27749793_1585460288201951_2002486987164446213_n (1)

ዋዜማ ራዲዮ- ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት ከሰባት ዐመታት በፊት “አሸባሪ” ብሎ ከፈረጀው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ጋር በኬንያ አስተናጋጅነት ለሦስተኛ ዙር ሰላም ድርድር ተቀምጦ ሰንብቷል፡፡ ድርድሩ የተካሄደው ከመንግስትም ሆነ ኦብነግ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያሉ መሆኑ ደሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በኦጋዴን እምቅ ነዳጅ ሃብት እንዳለ መገመቱ እንዲሁም ኢትዮጵያን፣ ሱማሌያንና ኬንያን የሚያካትት ቀጠናዊ ችግር በመሆኑ የአንዳንድ ዐለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት መሳቡ አልቀረም፡፡

መንግስት በህዝባዊ አመጽ ቀውስ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሁነኛ የፖለቲካ መዋቅራዊ ለውጦች እንዲያደርግ ከውስጥም ከውጭም ግፊቱ ጠንክሮበታል፡፡ በገባበት ቀውስ አስገዳጅነትም በሽብር ወንጀል ያሰራቸውን ፖለቲካኞች ሳይቀር እየፈታ ባለበት ሰዓት ነው ከኦብነግ ጋር ቀደም ሲል የጀመረውን ድርድር እንደገና የቀጠለው፡፡ በርግጥ በወህኒ ቤት እየማቀቁ ያሉ የኦብነግ አመራሮችና አባላት ያሁኑ የመንግስት ምህረት ተጠቃሚ መሆን አለመሆናቸው ወደፊት ይታያል፡፡

በርግጥ ኦብነግም አጣብቂኝ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ድርጅቱ ከሁለት የተከፈለው ከጥቂት ዐመታት በፊት ነው፡፡ እናም በአቶ መለስ ዜናዊ የመጨረሻ ስልጣን ዘመን ወቅት አንደኛው ተገንጣይ ክንፍ ከመንግስት ጋር ስምምነት ሲፈጽም አቶ መለስ “ከዚህ በኋላ ኦብነግ የሚባል ድርጅት የለም” ብለው ነበር፡፡ ሰሞኑን ድርድር የተካሄደው ከቀሪው የኦብነግ አመራር ጋር ነው፡፡ ከሦስት ዐመታት በፊት ከመንግስት ጋር ያለውን ሰላም ድርድር ለማቀላጠፍ ወደ ኬንያ የተጓዙ ሁለት አመራሮቹ ታነው እንደተወሰዱበት ገልጧል፡፡

የኦብነግ መዳከም

ባለፉት ጥቂት ዐመታት መሪዎቹ በመንግስት ደኅንነት ሃይሎች ከጎረቤት ሀገራት እየታፈኑ እንደተወሰዱበት የገለጸ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በመንግስት ጥቅማጥቅሞች ተደልለው እጃቸውን ስለሰጡ ድርጅታዊ ቁመናው ተዳክሟል፡፡ ታጣቂዎቹም በሱማሌ ክልል በርካታ ሥፍራዎች ድባቅ ተመትተው ተበታትነውበታል፡፡ የሱማሊያ መንግስትም ቀስ በቀስ በመጠናከሩ መጠጊያ ለማግኘት ዕድሉ አንሷል፡፡ ባጭሩ በትጥቅ ትግሉ ውጤታማ መሆን የሚችልበት ዕድል ከሞላ ጎደል እንደተሟጠጠ የተገነዘበበት ወቅት ላይ እያለ ነው ድርድሩን የቀጠለው፡፡

ኬንያ ዘንድሮም አደራዳሪ መሆኗ ግን “አመራሮቼን በግዛቷ ታፍነውብኛል” የሚለውን ውንጀላ የሚያከሽፍና ይልቁንስ “አመራሮቹ በፍቃዳቸው እጃቸውን ሰጥተው ሊሆን ይችላል” የሚለውን ግምት የሚያጠናክር ነው፡፡

ይህንን ነባራዊ ሃቅ ተንተርሰን ኦብነግ ለመሆኑ ባሁኑ ሰዓት ለሀገሪቱ ብሄራዊ ደኅንነት ይቅርና ለመንግስት ሥልጣንስ አደጋ ደቅኗንልን? የሚል ጥያቄ ብናነሳ የምናገኘው መልስ ላሁኑ በፌደራሉ መንግስትም ሆነ በሀገሪቱ ብሄራዊ ህልውና ላይ ከባድ ስጋት የደቀነ አይደለም የሚል ነው፡፡

አንዳንድ ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ታዛቢዎች ግን የሰሞኑን ሰላም ድርድር መንግስት በሕዝባዊ አመጽ አጣብቂኝ ውስጥ ከመግባቱ ጋር ያያይዙታል፡፡ ግምቱ ግን ብዙም ውሃ የሚቋጥር አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ካነሳናቸው የኦብነግ ደካማ ጎኖች በተጨማሪ ድርጅቱ ላለፉት ሁለት ዐመታት ሀገሪቱ ሲንጣት በኖረው ህዝባዊ አመጽና የጸጥታ ችግር ውስጥ ሁነኛ ተሳታፊ አልሆነምና፡፡

የህወሐት ስሌት

ያም ሆኖ የኦሮሞና አማራ ሕዝቦች በተቃውሞውና አመጹ ቀንደኛ ተሳታፊ መሆናቸው በገዥው ግንባር ውስጥ ያለውን የብሄሮች ሃይል አሰላለፍ ላይ መጠነኛ ለውጥ መፍጠር ስለፈጠረ የሱማሌ ክልልና ክልሉን የሚመራው የሱማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶሕዴፓ) ወደ ገዥው ግንባር የብሄር ፖለቲካ ቁርሾ ተጎትተው ገብተዋል፡፡ ጎረቤታሞቹ ኦሕዴድና ሶሕዴፓ ድርጅታዊና መንግስታዊ ቅራኔ ውስጥ ሲገቡ ባንጻሩ ሕወሃትና የኢሕአዴግ አባል ያልሆነው ሶሕዴፓ የተሟሟቀ ድርጅታዊ መፈቃቀድ ነው የጀመሩት፡፡ የፌደራሉ መንግስትም ቢሆን በአስር ሺዎች የሚገመቱ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ባፈናቀሉና ግድያ በፈጸሙ የሱማሌ ክልላዊ መንግስት ሃላፊዎች፣ የሶሕዴፓ ካድሬዎች እና የልዩ ፖሊስ አባላት ላይ ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ ዳተኛ መሆኑ ይህንኑ የድርጅትና ብሄር አሰላለፍ ለውጥ እንደሚያጠናክር አድርገን ብንወስደው ስህተት አይሆንም፡፡

መንግስት ዘላቂ ግብ ባይኖረው እንኳ አሁን የገጠውን ቀውስ ለማለዘብና የጠለሸ ስሙን ለማደስ ሲል ድርድሩን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ሊሰራበት ማሰቡ አይቀርም፡፡ እንደሚታወቀው እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ዐለማ ዐቀፍ የመብት ተሟጋቾችና ሀገራት በተለይ የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ አስተዳደር ኦብነግን ለመጠራረግ ባለሙ ተከታታይ ወታደራዊ ዘመቻዎቹ ኦጋዴንን ወደ ጦርነት ቀጠና በመቀየር በኦጋዴኖች ላይ ጅምላ ግድያ፣ ማፈናቀል እና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቸ መፈጸሙን ጠቅሰው ሲወነጅሉት መኖራቸው የሚታወስ ነው፡፡

በሌላ በኩል በኤርትራ የተጠለሉ ሌሎች ታጣቂዎችን ለመነጠልም ይጠቅመዋል፡፡ ኦብነግ ኤርትራ ውስጥ ካሉ ታጣቂዎች ጋር ጥምረት ባይፈጥርም መንግስት ግን ኤርትራ ኦብነግንንእንደምትደግፍ ሲወነጅል ነው የኖረው፡፡

ዞሮ ዞሮ ሁለቱም ወገኖች አሁን ያሉበት ተጨባጭ ሁኔታ የድሮውን አቋማቸውን አለሳልሰው ሁነኛ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ያበረታታቸው ነው የሚመስለው፡፡ ያ ማለት ግን ማሳካት የሚፈልጉት የመጨረሻ ግብም ሆነ ወደ ግባቸው የሚደርሱበት መንገድ አንድ ይሆናል ማለት አይሆንም፡፡

ሕወሃት ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ኦጋዴንን እንደ ፖለቲካ መጫዎቻ ካርድ ከመጠቀም ያለፈ ግብ ላይኖረው ይችላል፡፡ በርግጥ ስልጣኑን የሚያጣ ከሆነ ከወዲሁ በኦብነግ በኩል የሀገሪቱን የግዛት አንድነት አደጋ ላይ ከመጣል ወደኋላ እንደማይል ስር የሰደደ ጥርጣሬ ያላቸው ወገኖች ቀላል አይደሉም፡፡

በርግጥም የሀገሪቱን የግዛት አንድነት ከሚገዳደር ሃይል ጋር የሚደረግ ማንኛውም የሰላም ድርድር ወይም ስምምነት ከአንድ ገዥ ድርጅት ርዕዮተ ዐለም፣ መብትና አቅም የላቀ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡

ቁጥራቸው ባይታወቅም በርካታ የቀድሞ ኦብነግ ታጣቂዎች የሱማሌ ክልል ልዩ ሃይል አባላት ሆነዋል፡፡ ካሁን በፊት በዋዜማ ራዲዮ ባቀረብነው ዘገባ ሕወሃት አጠባቂኝ ውስጥ ከገባ የሱማሌ ክልል ወይም ኦጋዴን የመገንጠል ጥያቄ እንዲያነሱ በማድረግ የፖለቲካ ቁማር ሊጫወት እንደሚችል አንስተናል፡፡ አሁን እየታየ ያለው አዝማሚያም በከፊል ይህንኑ የሚያጠናክር ይመስላል፡፡

ድርድሩ በምን ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሊሆን ይችላል?

ለመሆኑ ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት ከኦብነግ ጋር በሚያርገው ድርድርና ምናልባትም የመጨረሻ ስምምነት ውስጥ ቁልፍ ሆነው የሚነሱት ጉዳዮች ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ማንሳት የጉዳዩን አሳሳቢነት ለመገንዘብ ይጠቅማል፡፡

በርግጥ ኦብነግ በጊዜ ብዛት በተቀያየሩ ፖለቲካዊና ጅኦፖለቲካዊ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፈ ድርጅት በመሆኑ አሁን ይዞት ያለው የመጨረሻ ግብ በትክክል ምን አንደሆነ እንኳ ግልጽ አይደለም፡፡ የኦጋደኒያ ሪፐብሊክን መመስረት ወይም በሂደት ከሱማሊያ ጋር መዋሃድ፣ ሰፋ ያለ የውስጥ የራስ ገዝ አስተዳደር ማግኘት፣ አሁን ባለው አወቃቀር የፌደራሉ መንግስት ሥልጣንና ሃብት ተጋሪ መሆን፣ የሱማሌ ክልል መንግስትን በበላይነት መቆጣጠር ከመሳሰሉ አማራጮች መካከል የትኛውን እንደሚመርጥ አስረግጦ  አይናገርም፡፡ አሁን ካለው የቀጠናው ጅኦፖለቲካዊ ሀኔታ አንጻር ስናየው ግን ሰፋ ያለ የውስጥ ራስ ገዝ አስተዳደር የማግኘቱ ጉዳይ ሊያመዝንበት እንደሚችል ግምት መያዝ ይቻል ይሆናል፡፡

በድርድሩ ሂደት ኦብነግ የታሰሩ መሪዎች ካሉት እንዲለቀቁለት የሚለው አንዱ ቅድመ ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ በርግጥ መንግስትም አሁን በያዘው በፖለቲካም ይሁን በሽብር የታሰሩ እስረኞችን የመፍታት ማዕቀፉን ተገን አድርጎ የኦብነግ ሰዎችን ለመፍታት ጥሩ ዕድል አለው፡፡ ሌላው የፌደራሉ ጦር ሠራዊት ቀስ በቀስ በክልሉ ያለው ቁጥር እንዲቀንስ ማድረግ እንደሚሆን ይገመታል፡፡

የኦብነግ ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው ከሱማሌ ክልል ልዩ ሃይል ጋር ወይንም ከፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ጋር እንደምን እንደሚቀላቀሉ. ለዐመታት በኦጋዴን ህዝብ ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሳ ስለሚከፈልበት ሁኔታም ሊነሳ ይችላል፡፡ ዐለም ዐቀፉ የግጭት አጥኝ International Crisis Group ማንኛውም የሰላም ድርድር ሦስቱ መንግስታት በኦጋዴን ሲፈጽሟቸው የኖሯቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚሽን እንዲቋቋም ጭምር ጥሪ ሲያደርግ የኖረ ቢሆንም ይሄን ጉዳይ ግን መንግስት መቀበሉ አጠራጣሪ ነው፡፡

ሌላው ቅድመ ሁኔታ በተሻሻለ ሕገ መንግስት ውስጥ የተለየ ውስጣዊ አስተዳደራዊ ነጻነት አግኝቶ ሱማሌ ክልልን መምራትም አንዱ ቅድመ ሁኔታ እንደሚሆን ይታሰባል፡፡ ወደፊት ተቆፍሮ ከሚገኘው የኦጋዴን የተፈጥሮ ነዳጅ ሃብት ክልሉ ከፍተኛውን ድርሻ እንዲያገኝ የመፈለግ ጥያቄም ይነሳ ይሆናል፡፡

በክልሉ ሕዝበ ውሳኔ በማድረግ ቢያንስ ኦጋዴን የራሱን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱን እስከ መገንጠል ድረስ እንዲጠቀምበት ማስቻል ከፍተኛው የስምምነቱ አካል ነው የሚሆነው፡፡ በርግጥ ለሩብ ክፍለ ዘመን ፈራርሳ የኖረችው ሱማሊያ ገና በእግሯ ስላልቆመች ኦብነግ ኦጋዴንን ገንጥሎ ከሱማሊያ ጋር ሊያዋህድ የሚችልበት ዕድል ከሞላ ጎደል ዝግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሱማሊያ ሰላምና ጸጥታ ቁልፍ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውም መንግስት ከሱማሊያ የሚነሳውን የኦብነግ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለማዳከም ሳይጠቅመው አልቀረም፡፡

እዚህ ላይ ችግሩ መንግስት ለኦጋዴን ልዩ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ህገ መንግስታዊ መብት ቢፈቅድ በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል፣ ሲዳማ ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንዲነሱ በር ስለሚከፍት ሕገ መንግስታዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል የሚለው ስጋት ነው፡፡ የራስ ዕድል በራስ መወሰን መብትን ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደው የ1979ኙ ሕገ መንግስትም ኦጋዴን ከአምስቱ ልዩ ራስ ገዝ አስተዳደሮች አንዷ አድርጓት ነበር፡፡

ኢህአዴግ ባንድ በኩል ከኦብነግ ጋር ላለፉት ስድስት ዐመታት ሲያካሂደው የኖረውን የሰላም ድርድር በተጓዳኝ ኦሕዴድ በውጭ ሀገር ሆነው በነፍጥ እንታገላለን ለሚሉና የኦሮሞ ብሄርን ለሚወክሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች የዘንባባ ዝንጣፊ በማቅር አብረን ለመስራት ፈቃደኛ ነን የሚል ምልዕክት እንዲያስተላልፉ ዕድል ሰጥቷል፡፡ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር ጥምረት የፈጸመው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የሚመሩት ሌንጮ ለታ ለኦሕዴድ ጥሪ ፈጥነው በጎ ምላሽ መስጠታቸውም አንድ ስውር ጉዳይ እንዳለ ጠቋሚ ነው፡፡

ሶሕዴፓም መንግስት ከኦብነግ ጋር ባደረገው የሰላም ድርድር ተሳታፊ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ እንዲህ የሚደረገው ከርዕዮተ ዐለም አንጻር የአንድነት ሃይሎችን፣ ከብሄር አንጻር ደሞ የአማራ ብሄርን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማዳከም እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ በአሸባሪነት ከፈረጃቸው ሌሎች በኤርትራ ከመሸጉ ታጣቂ ድርጅቶች ጋር ለመደራደር ግን እስካሁን ይፋዊ ፍላጎት አላሳየም፡፡

የይስሙላ ድርድር በሀገር ቤት

ሌላ በኩል ደሞ ኢሕአዴግ ሕዝባዊ መሠረት የሌላቸውን ጥቃቅን ተቃዋሚ ድርጅቶች አራት ኪሎ ላይ ሰብስቦ የይስሙላ የሚመስል የፖለቲካ ድርድር እያደረገ መሆኑን ይሰብካል፡፡ የትኛውን የምር አድርጎ እንደያዘው ለመናገር ግን ብልጣብልጥነት ያጠላበት እና ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ማግኘትን ግቡ ያደረገው ባህሪው ምቹ አይደለም፡፡

መንግስት የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑትን አቶ አብዲ ኢሌን ከኦብነግ ጋር ሲያደርገው ለሰነበተው የሰላም ድርድር መወከሉ ተሰምቷል፡፡ ድርድሩ ግን ከሀገሪቱ የግዛት አንድነት፣ ከሀገረ መንግስትነት ህልውናዋ እና ብሄራዊ ደኅንነቷ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ አንጅ የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልልን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ለዚህም ነው የማዕከላዊው መንግስትን ጥቅም ሊያስጠብቁ የማይችሉትን፣ እንዲያው በጉዳዩ የራሱ ልዩ ጥቅም ያለውን ክልል የሚመሩ ግለሰብን ለድርድሩ መላኩ ምናልባት መንግስት ከሕዝቡ ጀርባ ሚስጢራዊ ቁማር እተጫወተ ይሆናል የሚለውን ስጋት አጠናክሮታል፡፡

በርግጥም አብዲ ኤሊ የመንግስትና ኦብነግ አገናኝ መስመር የሆኑ ነው የሚመስለው፡፡ ወትሮውንም ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት ከሀገር-በቀል ታጣቂ ሃይሎች ጋር ይቅርና ከጎረቤት ሀገር መንግስታት ጋር እንኳ የሚፈጽማቸው የዐለም ዐቀፍ ድንበር ማካለል ሂደቶችን ሚስጢራዊ የሚያደርገው ብሄራዊ ደኅንነትና የሀገሪቱን ግዛት አንድነት የማስጠበቅ ሞራላዊ ብቃት ስለሚያጥረው እንደሆነ የሚያምኑ ወገኖች ቀላል አይደሉም፡፡

ቀጠናው ሰላሙ ተጠብቆ ልማቱ ቢፋጠን ሕገ ወጡን ገበያ ወደ መደበኛ ግብይት በመቀየር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ማድረግ በተቻለ ነበር፡፡ ችግሩ ከፌደራሉም ሆነ ከክልሉ መንግስት የሕገ ወጡ ንግድ ተጠቃሚ የሆኑ አካላት የመኖራው ነገር ነው፡፡

በሌላ በኩል መንግስት ከኦብነግ ጋር ብቻ በተናጥል የሚያደርገው ድርድር በሱማሌ ክልል ያሉ ሌሎች የኦጋዴን ተቀናቃኝ ጎሳዎችን እንደሚያሳስባቸው የታወቀ ነው፡፡ እንደ ኢሳቅ ያሉ ጎሳዎች ኦብነግ እንደገና የክልሉ መንግስት አካል ሆኖ ይቅርና አሁን ያለው የአብዲ ኤሌ መንግስትም ለኦጋዴኖች ያደላል የሚል ስር የሰደደ ቅሬታ አላቸው፡፡ ምናልባት ከኦብነግ ጋር ስምምነት ተደርሶ ክልሉን የማስተዳደር ሃላፊነቱ ከሞላ ጎደል ለኦጋዴኖች ከሰጠ ሰላም የመገኘት ዕድሉን ያጠበዋል፡፡የድርድሩ የመጨረሻ ውጤት ለህዝብ አልተገለፀም፣ ቀጣይ ዙር ድርድር እንደሚኖር ይጠበቃል። [ዝርዝር የድምፅ ዘገባውን ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/qjB6noZi2Fk