ዋዜማ ራዲዮ-በጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በማይካድራ፣ ሁመራ፣ አብደራፊ፣ አብርሃጅራ እና ዳንሻ ከተሞች እጅግ የከፉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸሙንና ህጻናትን ጨምሮ 1,100 በላይ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) የምርመራ ሪፖርት ይፋ አደረገ።

ተቋሙ ይህን ያለው ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም በወቅቱ ስልጣን ላይ በነበረው የትግራይ ክልል አስተዳደር እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ፣ በትግራይ ክልል፣ ምዕራባዊ ዞን፣ ማይካድራ ከተማ እና አካባቢው ላይ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም የተፈጸመውን ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ለመለየት የምርመራ ሪፖርት ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

በጭካኔ ከተገደሉት በተጨማሪ ከ122 በላይ ሰዎች የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ስለመሆኑና ከ20 በላይ ሴቶች ደግሞ በቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ኢሰመጉ ረቡዕ ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓም በምስል የተደገፈውንና የመጨረሻ ያለውን ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን በዚህም በማይካድራ፣በሁመራ እንዲሁም በዳንሻ ከተሞች የትግራይ ተወላጆች እየተለዩ መሳሪያ እንዲታጠቁና የመሳሪያ አጠቃቀም ስልጠና እንዲወስዱ ይደረግ እንደነበር በተለይ በዳንሻ ከተማ በነሐሴ 2012ዓ.ም እና በጥቅምት 2013 ዓ.ም ስልጠና የተሰጣቸው መሆኑን መረጃ ስለማግኘቱም አመለክቷል፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ባለሃብቶች ለዚህ ጭፍጨፋ የሚውል የጦር መሳሪያና ሌሎች ቁሳቁሶችን ያከፋፍሉ እንደነበር በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ባለ 42 ገጽ ሪፖርቱ እንደሚያመላክተው ምንም እንኳ የሰብዓዊ መብቶችን የማክበር እና በሌሎች አካላትም እንዳይጣሱ የመከላከል እንዲሁም የመጠበቅ ሃላፊነት በሰላም ጊዜ ብቻ ሳይሆን በግጭት ወቅትም ተግባራዊ መደረግ ያለበት ግዴታ ሆኖ ሳለ መንግስት ይህን ግዴታውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻሉ ሰላማዊ ዜጎች ላይ አሰቃቂ የሆኑ የመብት ጥሰቶች ሊፈጸሙ ችለዋል፡፡

በዚህም የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መጠን እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ የኢሰመጉ የመስክ ምርመራ ዐቅም እና በአካባቢው የነበረው የጸጥታ ሁኔታ በፈቀደው ልክ በዋናነት መሠረታዊ የሚባሉትን የመብት ጥሰቶች ብቻ እንዳካተተ ገልጿል፡፡

ጥቃቱ ከመከሰቱ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በማይካድራ ከተማና በዙሪያው የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን መታወቂያ ልንሰጣችሁ ነው በማለት እንዲመዘገቡ በማድረግ እና በየቦታው እየተንቀሳቀሱ የማጣራት ስራ የተሰራ ሲሆን በዚህም ወቅትም የሰዎቹን ብሄር እየለዩ የመመዝገብ ስራ ሲሰሩ እንደነበር ለማወቅ እንደቻለ ሪፖርቱ አብራርቷል።፡፡

ተቋሙ ልዩ ዘገባ በሚል ያወጣው ሪፖርት የኢሰመጉ የሰብዓዊ መብቶች ምርመራ ባለሙያዎች ከህዳር 24 – ታህሳስ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በማይካድራ፣ ሁመራ፣ አብደራፊ፣ አብርሃጅራ፣ ዳንሻ እና ጎንደር አካባቢዎች ለመስክ ምርመራ ሥራ በተሰማሩበት ወቅት ባደረጉት ምልከታ፣ ባሰባሰቡት የድምጽ፣ የፎቶ እና የቪዲዮ መረጃና ማስረጃዎች መሠረት እንደሆነ አስታውቋል፡፡

የኢሰመጉ የምርመራ ቡድን በተጠቀሱት አካባቢዎች ተዘዋውሮ የሟች ቤተሰቦችን፣ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን፣ የዓይን ምስክሮችን፣ የቀብር ስርዓቶችን ያከናወኑ ሰዎችንና የቤተ-ክርስትያን አባቶችን፣ በጊዜያዊነት የተቋቋሙ የመንግሥት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችንና ሌሎችም የመረጃ ምንጮችን ተጠቅሞ ልዩ ልዩ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ሪፖርቱን እንዳጠናቀረው አመላክቷል፡፡

የኢሰመጉ የምርመራ ቡድን በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ እና ከቤተ-ክርስቲያን ቅጥር ውጪ የሚገኙ የጅምላ መቃብሮችን ተዘዋውሮ የጎበኘ ሲሆን፤ በወቅቱ ያልተነሱ እና የቀብር ስርዓት ያልተፈጸመላቸው አስከሬኖችን ጭምር ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የማይካድራውን ጥቃት ተከትሎ በ ህዳር 2013 ዓም ይፋ ባደረገው የማይካድራ የምርመራ ሪፖርት በዚሁ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 600 ሰዎች መገደላቸውንና ቁጥሩም ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል አስታውቆ ነበር፡፡  

በተመሳሳይ በታህሳስ 2013 ዓ.ም በማይካድራ የተፈጠመውን ጭፍጨፋ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በማይካድራ በባህርዳር፣ ጎንደር፣ ዳንሻ፣ ሁመራና ማይካድራ ከተሞች የመጀመሪያውን ዙር የመስክ ምልከታ አድርጎ ከ 700 በላይ  ሰዎች በአሰቃቂ መንገድ ተገድለው ስለመገኘታቸው መግለጹ ይታወሳል፡፡

ከ40ሽ እስከ 45ሽህ የሚገመቱ ሰዎች እንደሚኖሩባት በሪፖርቱ የተነገረላት ማይካድራ በመልክዓምድራዊ አቀማመጧ በምዕራብ ዞን ቃፍታ ሁመራ ወረዳ በጎንደር ሁመራ መንገድ ላይ የምትገኝ ሲሆን ከሁመራ በስተደቡብ ከ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አብድራፊ በሚባል ከሚታወቀው ከምድረ ገነት ከተማ ደግሞ በሰሜን አቅጣጫ በ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኝ ለሱዳን ድንበርም በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት። [ዋዜማ ራዲዮ]