ebcዋዜማ ራዲዮ- ከሁለት ዓመት በፊት የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዮ የልደት በዓሉን በድምቀት ያከበረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቢሲ) ሁለት ወቅታዊ ፈተናዎች ከፊቱ እንደተደቀኑበት አመነ፡፡ እነዚህም የጣቢያው የማስታወቂያ ገቢ ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣቱና የበርካታ ተመልካቾች ወደ ግል የሳተላይት ጣቢያዎች ፊታቸውን ማዞራቸው እንደሆነ ማኔጅመንቱ ከከፍተኛ አዘጋጆች ጋር በቅርቡ ባደረገው የዉስጥ ዉይይት ተብራርቷል፡፡

በተለይም መንግሥት አንድ ልማታዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብን ለመፍጠር በሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት ወቅታዊና ትኩስ መረጃ ለአድማጭ ተመልካቾች በማቅረብ ረገድ ጣቢያው ለረዥም ዓመታት የማይተካ ሚና ሲጫወት እንደነበረና ኾኖም ይህ ሚናው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዳዲስ ጣቢያዎች ወደ ገበያው መጉረፍና በማኅበራዊ ሚዲያው ማየል የተነሳ ፈተና ዉስጥ መግባቱ ተመላክቷል፡፡

ጣቢያው አገራዊ ሚናውን ለማስጠበቅ ታዲያ ጊዜ ሳይሰጥ መውሰድ ያለበትን የእርምት እርምጃ አስመልክቶ ከከፍተኛ አዘጋጆች ጋር በስፋት እንደተነጋገረ በዉይይቱ ላይ የተሳተፉ የጣቢያው አንድ የወቅታዊ ፕሮግራም ከፍተኛ አዘጋጅ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ ይወሰዳሉ ተብለው አቅጣጫ ከተያዘባቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ ጣቢያውን በቻይናው CGTN(የቀድሞው CCTV) መልክ መልሶ ማዋቀርና 24 ሰዓት ሙሉ ዜናና ዘጋቢ ፊልሞችን ብቻ የሚያስተላልፍ ጣቢያ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ ይህን ማድረግ አሁን ወደ ገበያው እየመጡ ያሉ የሳተለይት የግል ጣቢያዎችን ልቆ ኢቢሲ በአሸናፊነት እንዲወጣ ያስችለዋል ተብሎ እንደታመነ እኚሁ ምንጭ ለዋዜማ ዘጋቢ አብራርተዋል፡፡

በዚህ መነሻ ጣቢያውን የ24ሰዓት የዜና ጣቢያ ለማድረግ ጥናት መጀመሩና ጥናቱ ሲጠናቀቅም ዶክተር ነገረ ሌንጮ ለሚመሩት ቦርድ ቀርቦ እንደሚጸድቅ እኚሁ የጣቢያው ባልደረባ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ ዋናው ኢቴቪ/ኢቢሲ በአገር ቤትና በዓለማቀፍ ቋንቋዎች ያስተላልፋቸው የነበሩ ፕሮግራሞችን ጨምሮ ዜና ነክ ያልሆኑ የመዝናኛ ዝግጅቶቹን ሙሉ በሙሉ በማጠፍ ወደ ኢቢሲ-3 ለማዘዋወር ሐሳቡ መኖሩም ተመልክቷል፡፡ ኢቢሲ-3 እሑድ መዝናኛን ጨምሮ ሁሉም የማኅበራዊና የስፖርት ዝግጅቶችን እንዲያስተላልፍ ዉጥን ተይዞለታል፡፡

ዋናውን ጣቢያ ሙሉ በሙሉ ወደ ዜና ጣቢያ (News Channel) እስኪሻገር የዜናና ወቅታዊ ጉዳዮችን አቀራረብ ከቀጥተኛ የልማታዊ ደረቅ ዘገባነት አውጥቶ በሕዝብ ጥያቄዎች ዙርያ የሚያጠነጥን ቅሬታ ተኮር፣ ለሕዝብ ጆሮ ሳቢና ዐይነግቡ የሆኑ የዘገባ አሠራሮችን ለመከተል የኢቢሲ ጋዜጠኞችን በባለሞያዎች ተከታታይ ሥልጠና እንዲያገኙ እንደሚደረግም ታውቋል፡፡ ይህ የሥልጠና መርሐግብር መሪ ጋዜጠኞችን ወደ ቻይና በመላክ ጭምር  ማሰልጠንን ያካትታል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው የቃና ቴሌቪዥን ጣቢያ ለተመልካች ከሚያቀርባቸው ተከታታይ የዉጭ ፊልሞች ባሻገር በአገራዊ ጉዳዮች የሚያተኩሩ ዜናዎችን እንዲያቀርብ ከብሮድካስት ባለሥልጣን ግፊት እየተደረገበት እንደሚገኝ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ 6 ወር በማይሞላ ጊዜ ዉስጥ የዜና መርሐግብር ለመጀመር መሰናዶ እያደረገ ይገኛል፡፡ ዜናዎቹ መንግሥት ለሕዝብ እንዲደርሱለት የሚሻቸው ቁልፍ መልዕክቶችን ያዘሉ እንደሚሆኑና ኾኖም የአቀራረብ ፎርማታቸው ቃና በመረጠው መንገድ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡

ከቃና የቴሌቪዥን ጣቢያ የተገኙ ምንጮች በበኩላቸው ዜና የማቅረቡ ሐሳብ በመንግሥት ግፊት የመጣ ሳይሆን ቀድሞም በጣቢያው ባለቤቶች የተጠነሰሰ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የመንግሥት ጫና እንዳለበት የሚናገሩ ምንጮች በበኩላቸው እንደማስረጃ የሚያቀርቡት ጣቢያው የቪዲዮ ክምችት (footage) ከዋናው የኢቢሲና የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በነጻ እንደልብ እንዲያገኝ ሁኔታዎች እንደተመቻቹለት በመጥቀስ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ዜጎች በተለይም ወጣቶች ለዋናው ብሔራዊ ጣቢያ ጆሮና ዐይናቸውን መንፈጋቸው ሳያሳስበው አልቀረም፡፡ የተመልካች ፍልሰቱን ለማቆምም የተለያዩ አማራጮችን ለመከተል እየተገደደ ነው፡፡ በኢቢሲ አምሳል የሚፈጠሩ አዳዲስ ጣቢያዎች እንዲከፈቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ፍላጎት እንደሆነ ከዚህ ቀደም ዋዜማ መዘገቧ ይታወሳል፡፡

በግንቦት ወር መጨረሻ (ምናልባትም ግንቦት 20) የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቴሌቪዥን ጣቢያውን በተሻለ ፎርማትና አቀራረብ ለማስጀመርና ለማስመረቅ ርብርብ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በዋና መሥሪያ ቤቱ በሚገኘው ሕንጻ 11ኛ ፎቅ ላይ ዘመናዊ የቴሌቪዥን ስቱዲዮ አስገንብቶ ያጠናቀቀ ሲሆን የሶኒ ኤሌክትሮኒክስ የስቱዲዮ ቁሳቁሶችን አቅርቦለታል፡፡

የሰው ኃይል ምልመላውንም በአሁኑ ሰዓት ከሞላ ጎደል እያገባደደ ይገኛል፡፡ የተሻለ አቅም አላቸው ተብለው የሚታመኑ ወጣቶችም ከዋናው የኢቢሲ ጣቢያ እየኮበለሉ ወደ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በመሄድ ላይ መሆናቸው በሁለቱ ጣቢያዎች መካከል በኃላፊዎች ደረጃ ለመነጋገር እንዳስገደዳቸው ይነገራል፡፡

ከነዚህ ጣቢያዎች በተጓዳኝ የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል የራሱን ቴሌቪዥን ጣቢያ በሙሉ ኃይል ለመጀመር የዉስጥ አደረጃጀቱን እያስተካከለ ሲሆን ጣቢያው በዋናነት በልማታዊ ዘጋቢ ፊልሞች ላይ ትኩረት አድርጎ ለመሥራት ፍላጎት አለው፡፡ የሙከራ ስርጭቱን ከጀማመረ ሰነባብቷል፡፡

ከነዚህ ጣቢያዎች ባሻገር በርካታ ባለሐብቶችንና ታዋቂ ግለሰቦችን በማሰባሰብ ኢትዮጵያን ሬኔሳንስ ቲቪ (ERT) በሚል መጠርያ የ24 ሰዓት የዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ጣቢያ በመመስረት ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ የሪፖርተር ጋዜጣ መሥራችና ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ እንደሚመሩት የተነገረለት ይህ የሳተላይት ጣቢያ መቀመጫውን አሜሪካ አድርጎ የሚንቀሳቀስ የሳተላይት ጣቢያ ይሆናል ተብሏል፡፡ የወኪል ቢሮውን በአትሌት ገብረእግዚአብሔር ባለቤትነት በተያዘውና ቦሌ ከቀነኒሳ ሆቴል ጎን  በሚገኘው የአውሎ ሕንጻ ላይ መልክ እያስያዘ ይገኛል፡፡ አትሌቱን ጨምሮ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴን፣ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱንና ሌሎች ከ20 በላይ ታዋቂ ባለሐብቶችን በባለቤትነት እንደያዘም ተነግሯል፡፡

መንግሥት የመረጃ ፍሰቱን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመቆጣጠር ካለው ፍላጎት የተነሳ የብሮድካስትም ሆነ የኅትመት ሚዲያዎችን ፍቃድ ወደ ግል ተቋማት ሲያስተላልፍ ሚዲያው አፍራሽ ሚናን ሊጫወቱ ይችላሉ በሚላቸው  ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች  እጅ እንዳይወድቅ ከፍተኛ ጥንቃቄን ያደርጋል፡፡

እንደምሳሌ አፍሮ ኤፍ ኤም 105.3 ሬዲዮ ጣቢያ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ ሲቋቋም የግል ሬዲዮ ጣቢያ እንደሆነ ተገልጾ የነበረ ሲሆን አሁን በባለቤትነት ትልቁን ድርሻ የያዘው ግን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ብሥራት ኤፍ ኤምና አባይ ኤፍ ኤምን ጨምሮ አሁን ወደ ገበያ ለመግባት የመጨረሻ መሰናዶ እያደረጉ የሚገኙ ሦስት ኤፍ ኤም ጣቢያዎችን መንግሥት በእጅ አዙር ቁጥጥር እንደሚያደርግባቸው ይታወቃል፡፡

በሺ ዘጠኝ መቶ አምሳ ሰባት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ምሥረታ አስመልክቶ ሥርጭት የጀመረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት በጥቁርና ነጭ ቀለም ለ20 ዓመታት ዝግጅቶቹን ያቀረበ ሲሆን 10ኛው የአብዮት በዓልና የኢሠፓ ምሥረታ ምክንያት በማድረግ በ1976 ባለቀለም ሥርጭቱን እንደጀመረ ይነገራል፡፡ በ20 ኢትዮጵያዊያንና በ5 እንግሊዛዊያን ጥምረት ሥርጭት የጀመረው አንጋፋው ኢቴቪ/ኢቢሲ በአሁኑ ሰዓት የሬዲዮ ዘርፉን ጨምሮ ከ2ሺ በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡