Ali Birra

በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ አብሪ ኮከብ የነበረው አሊ ቢራ ዛሬ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓም በሞት ተለይቷል። አሊ ያለፉትን ወራት በፅኑ ታሞ በህክምና ሲረዳ ነበር። ይህን አንጋፋ የኦሮምኛ ሌሎች ቋንቋዎች ቋንቋ ድምፃዊ ዋዜማ እንዲህ ትዘክረዋለች

ዋዜማ- ወላጆቹ ያወጡለት አሊ መሐመድ ሙሳ ተረስቶ፣ አሊ ቢራ የሚለው የመድረክ ስሙ መታወቂያው ሆኗል፡፡ አሊ የዘመነኛው (contemporary) ኦሮምኛ ሙዚቃ አባት መሆኑ ፈጽሞ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው የኦሮምኛ ሙዚቃ አልበም የእሱ የአሊ ቢራ ነው። አሊ የኦሮሞ ሕዝብ የባህል፣ ታሪክ፣ የጥበብ መገለጫ ነው፤ የትውልድ መልካም አርአያ ጭምር። ለሀገራችን ሙዚቃ፣ ባህል እና ስነ ጥበብ ማንሰራራት፣ እድገትና መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። አንጋፋው ድምጻዊ አሊ ቢራ የእርሱን ፈለግ ለተከተሉ በርካታ ድምፃዊያን ፈር ቀዳጅ  አርአያና መምህር ሆኗል፡፡

“A Fifty Years Journey for the Love of Music and His People” ላይ አሊ “…የኦሮሞን ሙዚቃ ለዓለም ያስተዋወቀ፣ የኦሮሞን ህዝብ ብሔራዊ ማንነት ያነቃቃ፣ በስደት ያሉ የኦሮሞ ተወላጆች ከማንነታቸው ጋር እንዲተሳሰሩ መንገድ የቀየሰ…” የሚል ምስክርነት ተሠጥቶታል::  አሊ ቢራ… ከፖለቲካ ድርጅቶችም በላቀ መልኩ… ብቻውን ከ50 አመታት በላይ በሙዚቃው የኦሮሞ ሕዝብ መብት እንዲከበር… ያለ ክፍፍልና መለያየት ያስተባበረና ያነቃ ጀግና መሆኑን ገልጸው የሚያወድሱትም ጥቂት አይደሉም፡፡ በኦሮሞኛ ቋንቋ መናገር፣ ማስተማር፣ መገልገልን የተመለከተ ጭቆና ይደረግ በነበረ ዘመን አሊ ድርጊቱን ተቃውሞ… በሙዚቃው የሕዝቡ መብት ይከበር ዘንድ ድምጹን አሰምቷል፡፡ ቀድሞ “ኢትዮጵያ” በሚል ያዜመውን ዘፈን “ኦሮሚያ” በሚል ተክቶ ለማዜም የተገደደው ጭቆናው በመክፋቱ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ኢትዮጵያዊነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባበት ምክንያት ምን እንደነበር ተጠይቆ አሊ ምላሽ ሲሰጥ፡-

“…ለሕዝብ የማይቆም ሥርዓት እስካለ ሁልጊዜም እንቃወማለን፡፡ በተለይ በደርግ ጊዜ እኔ ከሀገር ስወጣ የነበረው በጣም አስፈሪና አስጊ፣ ሠው እንደ ትንኝ የሚቆጠርበት ወቅት ነበር፤ ታፍነናል ብለን ስለምናምን ሁኔታውን ነበር የምናንጸባርቀው፤ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ግን ደግሞ ኦሮሞ ነኝ። የነበረው ሥርዓት ግን ይሄን አይቀበለውም። በቋንቋችን ላይ የነበረው ጫና የበዛ ነበር። ከሌሎች በተለየ ኦሮሞ እና ኦሮምኛ ቋንቋ ላይ የተለየ ተፅዕኖ ነበር። ሥለዚህ በወቅቱ የነበረውን ነገር በመንቀፍ እዘፍን ነበር፤ ለሕዝብ የቆመ ሥርዓት፣ የተረጋጋ ሥርዓት እስኪመጣ ድረስ ሁልጊዜም ትግል ያስፈልጋልና ይሕንን አቋሜን ነው ያንጸባረቅኩት” በማለት የሙዚቃ ሥራዎቹ ከፖለቲካዊ መልዕክቶች ጋር ተሳስሮ የዘለቀበትን ሁናቴ አብራርቷል፡፡

አሊ መሐመድ ሙሳ (አሊ ቢራ) መስከረም 15 ቀን 1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ገንደቆሬ ነው የተወለደው። ገና የ3 አመት ጨቅላ ህፃን እያለ ቤተሰቦቹ በመለያየታቸው አብዛኛውን የልጅነት ህይወቱን ያሳለፈው በአባቱ ቤት ነበር፡፡ አሊ በልጅነቱ ከኦሮሚኛና አማርኛ በተጨማሪ አረብኛን ትምህርት ቤት ገብቶ ተምሯል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ድሬዳዋ ከተማ በቀድሞዎቹ መድረስ ጅዲዳ እና በልዑል ራስ መኮንን ት/ቤቶች፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ካቴድራል ት/ቤት ተከታትሏል። በኋላም ወደ ካሊፎርንያ በማምራት በሳንታ ሞኒካ ኮሌጅ በሙዚቃ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ትምህርት ተከታትሏል። አሊ ቢራ ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ እና ለቤተሰቦቹ በማንጎራጎር ነበር የሙዚቃ ህይወቱን የጀመረው።

ጅማሮ

አሊ ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረክ የተጫወተው “ቢራ ዳ በርሄ – Birraa dahaa Barihee” (ቢራ ዳ በሪኤ) የተባለውን እጅግ ተወዳጅ ዘፈኑን ነበር፡፡ ቤተሰቦቹ ያወጡለትን አሊ መሐመድ ሙሳ አስትቶ አሊ ቢራ የሚለውን ስም እንዲያገኝ ያስቻለውም ይሕ ዘፈን ነበር።  እ.ኤ.አ. በ1963 ዓ.ም. ለኢድ-አልፈጥር በዓል ከአፍራን ቀሎ ባንድ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ “Birraa dhaa Barihe” (ቢራ‘ዻ ናበሬ፤ በአማርኛ ትርጉሙ ደግሞ “ጎህ ሲቀድ” ወይም “የብራ መውጣት”) የሚለውን የመጀመሪያ የመድረክ ሥራውን አቀረበ፤ አምስት አሰርት ዓመታት የዘለቀው የሙዚቃ ሕይወቱ መጀመሪያም ሆነ፡፡ የኦሮሞን ሙዚቃ ለማስተዋወቅ ዓላማ አድርጎ ከተመሰረተው አፍረንቀሎ የሙዚቃ ቡድን ጋር ሲቀላቀል አሊ ዕድሜው ገና 13 ዓመት ነበር። ሶስት በአሊ ስም የሚጠሩ ታዳጊዎች በነበሩበት የአፍረንቀሎ የሙዚቃ እና የባህል ቡድን ውስጥ የያኔው ታዳጊ ከቀሪዎቹ አሊዎች እንዲለይ በማለት ነበር በዚሁ የመጀመሪያ ዜማው “አሊ ቢራ” የተባለውና በዚያው የቀጠለው፡፡ ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣን በያዘ በቀጣይ ዓመት በአፍራን ቀሎ አባላት ላይ በወሰደው የግድያና የእስራት ዘመቻ የቡድኑ አባላት ወደተለያዩ በታ ሲበታተኑ አሊ ወደ አዲስ አበባ ተሻገረ፡፡

ወደ አዲስ አበባ

አሊ ወደ አዲስ አበባ በመጣበት ወቅት ካሴት የሚባል አይታወቅም ነበር፡፡ የሙዚቃ ቀረጻ የሚከናወነው በሪል ቴፕ አለያ ደግሞ በሸክላ ነበር፡፡ አሊ ከካሴት በፊት በነዚህ መንገዶች የማስቀረጽ ፍላጎት ነበረው፡፡ አዲሳባ በርካታ ዘፈኖችን አዘጋጅቶ ቢጨርስም በጊዜው የሙዚቃ ኣሳታሚዎች የእሱን ኦሮምኛ ዘፈን ለመግዛት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው ታዳጊውን ድምጻዊ “የኦሮምኛ ዘፈን ማስቀረጽ ክልክል ነው” ብሎ እንዲያምን ስለገፋው የራሱን መፍትሔ አበጀ፡፡ እናም የራሱን ዘፈኖች በጊታር፣ በቶም ቶምና በከበሮ በማቀናበር፣ በሪል ቴፕ የተቀረጸ የአሮምኛ ዘፈኖችን ለሚያውቃቸው ሠዎች ብቻ እንዲያዳምጡ እጅ በእጅ ይሠጥ ነበር፡፡ ባለማሠልቸት በዚህ መልኩ ሲሰራ ቀጥሎ ከውጪ ሀገር የመጣ አንድ ሰው የአሊን ሙዚቃ ከኢትዮጵያ ውጪ ለማስቀረጽ ፍላጎት እንዳለው ገለጸለት፡፡ ይሄኔ አሊ ከስደት የተረፉ ጓደኞቹን ፍለጋ ወደ ድሬዳዋ ሄደ፡፡ በድሬዳዋም አሁን አውስትራሊያ ከሚገኘው የአፍረንቀሎ መስራች አሊ ሸቦና አብዲ ቡሂ ጋር በመሆን ከሠሯቸው አዳዲስ የኦሮምኛ ሙዚቃዎች ውስጥ ሁለቱ በዚሁ ከውጪ በመጣው ሠው አማካይነት በሸክላ ታትመው ወጡ፡፡ ሆኖም ግን የሸክላ ማጫወቻ በብዙ ሰው ቤት ባለመኖሩ ሙዚቃዎቹ ያን ያሕል ተደምጠዋል ማለት አይቻልም፡፡ በዚህ ሠበብ የተዘጋው በር ተከፈተና የዝነኞቹን አማርኛ ሙዚቃ ያሳትም የነበረው ፊሊፕስ ኩባንያ “አዋሽ” የተሰኘውን ጨምሮ የአሊ ቢራን ሁለት ዘፈኖች አሳተመለት፡፡ ከዚያ በኋላ የተለያዩ የአሊ ቢራ ሙዚቃዎች በካሴትና ሸክላ ታትመው ወጡ፡፡ “Hin Yaadin”፣ “Asabalee”፣ “Ammalelee”፣ እና “Gamachu”ን ለአድማጮች በማድረስ ዝናው የናኘ ለመሆን በቃ፡፡ አንጋፋው ደምጻዊ በአጠቃላይ 265 ዘፈኖችን የተጫወተ ይሁን እንጂ በሕይወት ዘመኑ ያሳተማቸው ሙሉ አልበሞች ግን ስድስት ብቻ ናቸው።

የአሊ ስራዎች አፋን ኦሮሞንና ሌሎች የዘፈነባቸውን ቋንቋዎች ለሚሰሙ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሙዚቃ አፍቃሪ ዘንድ እጅግ የሚወደዱ ትውልድና ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ናቸው፡፡ ሱዳንኛ፣ ሐረሪኛና አማርኛ ዘፈኖች የተቀላቀሉበት አልበም አውጥቷል፤ በነገራችን ላይ ስምንት ቋንቋዎችን አቀላጥፎ የሚናገረው አሊ በኦሮምኛ ብቻ ሳይሆን በአማርኛ፣ በአረብኛ፣ ሱዳኒኛ፣ በሐረሪ፣ እንግሊዝኛ፣ ስፓኒሽ፣ ስዋሒሊ እና በሱማሊኛ ቋንቋዎችም አዚሟል፡፡ ከአርባ በላይ ሀገራት በበርካታ በሆኑ መድረኮችም ላይ ተጫውቷል፡፡  አሊ ለራሱ እና ለሌሎች ድምፃውያን በርካታ ግጥም እና ዜማዎችን ደርሷል፡፡ የራሱን ልዩ የአዘፋፈን ዘዬ ፈጥሯል፡፡ በሀገራችን ታሪክ ታላላቅ ከሚባሉ የሙዚቃ ቡድኖችና አንጋፋ ድምጻውያን ጋር ሰርቷል፡፡ በሀገር ውስጥ እና በውጪም በዛ ባሉ መድረኮች ተጫውቷል፡፡ በርከት ያሉ ሽልማቶች አግኝቷል፡፡

ክቡር ዘበኛ

አሊ በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ተቀጥሮ ለሦሥት አመታት ሙዚቃን የተጫወተ ሲሆን፣ ፒያኖ፣ ጊታር እና ኡድ የመሳሰሉ መሳሪያዎችን ወጫወት የጀመረው በዚሁ ወቅት ነበር፡፡ ከክቡር ዘበኛ በኋላ አይቤክሥ ባንድን በመቀላቀል በአጠቃላይ ለስምንት አመታት ያሕል የሙዚቃ ሥራውን በዲ-አፍሪክ ሆቴል ሲያቀርብ ቆይቷል፤ በተለያዩ የምሽት ክለቦች ሠርቷል።

በ1985 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1976) ከሀገር አብሯት ከወጣው ስዊደናዊቷ ዲፕሎማት ብሪጊታ ጋር ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማምራት በጋብቻ አብረው ቆይተዋል፡፡ የሳዑዲ ቆይታው እምብዛም ሳይመቸው ሲቀር ወደ ስዊድን ተጉዞ ለሶስት ዓመት ከኖረ በኋላ በ1988 ወደ አሜሪካ በማቅናት በሎሳንጀለስ አርት አካዳሚ ሙዚቃን ተምሮ በ1990 ተመርቋል፡፡ ለከፍተኛ ዝና የበቃባቸውን ሁለት አልብሞች አከታትሎ ያወጣውም በ1992 ዓም ነበር፡፡

አሊ ትምህርትና ጥበብ የዕድገትና የስኬት መሰረቶች መሆናቸውን፣ አለመማር ሕሊናን እንደሚያሳውር በጽኑ ያምናል። ለአሊ ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ቤት የሚገኝና አእምሮን ብቻ የሚያሳትፍ ሂደት ሳይሆን፣ የሰው ልጅ እድሜ ልኩን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው የሚያካሂደውና ሁለመናን (አካልን፣ አእምሮን፣ መንፈስንና፣ ልቡናን) የሚያሳትፍ ሰፊና ረጅም ሂደት ነው።ይህን እምነቱን በዘፈኖቹ በማስተላለፍ ብዙዎችን ለትምህርት አነሳስቷል፣ ራሱም እምነቱን በተግባር በመኖር ምሳሌ ሆኗል። ከሶስት ዓመት በፊት የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓሉ ሲከበርም መሪ ቃሉ “Barnootaa ammas Barnootaal” (“መማር አሁንም መማር!”) እንዲሆን ያደረገውም በዚህ አቋሙ እንደሆነ ይታመናል፡፡

አሊ ቢራ ከ50 በላይ ዓመታት በዘለቀ የሙዚቃ ጉዞው ላስመዘገባቸው ስኬቶች ዋነኛው መሰረት ከአፍሪቃዎቹ፣ ከአድናቂዎቹና ከህዝብ የተደረገለት ድጋፍና እርዳታ መሆኑን ደጋግሞ ገልጿል። ምስጋናውን ያቀረበበት ዝግጀትም ከጥቂት ዐመታት በፊት በሀገረ ውስጥና በተለያዩ የምዕራባውያን ሀገራት ከተማዎች ተከናውኗል። ይሕም አሊ እምነቱን፣ ዕውቀቱን፣ እቅዱን፣ ተስፋውን፣ ራዕዩን በተለያዩ መድረኮች ለማካፈል ይዞት የመጣውን ችቦ ለሌሎች ያስተላፈበት መድረክ ጭምር እንደነበር ተገልጿል። የስመጥሩን ደምጻዊ 50ኛ ዓመት የሙዚቃ ክብረ በዓል አስተባባሪ ኮሚቴን ጄነራል ባጫ ደበሌ በአማካሪ ቦርድ ሊቀመንበርነት… እነ ውብሸት ወርቃለማሁ፣ ዳዊት ይፍሩ፣ ዳግማዊ አሊ፣ ታደለ ገመቹ፣ ዕቁባይ በርኼ፣ ጋዜጠኛ ኢቢራሂም ሀጂ አሊን የመሳሰሉት ደግሞ በአባልነት የተሳተፉበት ነበር፡፡ በወቅቱ በአዳማ ከተማ በተከናወነው ዝግጅት አሊ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የመኪና እና የመኖሪያ ቤት ስጦታ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንደተበረከተለት ተገልጿል፡፡  ከሽልማቱ አስቀድሞ ሠጥቶት በነበረ ቃለ ምልልስ አሊ “…እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቤትና መኪና አልነበረኝም፡፡ አሁን ናዝሬት ላይ በጣም ትንሽዬ ቤት አለን፡፡ ለእኔና ለባለቤቴ በቂ ናት፡፡ እንግዳ ቢመጣብን አንድ ክፍል አላት፤ ትበቃለች። መኪና ግን የለኝም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለብር ግድ ስለሌለኝ ነው፡፡ ብር የምበትን አባካኝ ባልሆንም እጄ ላይ ብር ካለ እስኪያልቅብኝ ድረስ ለሌለው ሰው እሰጣለሁ” በማለት ስለነበረበት ሁኔታ ገልጾ ነበር፡፡

ስብዓዊ ተግባራት

አሊ ቢራ ከአሁኗ ባለቤቱ ቢሊ ማርቆስ ቢራ ጋር በመሆን “ቢራ ቺልድረን ኢጁኬሽን ፈንድ” የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት አቋቁሞ ለህፃናት ትምህርት ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ “ቢራ ቺልድረን ኢጁኬሽን ፈንድ” ዓላማው ወላጅ ወይም ቤተሰብ የሌላቸውን ህፃናት መርዳት ነው፡፡ ድርጅቱ በድሬዳዋ አካባቢ ባሉ የገጠር ት/ቤቶች ላይ እየሰራ ሲሆን፣ በቀጣይነት በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የተጠናከረ ስራ ለመስራት እቅድ እንዳለው ተገልጿል፡፡ የፊሊፒንስ ዜግኀት ካላት ባለቤቱ ቢሊ ጋር ከተጋቡ 19 ዓመት እንዳለፋቸው የሚናገረው ድምጻዊው “እሷን ካገባሁ በኋላ ለሁሉ ነገር የምትበጀኝ ሆናለች፤ እግዚአብሔር ጥሩ ሚስት ሠጥቶኛል” ብሏል፡፡

መንፈሰ ጠንካራው አሊ በካንሰር ተጠቅተሀል ተብሎ ለረዥም ዓመታት የሕክምና ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ሙሉ በሙሉ ከካንሰር ነጻ መሆኑ ከሀኪሞች ተገልጾለታል፡፡ ይሕ ከሆነ ከአንድ ህመት በኋላ የቀኝ ዓይኑን ታሞ ለሕክምና ሆስፒታል ባመራበት ወቅት በጭንቅላቱ ውስጥ በበቀለ እጢ ምክንያት ሁለቱም ዓይኖቹ ሊጠፉ፣ በዚህ የተነሳም ሕይወቱ አደጋ ላይ መሆኑ ተገልጾለት ኦፕራሲዮን ማድረግ እንዳለበት ይገለጽለታል፡፡ ጭንቅላቱ ላይ ቀዶ ጥገና በተደረገለት ወቅት በተፈጠረ የሕክምና ስሕተት ግን የግራ አይኑ ሙሉ በሙሉ ማየት ሲያቆም የቀኙም እንደተዳከመ ተገልጿል።

አሊ ቢራ፣ በሙዚቃ ዓለም በቆየባቸው ዓመታት በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደር የሌለው የሕዝብ ፍቅርና አክብሮትን ተቀዳጅቷል፡፡ በሚሊዮኖች ሕሊና እና ልብ ውስጥም ልዩ ቦታ ይዟል፡፡ ለስኬቶቹና ለአስተዋጽኦዎቹ ዕውቅና ከሰጡ የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ተቋማት ከሃምሳ በላይ ሽልማቶችን ያገኘ ሲሆን፣ በ1995 በቶሮንቶ ካናዳ የአፍሪካ የምንግዜም ምርጥ አንጋፋ ሙዚቀኛን ሽልማት ተጎናጽፏል፡፡ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በ2003 የክብር ዶክትሬት ተበርክቶለታል። [ዋዜማ]