Kenya and Ethiopia leaders press briefing in Nairobi mid June 2016
Kenya and Ethiopia leaders press briefing in Nairobi mid June 2016

ዋዜማ ራዲዮ- ሃያ አራት ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል የተባለለት ኢትዮጵያን፣ ኬንያንና እና ደቡብ ሱዳንን በመሰረተ ልማት የሚያስተሳስረውላፕሴትየተሰኘው ክፍለአህጉራዊ የልማት ፕሮጄክት ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ በዓይነቱና በግዙፍነቱ በቀጠናው ተወዳዳሪ የሌለው ላፕሴት ከወዲሁ የውስጥና የውጭ እንቅፋቶች በዝተውበታል፡፡ የፕሮጄክቱ ዕምብርት ትሆናለች ተብላ የምትጠበቀው የኬንያዋ ላሙ ወደብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከታንዛኒያና ጅቡቲ ወደቦች ከባድ ፉክክር ገጥሟታል፡፡ በተለይ ከኬንያ ጋር ወደ ላሙ ወደብ የጋራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ለመዘርጋት ተስማምታ የነበረችው ኡጋንዳ ከሁለት ወራት በፊት ሃሳቧን ቀይራ ፊቷን ወደ ታንዛኒያ ወደብ ማዞሯ ለላፕሴት ከባድ መርዶ ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል ከጥቂት ቀናት በፊት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ናይሮቢ ተጉዘው ከላሙ ወደብ ወደ አዲስ አበባ ነዳጅ ሊያስተላለፍ የሚችል ቱቦ ለመዘርጋት መግባቢያ ስምምነት መፈረማቸው ለላፕሴት ነፍስ ይዘራለት ይሆናል የሚል ተስፋ አጭሯል፡፡

ቻላቸው ታደሰ ዝርዝር ዘገባ አለው፣ እዚህ በድምፅ ያገኙታል አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ

እውን ብዙ የተወራለት ላፕሴት ቅዠት ሆኖ እየቀረ ነው? ወይንስ እያንሰራራ ነው? ክፍለአህጉራዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ከብሄራዊ ደህንነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችስ በላፕሴት ላይ ምን አሉታዊ ወይም በጎ ተፅዕኖ አላቸው? በላፕሴት ዙሪያ የሚታዩት ለውጦችስ በቀጠናው ሀገሮች ኃይል ሚዛን ሽግሽግ ያስከትሉ ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡

ላፕሴት ከአራት ዓመታት በፊት ሲጠነሰስ ዋና ዓላማው በህንድ ውቂያኖስ ዳርቻ ኬኒያ ልትገነባ ያሰበቸውን የላሙ ወደብ ከሰሜን ኬንያ፣ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን ነዳጅ ዘይት ጉድጓዶች ጋር በማገናኘት ሦስቱ ሀገሮች በጋራ ማስተላለፊያ ቱቦ ነዳጃቸውን ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ታስቦ ነበር፡፡ የላሙ ወደብና ነዳጅ ማጣሪያ ግንባታን፣ የነዳጅ ቱቦ፣ አውራ ጎዳናዎች፣ የባቡር ሃዲድ፣ ሦስት አዳዲስ ከተማዎችንና ሦስት አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታዎችን ያቀፈው ላፕሴት የአፍሪካ ቀንድ ክፍለ አህጉርን በመሰረተልማት ለማስተሳሰር ያስችላል የተባለለት ግዙፍ ውጥን ነው፡፡ ሆኖም እኤአ 2021 ይጠናቀቃል ቢባልም ላፕሴት ገና ከጅምሩ ነበር ላይሳካ ይችላል በሚል የተሰጋለት፡፡

ኬንያ በሰሜናዊ ቱርካና ግዛቷ ኡጋንዳ ደግሞ ከአልበርት ሐይቅ አካባቢ ነዳጅ ዘይት እያለሙ ስለሆነ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኡጋንዳ የላፕሴት ስምምነት አካል ባትሆንም ከኬንያ አስር ዕጥፍ የሚልቅ ነዳጅ ክምችት ስላላት ከኬንያ ጋር በጋራ ቱቦ በላሙ ወደብ በኩል ነዳጇን ለውጭ ገበያ መሸጧ ግን ለኬንያም ሆነ ለላፕሴት ጉልህ ጠቀሜታ አለው፡፡ አራት ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል ተብሎ የተገመተው የላፕሴት ሰሜናዊ ኮሪደር የሆነው የሁለቱ ሀገሮች የጋራ ነዳጅ ቱቦ በቀን 300 ሺህ በርሜል ድፍድፍ እንዲሸከም ታስቦ ነበር፡፡ ላፕሴት ቢሳካ ኬንያ በልማት ኋላ ቀርነትና ግጭት የሚታመሱትን ሰሜናዊ ግዛቶቿን ለማልማት እንደሚረዳት ይታመንበታል፡፡

ክፍለአህጉራዊ የጋራ መሰረተልማት ፕሮጄክት ላፕሴት ገና ከጅምሩ ነው ብዙ ፈተናዎች የተጋረጡበት፡፡ በተለይ ኬንያና ታንዛኒያ የቀጠናው ኃያል ሀገር ለመሆን የሚያደርጉት የቆየ ታሪክ ያለው ፉክክር በላፕሴት ዕጣ ፋንታ ላይ ቀጥተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ አልቀረም፡፡

ምንም እንኳ ኡጋንዳ የላፕሴት አካል ባትሆንም ከኬንያ ጋር በጋራ ልትዘረጋው አስባው የነበረው ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ዋነኛው የላፕሴት ተስፋ ነበር፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ግን ኡጋንዳ በኬንያው ሰሜን ኮሪደር በኩል ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሯን ለመዘርጋት የነበራትን ሃሳብ ቀይራ በታንዛኒያው ታንጋ ወደብ በኩል ለመዘርጋት ከታንዛኒያ ጋር ስምምነት በመፈፀሟ የላፕሴት ሰሜናዊ ኮሪደር ውጥን ውሃ በልቶት ቀርቷል፡፡ የሙሴቬኒ መንግስት ውሳኔ ለኬንያዊያን መራራ ጽዋ ሆኖባቸዋል፡፡ ከፍተኛ ነዳጅ ክምችት ያላት ኡጋንዳ ላሙ ወደብን ካልተጠቀመችበት ኬንያ ለወደቡ ግንባታ ግዙፍ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሷ ያጠራጥራል ይላሉ ታዛቢዎች፡፡ ወደቡም አዋጭ ላይሆን ይችላል፡፡ ኬንያ የላሙ ወደብንም ሆነ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ግንባታ በቅጡ ያልጀመረችው የኡጋንዳን የመጨረሻ ውሳኔ እስክታውቅ ነበር፡፡

ኡጋንዳ በላሙ ወደብ በኩል ለመጠቀም ያልፈለገችባቸው ምክንያቶች አሏት፡፡ ባንድ በኩል ኬንያ የላሙን ወደብ ለመገንባት የሚስችላትን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ብድር ለማሰባሰብ በመቻሏ ላይ ጥርጣሬ አላት፡፡ በኬንያ መሬት በግለሰቦች የተያዘ በመሆኑ ለግለሰቦች የሚከፈለው ካሳ ክፍያ ከፍተኛነት ከልምድ  የሚታወቅ እና የተጓተተ የፍርድ ቤት ክርክር የሚያስከትል መሆኑ ሌላኛው የሽሽቷ ምክንያት መሆኑን ትጠቅሳለች፡፡ በሰሜን ኬንያም ሆነ ላሙ ወደብ አካባቢ የደህንነት ስጋቶች መኖራቸም ስጋት እንደፈጠረባት አልሸሸገችም፡፡ በተለይ የኡጋንዳው ነዳጅ ማስተላለፊያ ያልፍበታል ተብሎ የሚጠበቀው የሰሜን ኬንያ አከባቢ ለተደራጁ ወንጀለኞችና አልሸባብ መናህሪያ መሆኑ ስጋቷን አባብሶታል፡፡ ከኢኮኖሚ አዋጭነት አንጻርም ቢሆን ታንዛኒያ ለአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ኡጋንዳን የምታስከፍለው ቀረጥ ኬንያ ካቀረበችው ዋጋ በአምስት ዶላር ማነሱ ሌላኛው ምክንያቷ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

የጋራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦው ግንባታ ውጥን መክሸፍ ለኬንያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ውደቀት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ የቀጠናው ኢኮኖሚ ዕምብርት ለመሆን በምታደርገው ጥረት ላይም ውሃ የሚቸልስ ነው፡፡ በዚህ የተበሳጩት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኡጋንዳ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት ገበያ ድርሻ ያለው የፈረንሳዩ ኩባንያ ቶታል ካፓላ የታንዛኒያውን መስመር እንድትመርጥ ግፊት አድርጋል በሚል ወቅሰዋል፡፡ቶታል ወንድማማች ህዝቦችን እንዲከፋፍል ሊፈቀድለት አይገባምሲሉም ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ያም ሆኖ የኡሁሩ ኬንያታ መንግስትኡጋንዳ ከጅምሩም የላፕሴት ባለድርሻ ባለመሆኗ ሃሳቧን መቀየሯ በፕሮጄክቱ ላይ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣምበሚል ማስተባበያ የላፕሴትን ነፍስ ለማቆየት እየተሯሯጠ ይገኛል፡፡

በላፕሴት ላይ አሉታዊ አሻራውን አሳርፎ የቆየው ሌላኛው መሰናክል የደቡብ ሱዳን የርስርበርስ ግጭት ነው፡፡ዕቅዱ ደቡብ ሱዳን የራሷን ነዳጅ ማስተላለፊያ በመዘርጋት ከኬንያና ኡጋንዳ የጋራ ቱቦ ጋር በማገናኘት በላሙ ወደብ በኩል ነዳጇን ትሸጣለች የሚል ነበር፡፡ ካርቱም በምትጥልባት ከፍተኛ ቀረጥ የተማረረችው ደቡብ ሱዳን ተስፋዋን በላፕሴት ላይ ጥላ ቆይታለች፡፡ ኬንያም ከኡጋንዳ ሽሽት በኋላ ወዲያውኑ ነበር  ረስታት ወደቆየችው ደቡብ ሱዳን ፊቷን ያዞረችው፡፡

አሁን የጁባ ኢኮኖሚ በሁለት ዓመቱ ርስበርስ ግጭት ክፉኛ ደቋል፡፡ የነዳጅ ዘይት ምርቷ በግጭቱ ሳቢያ መቀነስ እንዲሁም የነዳጅ ዓለም ዓቀፍ ዋጋ ማሽቆልቆል ከነዳጅ የምታገኘውን ገቢዋን ቀንሶባታል፡፡ ባሁኑ ጊዜ ዓለም ዓቀፍ የነዳጅ ኩባንያዎችም ለደቡብ ሱዳን አዲስ ነዳጅ ቱቦ ዝርጋታ ብድር ለመስጠት መቻላቸው እጅጉን አጠራጣሪ ነው፡፡ ዓለም ዓቀፍ ነዳጅ ድርጅቶች ራሳቸው በነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል ሳቢያ ኪሳራ ውስጥ ስለሆኑ እንዲህ ዓይነት ፕሮጄክቶችን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለመደገፍ ተነሳሽነት ይኖራቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡

የኡጋንዳን ውሳኔ መቀየር ተከትሎ ከቀናት በፊት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትርና የኬንያው ፕሬዝዳንት ናይሮቢ ላይ በሞት አፋፍ ላይ ላለው ላፕሴት ነፍስ የሚዘራ አዲስ ስምምነት ደርሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከላፕሴት ዕቅድ ጋር በሚጣጣም መልኩ ከላሙ ወደብ በሞያሌ በኩል ወደ አዲስ አበባ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ለመዘርጋት ተስማምታለች፡፡ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ዝርጋታው እንደሚጀመርም ሁለቱ መሪዎች ገልፀዋል፡፡

በሁለቱ ሀገሮች ስምምነት ዙሪያ ግን ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ አዲሱ ስምምነት የገባው ከምር ላፕሴትን ከውድቀት ለመታደግ ፈልጎ ነው? ጊዚያዊ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ጨዋታ ነው? ወይስ ወደብ አልባዋን ሀገር ተጨማሪ አስተማማኝ የነዳጅ ማስገቢያ መስመር እንዲኖራት ታስቦ የተደረገ ኢኮኖሚያዊ ስሌት ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ጊዜው ገና ነው፡፡

አዲሱን ስምምነት አጠራጣሪ የሚያደርገው ሌላኛው ጉዳይ የላፕሴት ባለድርሻ የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት ከወራት በፊት 550 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ ለመዘርጋት ስምምነት መፈፀሙ ነው፡፡ መንግስት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በሰሜን ኬንያ ያለው ፀጥታ ሁኔታ ማሽቆልቆልና የደቡብ ሱዳንን ግጭት ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ይታመናል፡፡ የጅቡቲው ነዳጅ ቱቦ ዝርጋታ ዕቅድ እየተፋጠነ መሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ከላፕሴት ይልቅ ወደ ጅቡቲ ወደብ ለማዘንበሉ ማረጋገጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ላፕሴት ከመጠንሰሱ በርካታ ዓመታት ቀደም ብሎ የጅቡቲ ወደብን የምስራቅ አፍሪካ ሎጅስቲክስ ማዕከል ለማድረግ ሲጥሩ መቆየታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ብቻ ሳይሆን ከሱዳንም ነዳጅ በብዛት የምታስገባ በመሆኗ የላሙ ወደብን ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት አጠራጣሪ ያደርገዋል ይላሉ ባለሙያዎች፡፡

የኡጋንዳን ውሳኔ መቀየር ተከትሎ የመጣው ይኸው ስምምነት የጋራ መግባቢያ ስምምነት እንጂ አጠቃላይ አሳሪ ስምምነት አለመሆኑም ትኩረት መሳቡ አልቀረም፡፡ ስምምነቱ ድንገተኛና ቀደም ብሎ ድርድሮችና ውይይቶች ያልተካሄዱበት መሆኑም ይህንኑ ጥርጣሬ አጉልቶታል፡፡  ስምምነቱ ግልፅ ያላደረጋቸው ሌሎች ጉዳዮችም አሉ፡፡ ከላሙ ወደብ ወደ አዲስ አበባ የሚዘረጋው ቱቦ በቀጥታ ወደ ሞያሌ የሚያልፍ ነው ወይስ ከደቡብ ሱዳን ጁባ ጋር የሚተሳሰር ነው? የሚለው ጥያቄ ገና ምላሽ አላገኘም፡፡ አሁን ደቡብ ሱዳን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ግን የመሰረተ ልማት ትስስሩን አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡

በግዙፍ የውጭ ዕዳ የተዘፈቀችው፣ ሌሎች ሜጋ ፕሮጄክቶችን በውዝፍ የተወችው እና በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ጎረሮዋ የታነቀው ኢትዮጵያ ከሁለት ሃገሮች ጋር ሁለት ረዥምና ግዙፍ ነዳጅ ቱቦዎችን ለመዘርጋት የሚያስችል የገንዘብ አቅም አላት ወይ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ የኬንያውን ቀርቶ የጅቡቲውን ቱቦ ማጠናቀቅ በራሱ ገና ብዙ መሰናክሎች እንደሚጠብቁት ዕሙን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከላሙ ወደብ ነዳጅ ለማግኘት ቁርጠኛ ብትሆን እንኳ ገና ኬንያ ከወደቡ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ያለውን ቱቦ ለመዘርጋት የሚያስችሏት ቴክኒካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መቀረፍ ይኖርባታል፡፡

በተለይ ኡጋንዳ በኬንያ መሬት ካሳ ክፍያ ውዝግብ፣ ከፍተኛ ቀረጥ እና ደህንነት ስጋት ሳቢያ ፊቷን ወደ ታንዛኒያ ባዞረችበት ሰዓት ኢትዮጵያ ዘው ብላ መግባቷ ምን መተማመኛ አግኝታ ነው የሚል ጥያቄም ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በተለይ ሰሜናዊ ኬንያ ለአልሸባብ ሽብርና የተደራጁ ወንጀለኞች ጥቃት የተጋለጠ መሆኑ ኢትዮጵያ ልትዘረጋ ባሰበችው ነዳጅ መስመር ላይ የደህንነት ስጋት መደቀኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ግን እነዚህን ሁሉ ስጋቶች በምን መንገድ ሊቀርፋቸው እንዳሰበ ፍንጭ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡

ለላፕሴት ሌላኛው ራስ ምታት ሩዋንዳ ከኬንያ ጋር በባቡር ሃዲድ ለመተሳሰር የነበራትን ዕቅድ ሰርዛ ፊቷን ወደ ታንዛኒያ ማዞሯ ነው፡፡ ወደብ አልባዋ ሩዋንዳ ከኬንያ ጋር በባቡር መስመር ብትተሳሰር ኖሮ በላፕሴት ማዕቀፍ ስር በተለይም ላሙ ወደብን የቀጠናው ገበያ ማዕከል ለማድረግ ከፍተኛ ድርሻ ነበረው፡፡

ሆኖም የኬንያ መንግስት ለቀጠናው ሀገሮች አዋጭና ተወዳዳሪ ገበያ ብሎም አስተማማኝ  የደህንነት ዋስትና መስጠት ባለመቻሉ በላፕሴት ዕቅድ ላይ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ የኬንያና የላፕሴት ተስፋዎች የነበሩትን ኡጋንዳንና ሩዋንዳን በተፎካካሪው ታንዛኒያ መነጠቁም የኡሁሩ ኬንያታ መንግስት ዲፕሎማሲ ውድቀት ያመጣው ጣጣ መሆኑን ብዙ ታዛቢዎች ይስማሙበታል፡፡ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳንና ታንዛኒያ የምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ አባላት ሲሆኑ ታዛኒያና ኬንያ የዚሁ ሰፊ ገበያ ማዕከል ለመሆን በጦፈ ፉክክር ተጠምደዋል፡፡ አሁን እየታየ ያውለው ግን የምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማዕከል ከኬንያ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ ታንዛኒያ እየዞረ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደሞ በላፕሴት የታቀፉት ሦስቱ ሀገሮች ለሚያስቡት ኢኮኖሚያዊና መሰረተልማት ትስስር መልካም ዜና አይደለም፡፡

እነዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ በማጣጣር ላይ ያለው ላፕሴት አንዳችም በቂ እስትንፋስ ላለማግኘቱ በቂ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ የቅርቡ የአዲስ አበባና ናይሮቢ ስምምነትም ቢሆን በላፕሴት ላይ ነፍስ ይዘራል የሚለው ተስፋ ዕምብዛም ይመስላል፡፡ አልሸባብ በኬንያ ላይ የሚፈጥረው ደህንነት ስጋትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቀረፋል ተብሎ ስለማይታሰብ በላፕሴት ስኬታማት ላይ አደጋ ደቅኖ መቆየቱ አይቀርም፡፡ የላፕሴት ዕጣ ፋንታ ኬንያ ውስጥ በሚዘረጉ ቁልፍ መሰረተልማቶች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆኑ በስኬታማነቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡ ላፕሴት ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ የኬንያ መንግስት በዘርፈብዙዎቹ የላፕሴት ፕሮጄክቶች ግንባታ ረገድ እዚህ ግባ የሚባል እመርታ አለማሳየቱም ከጅምሩም የፕሮጄክቱን ስኬታማነት ይጠራጠሩ ለነበሩ ታዛቢዎች ጥሩ አስረጂ ሆኖላቸዋል፡፡

የመንግስታቸውን ዳተኝነትና ቅርቃር ውስጥ የገባ ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ከወዲሁ የተገነዘቡት የኬንያ መገናኛ ብዙሃንየኡሁሩ ኬንያታ መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ የገባውን ላፕሴት ከውድቀት ሊታደገው የሚገባው አሁን ነውበማለት በመወትወት ላይ ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም እየተቃረበ በመሆኑ የፕሬዝዳንት ኬንያታ ጥምር መንግስት ሙሉ ትኩረቱን ለምርጫ ዘመቻው እንጂ ወደ ለላፕሴት ያደርጋል የሚለው ዕምነት አነስተኛ ነው፡፡