Oromia IDPs -PHOTO-OPride
Oromia IDPs -PHOTO Credit -OPride

ዋዜማ ራዲዮ- በቅርቡ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን በአዲስ አበባ ዙሪያ ለማስፈር በተደረገ ጥረት በተነሳ አለመግባባት የሰው ህይወት መጥፋቱን በቦታው የተገኙ እማኞች ገለፁ።
እማኞች እንደነገሩና የዋዜማ ሪፖርተር እንዳጣራችው በአዲስ አበባ በኮልፌ አቅጣጫ አዲስ አበባና ኦሮምያ በሚዋሰኑበትና በኦሮምያ ክልል በሚገኘው አሸዋ ዴዳ በተባለው አካባቢ ከዚህ ቀደም ከገበሬዎች ላይ መሬት በመግዛት መኖሪያ ቤት ገንብተው በአካባቢው የሚኖሩና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን ለማስነሳት የተደረገው ሙከራ ደም አፋሳሽ ሆኗል።
“ህጋዊ አይደላችሁም” በሚል ከአካባቢው እንዲለቁ የተነገራቸው ነዋሪዎች ከደንብ አስከባሪዎች ጋር አርብ ዕለት በፈጠሩት ግጭት የአንድ ሰው ህይወት መጥፋቱንና በርካቶች መጎዳታቸውን ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።
ግማሽ ሚሊየን ያህል ዜጎች ከሶማሌ ክልል ከተፈናቀሉ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ ለማድረግ እየተሞከረ ሲሆን አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ቀድሞ ወደ ነበሩበት ሶማሌ ክልል የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ገልፀዋል።
ተፈናቃዮቹን በአዲስ አበባ ዙሪያ ለማስፈር የኦሮምያ ክልል እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን ቀደም ሲል ከገበሬዎች መሬት በመግዛትም ሆነ በተለያየ መንገድ የመኖሪያ ቤት የገነቡ ነዋሪዎች መሬቱን እንነጠቃለን በሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።
በተለይ ከዛሬ ነገ “ህጋዊ ት ሆናላችሁ”  ተብለው ከአስር አመታት በላይ ግብር እየከፈሉ መቆየታቸውን ገልፀው አሁን ግን የኦሮምያ ክልል የመሬት አስተዳደር ስራተኞች በየኣአካባቢው እየተዘዋወሩ ቅኝት በማድረግና መረጃ በማሰባሰብ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል።
የኦሮምያ ክልል ተፈናቃዮችን በተለያዩ አካባቢዎች የማስፈር እቅድ እንዳለው ገልፆ መልሶ ማስፈሩ የተፈናቃዮችን ፍላጎትና የኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ እንደሚሆንና ሁሉንም በአዲስ አበባ ዙሪያ የማስፈር እቅድ አለመኖሩን ገልጿል።
በርካታ ተፈናቃዮች ከአዲስ አበባ ርቀው ባህላቸውና ወጋቸው ወደሚመሳሰልበት አካባቢ ለመስፈር ፍላጎት እንዳላቸው እንደነገሩት የኦሮምያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ባልደረባ ነግሮናል።