House speaker, Tagesse Chaffo- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸሙትን ጭካኔ የተሞላበት ጅምላ ጭፍጨፋ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚያወግዝ ዓርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ምክር ቤቱ ታጣቂዎች በቅርቡ በጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ደቡብ ክልሎች ጭምር በንጹሃን ላይ የፈጸሟቸውን ግድያዎች አውግዟል። ምክር ቤቱ በዚሁ መግለጫው፣ የዜጎችን የሰላም ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጫለሁ ብሏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በንጹሃን ላይ የተፈጸመውን ግፍ የተሞላበት ጭፍጨፋ ያወገዘው፣ ከመንግሥት ጸጥታ ሃላፊዎች እና ከምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጭፍጨፋው ዙሪያ በዝግ ከመከረ በኋላ መሆኑን ገልጧል። ምክር ቤቱ ከመንግሥት ከፍተኛ ጸጥታ ሃላፊዎች ጋር ያካሄደውን ምክክር ለምን በዝግ እንዳደረገው ግን በመግለጫው አላብራራም።

የምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ቀደም ሲል የምክር ቤቱ የማኅበራዊ እና ባሕል ቋሚ ኮሚቴ በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ እንዲሁም በጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በንጹሃን ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችን እንዲያጣራ በደብዳቤ ማዘዛቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ሆኖም ቋሚ ኮሚቴው ለሚያደርገው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ማጣራት የአፈ ጉባዔው ደብዳቤ የጊዜ ገደብ አላስቀመጠም፤ ቋሚ ኮሚቴው ጭፍጨፋውን እና ግድያዎቹን በምን አግባብ እንደሚያጣራ ምክር ቤቱ የስነ ምግባር እና ሌሎች ደንቦችን በግልጽ ያስቀምጥ አያስቀምጥ አልተብራራም።

ይኸው ቋሚ ኮሚቴ ሃላፊነቱ ከተሰጠው ወዲህ፣ ጭፍጨፋውን እና ግድያዎቹን ማጣራት ይጀምር አይጀምርም ምክር ቤቱ በዛሬው መግለጫው ያለው ነገር የለም። የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ትናንት በሰጠው መግለጫ፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በታጣቂዎች የተጨፈጨፉት ንጹሃን ብዛት 338 ነው ብሏል።

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዮች በምዕራብ ወለጋ ጅምላ ጭፍጨፋ የተፈጸመው በተለይ በአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ መሆኑን በመግለጽ፣ ምክር ቤቱ ጭፍጨፋውን በአጣዳፊ አጀንዳነት ይዞ እንዲወያይበት ሃሳብ አቅርበው፣ አፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ አጀንዳውን ባለመቀበላቸው የአብን ተወካዮች ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው ይታወሳል።

ይህንኑ ተከትሎ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት አብን የምክር ቤቱን ስብሰባ ለፖለቲካ መሳሪያነት ተጠቅሞበታል በማለት እስከመክሰስ ደርሶ ነበር። ከአብን ቀጥሎ ኢዜማ እና የቁጫ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወይም ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት በወለጋው የንጹሃን ዜጎች ግድያ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ ምክር ቤቱን በዚህ ሳምንት በደብዳቤ መጠየቃቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]