Ethiopia Delegation Jan 13/2020- Photo Fitsum Arega
  • የአፍሪቃ ህብረት አደራዳሪ እንዲሆን በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት አለ

ዋዜማ ራዲዮ- የሕዳሴው ግድብ ውዝግብ በተካረረበት በዚህ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ሀገራቱን ለማስማማት አዲስ የስምምነት ስነድ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላት ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
የዓለም ባንክና ዩናይትድ ስቴትስ ላለፉት ሁለት ወራት በታዛቢነት ሲከታተሉት የነበረው የሕዳሴው ግድብ ውዝግብ ሊፈታ ባለመቻሉ የየሀገራቱ ባለስልጣናት ዋሽንግተን ላይ ለውይይት ታድመዋል።
የዋሽንግተኑ ስብሰባ ዓላማ እስካሁን የተደረጉ አራት ስብሰባዎችን ውጤት ለመነጋገር ቢሆንም በአሜሪካ በኩል ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮችን የሚፈቱበትን መንገድ ያካተተ አዲስ የስምምነት ሰነድ ሀገራቱ እንዲፈርሙና ድርድሩ እንዲቀጥል የሚል ፍላጎት አላት።

የድርድሩን ጊዜ ማራዘም የሚል ሀሳብም አማራጭ አንደሆነ ስምተናል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሀ አሞላል እንዲሁም በግድቡ የላይኛውና የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ድርቅ ቢከሰት እንዴት መቋቋም ይቻላል በሚለው ላይ በኢትዮጵያ ; ግብጽና ሱዳን በካይሮና በካርቱም አንድ አንድ ጊዜ እንዲሁም በአዲስ አበባ ደግሞ ሁለት ጊዜ በውሀ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው እየተመሩ ያደረጉት የቴክኒክ ስብሰባ ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ይታወቃል። በአሜሪካ ጠሪነት በተጀመረው ይህ ስብሰባ ተጨማሪ ሁለት የዋሽንግተን ስብሰባዎችም ይደረጉበታል የሚል ስምምነት የነበረው ነው። አለም ባንክና አሜሪካም የውይይቱ ታዛቢ እንደሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል። በዋሽንግተን የሚደጉት ሁለት ስብሰባዎች የቴክኒክ ሳይሆኑ በሶስቱ ሀገራት የሚደረጉ ውይይቶች ሪፖርት ይቀርብበታል የተባለ ሲሆን አንዱ የዋሽንግተን ስብሰባ ታህሳስ ወር ተካሂዷል።ሁለተኛው የዋሽንግተን ስብሰባም ዛሬ ይጀመራል።ይህ ስብሰባ አራቱ ቴክኒካዊ ስብሰባዎች ከምን እንደደረሱ ለመነጋገር እንጂ ቴክኒካዊ እንዳልሆነ ተሰምቷል።


አሜሪካ ግን በዚህኛው የዋሽንግተን የህዳሴው ግድብ ስብሰባ ላይ ስምምነት የማፈራረም ፍላጎት እንዳላት ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች። አራተኛው የቴክኒክ ስብሰባ እንደተጠናቀቀም የአሜሪካ ባለ ስልጣናት ሶስቱም ሀገራት የህግ ሙያተኞች የተካተቱበት አስር አስር አባላት ያሉት የልኡክ ቡድን እንዲልኩ መልእክት ልከዋል።


ሆኖም ከኢትዮጵያ በኩል ስድስት አባላትን ያካተተ የልኡክ ቡድን ወደ ዋሽንግተን አቅንቷል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ገዱ እንዳርጋቸውና አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ ፣ የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ(ዶ /ር ኢ/ር) ፣ የሚኒስትሩ የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች አማካሪ ጌድዮን አስፋው ፣ የአለማቀፍ የውሀ ጉዳዮች ህግ የግል አማካሪ እምሩ ታምራት እንዲሁም የውሀ ፍሰት ሞዴሊንግ ባለሙያው አቶ በለጠ ናቸው ወደ ዋሽንግተን ከኢትዮጵያ በኩል ያቀኑት።

ግብጽ አራቱ የቴክኒክ ስብሰባዎች ተጠናቀው አሜሪካና አለም ባንክ አደራዳሪ እንዲሆኑ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት። አራቱ ስብሰባዎች ያለ ስኬት እንዲጠናቀቁም ተቀባይነት የሌላቸውን ሀሳቦች ስታቀርብ ቆይታለች።በተለይም አዲስ አበባ በተደረገው የመጨረሻ የቴክኒክ ስብሰባ ላይ የህዳሴው ግድብ ከ12 እስከ 21 አመት በሚሆን ጊዜ ውሀ ይሞላ የሚል ሀሳብ ማቅረቧ ስብሰባዎቹ እንዳይሳኩ ለመፈለጓ ዋነኛ ማሳያ ነው።

አሜሪካና የአለም ባንክ በአራቱ የቴክኒክ ስብሰባዎች ወቅት ለስሙ ታዛቢ ብቻ ናቸው ቢባልም በካርቱምና በአዲስ አበባ በተደረጉት ስብሰባዎች ላይ ሙሉ ለሙሉ አደራዳሪ ሆነው ሲሰሩ እንደነበር ዋዜማ ራዲዮ አረጋግጣለች።

እርግጥ የሶስቱ ሀገራት የህዳሴው ግድብ የውሀ አሞላል ስምምነት ጥር 6 2012 አ.ም እንዲጠናቀቅ ነው ከወራት በፊት በዋሽንግተን የተስማሙት።ይህ የሚሆነው ግን በአራቱ ቴክኒካዊ ስብሰባዎች ላይ ከተስማሙ ነው።በአራቱ የቴክኒክ ስብሰባዎች ላይ በህዳሴው ግድብ ውሀ አሞላል ላይ ከስምምነት ካልተደረሰ በዋሽንግተኑ ስብሰባ ሪፖርት የሚደረግ እንጂ ከስምምነት እንዲደረስበት የሚቀመጥ አጀንዳ አይኖርም።

ሶስቱ ሀገራት በአራቱ የቴክኒክ ስብሰባዎች ላይ ካልተስማሙ በ2007 አ.ም በካርቱም የተፈራረሙት የመርህ ስምምነት አንቀጽ አስርን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ነው በዋሽንግተኑ የመጀመርያ ስብሰባ ላይ የጋራ መግለጫ ያወጡት። አንቀጽ 10 ደግሞ የሶስቱ ሀገራት የውሀ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የቴክኒክ ቡድን አባላት በህዳሴው ግድብ ውሀ አሞላል ላይ በአራቱ ስብሰባዎች ካልተግባቡ ጉዳዩን ለየሀገራቱ መሪዎች እንዲያቀርቡ ካልሆነም አሸማጋይ እንዲያስገቡ አማራጭ የሚያቀርብ አንቀጽ ነው።

ስለዚህ የዋሽንግተኑ ስብሰባ ለአሜሪካው የገንዘብ ሚኒስት ስቴፈን ሙኒሽን እና ለአለም ባንኩ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ ስለ አራቱ ስብሰባ ሂደት መረጃ መስጠት እንጂ በሌላ ቴክኒካዊ ጉዳዮ ላይ ለመደራደርም ሆነ ለመፈራረም ያለመ እንደማይሆን ሲጠበቅ ነበር።

ነገር ግን በ2007 አ.ምቱ የመርህ ስምምነት አንቀጽ 10 አተገባበር ምርጫ ላይ በኢትዮጵያ በኩል ግራ መጋባት ታይቷል። አራተኛው የቴክኒክ ስብሰባ ባለፈው ሳምንት ሀሙስ ያለ ስምምነት ሲጠናቀቅ የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ ” በኢትዮጵያ በኩል አንቀጽ 10 ላይ ካለው አማራጭ ጉዳዩ ለየሀገራቱ መሪዎች ተልኮ የሶስቱ ሀገራት መሪዎች ይነጋገሩበት የሚለው ነው ተመራጭ ፤ ለኢትዮጵያም የሚጠቅመውም መሪዎቹ ቢነጋገሩ ነው” ሲሉ በመግለጫቸው ጠቁመው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በደቡብ አፍሪካ ባደረጉት ጉብኝት ከፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ግን ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር በህዳሴው ግድብ የገባችበት ውዝግብ እንዲፈታ ደቡብ አፍሪካ እንድታሸማግል ጥያቄ አቅርበው ደቡብ አፍሪካም ጥያቄውን እንደተቀበለች ተሰምቷል። በአንድ በኩል ሶስተኛ ሀገርን በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ማስገባት ተገቢ እንዳልሆነ አቋም ተይዟል ተብሎ በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዋሽንግተኑም ስብሰባ ሳይጀመር አሸማጋይ መጠየቃቸው ያልተጠበቀ ነበር።

ደቡብ አፍሪቃ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነትን ቦታ በቅርቡ ስለምትረከብ የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ ላይ የአፍሪቃ ህብረት እንዲገባ በኣኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮቻችን ነግረውናል። [ዋዜማ ራዲዮ]