PHOTO Credit -CaptureAddis

ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል መንግስት ዋና ከተማ፣ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እና የአለም አቀፍ ተቋማት መናኸሪያ የሆነችውን አዲስ አበባ ከተማን የሚዘክር የፎቶግራፍ ውድድር እና አውደርዕይ (ኤግዚቢሽን) ተዘጋጀ፡፡


“ሌላ ቀለም” የግል ማህበር ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ጋር በመተባበር የከተማዋ ገጽታ የሚያሳይ “አዲስን እናንሳ” በእንግሊዝኛው (Capture Addis) የተሰኘ ለ7 ቀናት የሚቆይ የፎቶ ውድድር እና ኤግዚቢሽን ያዘጋጀ ሲሆን የፎቶ ኤግዚቢሽኑ ከጥቅምት 15 እስከ 21/2012ዓ.ም ተካሂዶ ጥቅምት 22 በደማቅ ሁኔታ የመዝጊያ ስነስርአት የሚደረግ መሆኑን የፕሮግራሙ አዘጋጀች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡


የፎቶግራፍ ውድድሩ በሶስት ምድቦች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን የመጀመሪው ምድብ በፎቶግራፍ ባለሙያዎች አማካኝት የተነሱ ፎቶዎችን የሚያካትት ሲሆን ሁለተኛው ምድብ ደግሞ ማንኛውም የከተማው ነዋሪ በአጋጣሚዎች ያነሳቸውን ፎቶዎች በመላክ የሚወዳደርበት ነው፤ በሶስተኛው ምድብ የተካተቱት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የሚሳተፉበት ሲሆን ፤ የውጪ ዜጎች በራሳቸው እይታ ግርምትን ፈጥሮባቸው በካሜራቸው ያስቀሯቸውን ፎቶ ግራፎች በመላክ የሚወዳደሩበት መሆኑ ታውቋል፡፡


150 የተመረጡ ፎቶዎች የሚቀርቡበት የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽኑ የሚካሄደው በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር (ማዘጋጃ ቤት) ሲሆን ዝግጅቱን እዚያ የተደረገበት ምክንያት ሰዎች ለበርካታ አመታት ለከተማ መስተዳድሩ ያላቸውን አሉታዊ አመለካከት ተቀይሮ ከተማውም ሆነ ማዘጋጃ ቤቱ የእነሱ እንደሆኑ እንዲረዱ እንደሆነ አዘጋጆቹ ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡


ለሰባት ቀናት የሚቆየው የፎቶ ኤግቢሽን ሲጠናቀቅ በሸራተን አዲስ 500 ታዳዎች በሚገኙበት የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ በየምድቡ ከተላኩ ፎቶግራፎች ውስጥ አሸናፊ ለሆኑት የክብር እንግዶች በተገኙበት ሽልማት የሚበረከት ሲሆን በታዋቂው ሙዚቀኛ ሳሙኤል ይርጋ ሙዚቃ የሚቀርብ ይሆናል፡፡


www.captureaddis.com በተሰኘው ድረገጽ ላይ የፎቶ ኤግዚቢሽኑን የተመለከቱ መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉ ሲሆን በተጨማሪም በዚሁ ድረገጽ አማካኝት ፎቶ ግራፎችን መላክ ይችላሉ ተብሏል፡፡