Mamo Mihretu, Governor, National Bank of Ethiopia

ማሞ ምህረቱ ባለፉት አራት አመታት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውሳኔዎች ላይ በማማከርና ፖሊሲ በማዘጋጀት ቁልፍ ሚና ነበራቸው። አሁን የብሔራዊ ባንኩ ገዢ ሆነው ተሹመዋል። የዋጋ ግሸበት፣ የገንዘብ ፖሊሲ፣ የውጪ ዕዳ እና በቀጣይ ይኖራል የተባለው የውጪ ባንኮች ፉክክር የአዲሱ ተሿሚ የቤት ስራዎች ናቸው። ዋዜማ ጉዳዩን በዝርዝር ተመልክታለች፣ አንብቡት

ዋዜማ- መንግስት በ100 ቢሊየን ብር ያቋቋመውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን ከመምራት ተነስተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክን በገዥነት እንዲመሩ በቅርቡ የተሾመት አቶ ማሞ ምህረቱ ዛሬ በኢትዮጵያ ካሉ የባንክ :የኢንሹራንስ እና ሌሎች ፋይናንስ ነክ ተቋማትን ከሚመሩ ሀላፊዎች ጋር ትውውቅና ውይይትን ያደርጋሉ።

ውይይቱም በሀገሪቱ ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩርም ተሰምቷል። ይናገር ደሴን(ፒኤችዲ) ተክተው ለብሔራዊ ባንኩ ገዥ የሆኑት ማሞ ምህረቱ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ አንስቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪና የተለያዩ ተቋማትን በቦርድ አባልነት ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል።

ለብሄራዊ ባንክ ገዥነት ከተሾሙ በኋላ ከተቋሙ አመራር አባላት ጋር ባደረጉት የትውውቅ ውይይት ላይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በተለይም የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ላይ ዋና ትኩረታቸው አድርገው እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ዋዜማ ሰምታለች።

ብሄራዊ ባንክ ሀገሪቱን በገንዘብ ፖሊሲ የሚመራ እንደመሆኑ ይናገር ደሴ(ፒኤችዲ) ብሔራዊ ባንኩን በመሩባቸው ጊዜያት ዋጋ ንረት ፈጣሪ የሆኑ ፖሊሲዎችን ተግብሯል በሚል ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል። 

ከ2012 አ.ም ጥቅምት ወር አንስቶ የወጪ ንግድን ለማሳደግ እና የኢትዮጵያ ብር ትክክለኛ ዋጋውን ያግኝ በሚል ከንግድ ሸሪክ ሀገራት አንጻር የብር የምንዛሬ ተመኑ እንዲዳከም መደረጉ የገቢ ምርቶችን በማስወደድ ከባድ የዋጋ ንረት እንደፈጠረ ይታመናል።  ኢትዮጵያ ይህን አይነት የምንዛሬ ፖሊሲን መተግበር ከጀመረች በኋላ የዋጋ ንረት ያለማቋረጥ ጨምሮ ከ30 በመቶ በላይ ሆኖ ከዓመት በላይ ቆይቷል።

የአብይ መንግስት ከመጣ የአንድ የአሜሪካ ዶላርን በይፋዊ ገበያ ለመግዛት የሚጠየቀው የኢትዮጵያ ብር በእጥፍ ከ27 ብር ወደ 54 ብር ጨምሯል። ነገር ግን የምንዛሬ ፖሊሲው የዋጋ ንረት ከመፍጠር ባለፈም በይፋዊ ገበያ እና ትይዩ ገበያ መካከል ያለውን የምንዛሬ ዋጋ ልዩነትንም ለማጥበብ የተቀመጠለትን አላማ ማሳካት አልተቻለም። የጥቁር ገበያ የአንድ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ አሁን ድረስ የይፋዊ ገበያውን በ50 ብር ብልጫ አለው።

ከምንዛሬ ፖሊሲ አንጻር ማሞ ምህረቱ በብሄራዊ ባንክ ገዥነታቸው የተለየ አካሄድን ይከተላሉ ተብሎ አይጠበቅም።  ምናልባትም የምንዛሬ ተመን ሙሉ በሙሉ ለገበያ የሚተወውም በሳቸው የብሔራዊ ባንክ ገዥነት ጊዜ እንደሚሆንም ጠቋሚ ምልክቶች አሉ። 

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ፒኤችዲ) ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሪፖርተር እንግሊዝኛው ህትመት ላይ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የሁለተኛው ” የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ “መርሀ ግብር ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ዋና ትኩረት የምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረግ ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ያላት የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለሶስት ሳምንታት የገቢ እቃዎች ብቻ  የሚበቃ እንደሆነ በሚነገርበት በዚህ ጊዜ የምንዛሬ ተመንን ለገበያ መተው የውጭ ምንዛሬ ዋጋን በማስወደድ ተጨማሪ የዋጋ ንረት ፈጣሪ እንዳይሆን የተክለያዩ ባለሙያዎች ምክረ ሀሳባቸውን ለመንግስት ሲያቀርቡ ቆይተዋል።  የምንዛሬ ተመን ጉዳይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የደቀነውን ከባድ ፈተና ማሞ ምህረቱ እንዴት ይወጡታል የሚለው የአዲሱ ተሿሚ የቤት ስራ ነው።

በሌላ በኩል አዲሱ የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ በገንዘብ ፖሊሲ በኩል የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ባለፈው አመት በስፋት የታየው የብር ህትመት ላይ እርምጃን እንዲወስዱ ይጠበቃል። ካለፈው አመት መጀመርያ አንስቶ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ የፌዴራል መንግስት ከብሄራዊ ባንክ የተበደረው ገንዘብ ከ200 ቢሊየን በላይ ብር መበደሩን መረጃዎች ያሳያሉ። 

መንግስት ከብሄራዊ ባንክ ብድርን ወሰደ ማለት ብሄራዊ ባንክ እንደ ሌሎች ባንኮች ቁጠባን ስለማይሰበስብ የብር ህትመትን ያባብሳል ተብሎ ይታመናል። መንግስት ከብሄራዊ ባንክ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ለመበደር የተገደደው በጦርነት ሳቢያ በቂ ግብር ባለመሰብሰቡ እና የውጭ ዕርዳታ እና ብድር ላይ የታየው ከፍተኛ መቀዛቀዝ የበጀት ጉድለትን የማሟያ መንገድ በመታጣቱ ነው። 

የብር ህትመቱ የዋጋ ንረት ስጋትን ሲፈጥርም በዚህ አመት መጀመርያ ላይ ንግድ ባንኮች ከሚያበድሩት ገንዘብ ላይ 20 በመቶውን ከብሄራዊ ባንክ ቦንድ እንዲገዙ ታዘዋል። አዲሱ የብሄራዊ ባንክ ገዥ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርም ይህን መሰል ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ላይ ሊያተኩሩ ይችላሉ። 

የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለል ከአለም አቀፍ አበደሪዎች ሲጠበቅ የነበረው እና በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ እና በሌሎች ምክንያቶች እስካሁን ሊሳካ ያልቻለው እዳን ማሸጋሸግ እና ተጨማሪ ብድር የማግኘት ነገርም ሌላው ጉዳይ ነው።ኢትዮጵያ ጊዜው የተጠናቀቀው የመጀመርያው “የሀገር በቀል”ኢኮኖሚ ማሻሻያን መተግበር ስትጀምር ከአለም ባንክ ; አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ሌሎች አበዳሪዎች 10 ቢሊየን ዶላር ብድር ይቀርብልሻል ተብላ ነበር። ሆኖም የሰሜኑ ጦርነት የቆየባቸው ሁለት አመታት ብድሩ እንዳይገኝ አድርጓል። 

የቻይና ብድር መጠን ይገለጽልን በሚልም አበዳሪዎች የኢትዮጵያን የእዳ ሽግሽግ አዘግይተውታል።የኢትዮጵያ የውጭ እዳ 27 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር አካባቢ ነው። የመክፈያ ጊዜን የማራዘሙ ነገርም እስካሁን ተንጠልጥሎ ያለ ጉዳይ ሲሆን የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አዲስ ፕሮግራምን በኢትዮጵያ የሚያስጀምሩበት ድርድር ደግሞ ገና ጊዜ የሚወስድ ሆኗል። 

በዛሬው መድረክም እነዚህን ነጥቦች ጨምሮ የውጭ ውድድር በቅርቡ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ መወያያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። [ዋዜማ]