬዝዳንት ፅሕፈት ቤት የተሰጠው መግለጫ መሰረተ ቢስና በሶስቱ ሀገራት የተደረሰበትን ስምምነት የሚፃረር መሆኑን የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባለስልጣናት ለዋዜማ አረጋግጠዋል።

በአፍሪቃ ህብረት አደራዳሪነት በተደረገው ውይይት ላይ ሀገራቱ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ድርድራቸውን ለመቀጠል የተሰማሙ ሲሆን ከማናቸውም አደናቃፊ መግለጫዎች ለመታቀብ ተስማምተው ነበር።

ይሁንና የግብፅና የሱዳን መንግስታት ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት የያዘችውን እቅድ ለማዘግየት ተስማምታለች በሚል ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ በመስጠት የፕሮፓጋንዳ ትርፍ ለማግኘት ሙከራ ማድረጋቸውን ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ሁለት የውጪ ጉዳይ ከፍተኛ ባላስልጣናት አረገግጠዋል።


የአፍሪቃ ህብረት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የግድቡን ሙሌት በተመለከተ ውይይት ስለመደረጉ ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠም።


ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የዲፕሎማቲክ ምንጮች እንደነገሩን ግብፅ በመንግስታቱ ድርጅት በኩል በአጋሮቿ ድጋፍ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ያደረገችው ሙከራ ባለፉት ቀናት ዉጤት ባለማምጣቱና ወደ አፍሪቃ ህብረት ሸምጋይነት እንዲሸጋገር በመወሰኑ የደረሰባትን የዲፕሎማሲ ኪሳራ ለማካካስ የተጠቀመችው የፕሮፓጋንዳ ስልት መሆኑን ያምናሉ።


የአፍሪቃ ሕብረቱ ድርድር ግብፅ በሙሉ ልብ የምትገባበት ባለመሆኑና በአጭር ቀናት ከስምምነት እንዲደረሰ ታስቦ የሚካሄድ ስለሆነ ውጤታማ ይሆናል የሚል ግምት እንደሌላቸው ከኢትዮጵያ ወገን የሆኑት ዲፕሎማት ያስረዳሉ።


ድርድሩ ወደ አፍሪቃ ህብረት መመለሱ ለሀገራችን ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑንና ከዚሀ ቀደም ወደ ሌሎች የድርድር መድረኮች በመሄድ የተከሰቱ ስህተቶ የታረሙበት እርምጃ ነው።


ይሁንና ግብፅ የአፍሪቃ ህብረት ድርድር እንዳይሳካ በማድረግ ጉዳዩ በድጋሚ ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲመለስ ፍላጎት ሊኖራት እንደሚችል ነግረውናል።

በኢትዮጵያ በኩል ካሉ ተደራዳሪዎች እንደሰማነው ደግሞ በሚቀጥሉት ቀናት የሚጀመረው ድርድር ከዚህ ቀደም መግባባት ባልተደረሰባቸውና የህግ ብያኔ ባልተሰጠባቸው ቅንፎች ላይ ያተኮረ እንደሚሆንና ለዚህም የተደራዳሪ ቡድኑ ዝግጅትና ምክክር ማድረጉን አስታውቀዋል።


የግድቡ ውሀ አሞላልና አለቃቀቅ በተለይ የድርቅ ወቅት የውሀ ስሌት ፣ የግድቡ አስተዳደርና ቁጥጥር እንዲሁም የግድቡ የደህንነት ጉዳዩች በቴክኒክና በህግ ባለሙያዎች በሚቀርቡ አማራጮች ላይ አተኩሮ ይካሄዳል የሚል እምነት አላቸው።


የግድቡ የውሀ አሞላል የጊዜ ሰሌዳን በተመለከተ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮች በኩል እንዲዘገይ ብርቱ ፍላጎት ቢኖርም በኢትዮጵያ ወገን ሌላ አሳማኝ ምክንያት ካልተከሰተ በቀር ሙሌቱን የማዘግየትም ሆነ በጊዜ ሰሌዳው ላይ የመደራደር ዕቅድ የለም።

የህዳሴው ግድብን በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል መረጃን በወቅቱ በማድረስ በማብራራትና በተለያዩ ተቋማት መካከል ቅንጅት በመፍጠር በኩል ስር የሰደደ ችግር መኖሩንና ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ወቅታዊና የተብራራ መረጃ ማቅረብ ከመቼውም በላይ አስፈላጊ ነው ብለው እንደሚያምኑ ለዚህ ዘገባ ያነጋገርናቸው አራት የመንግስት የስራ ሀላፊዎች አስምረውበታል።


በድርድሩም ቢሆን ከዚህ ቀደም የተከሰቱ ተግዳሮቶችን እንደመማሪያ ወስዶ አሁን በአፍሪቃ ህብረት የተጀመረውን መድረክ በተገቢው መጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ።
በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ፣ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርና በተደራዳሪ ቡድኑ መካከል መናበብና ቅንጅት ካልተፈጠረ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ልናገኝ የሚገባንን የዲፕሎማሲ ድጋፍ ያኮሰምነዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]