Dr.Birhanu Nega
Dr.Birhanu Nega
  • የአማራ ክልልን ተቃውሞ ለመግታት የመከላከያ ሰራዊት የሀይል አሰላለፉን አሸጋሸገ
  • በኦሮሚያ በቀጣዮቹ ቀናት የተጠናከረ ህዝባዊ አመፅ ዝግጅት እየተደረገ  ነው
  • የአሜሪካ ኤምባሲ የኢትዮዽያ ህዝቦች ማህበራዊ ትስስር (social fabric) እንዳይናጋ ሁሉም ወገኖች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል

 

ዋዜማ ራዲዮ-በአማራና ኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች ፀረ አገዛዝ የተቃውሞ ሰልፎች ቀጥለዋል። እስካሁን ከ 112 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ቢያንስ 5 የፀጥታ ሰራተኞች መገደላቸውን ያሰባሰብነው መረጃ ያመለክታል። በጎንደርና በአርሲ አቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች አዳዲስ ተቃውሞዎች የተቀሰቀሱ ሲሆን በባህር ዳር በፀጥታ ሀይሎች የተገደሉ ዜጎች የቀብር ስነስርዓትን ታኮ ያገረሸውን ተቃውሞ ለማስቆም ወታደሮች የከተማይቱን አንዳንድ አካባቢዎች በተኩስ ሲንጡ ውለዋል።

የአማራ ክልልን ተቃውሞ ለመግታት የመከላከያ ሰራዊት የሀይል አሰላለፉን ተቃውሞ ወደበረታባቸው አካባቢዎች ያሽጋሸገ ሲሆን ከክልሉ ፖሊስ አባላት ጋር አልፎ አልፎ አለመግባባት እየተከሰተ መሆኑንም ነዋሪዎች ተናግረዋል። መንግስት የበረታውን ተቃውሞ ለማብረድ ህዝባዊ ውይይቶችን ለማድረግ እየተዘጋጀ ቢሆንም በመንግስት የሀይል እርምጃ የተቆጣው የባህርዳርና የጎንደር ህዝብ ምንም አይነት ውይይት ለመድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑን እየገለፀ ይገኛል።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ በበኩላቸው የተቀረው የኢትዮዽያ ህዝብ አመፁን እንዲቀላቀል ጥሪ አቅርበዋል። ዶ/ር ብርሀኑ በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል አሁኑኑ ትብብር እንዲደረግ ጠይቀው፣ “ትብብር የማይኖር ከሆነ ሀገሪቱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ልታመራ ትችላለች” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች በበኩላቸው በቀጣዮቹ ቀናት የተጠናከረ ህዝባዊ አመፅ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን እየተናገሩ ነው። በኦሮሚያ መንግስት ከሚወስደው የሀይል እርምጃና ግድያ ባሻገር ተቃውሞው በትናንሽ ከተሞች እንደቀጠለ ነው።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በሰሞኑ ተቃውሞ ላይ ለዘብተኛ መግለጫ ያወጣ ሲሆን የኢትዮዽያ ህዝቦች ማህበራዊ ትስስር (social fabric) እንዳይናጋ ሁሉም ወገኖች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል። በኤምባሲው መግለጫ ለዘብተኝነት ላይ ትችት ያቀረቡ ወገኖችም አሉ። ከዋሽንግተን ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ግን የአሜሪካ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች ከጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘዋል።

በሀገሪቱ የተባባሰው አመፅ በሰልጣን ላይ ያለውን መንግስት ክፉኛ ከማስደንገጥ አልፎ መፍትሄ በማፈላለጉ በኩል ግራ በመጋባትና የሀይል እርምጃ በመውሰድ ላይ ብቻ እንዲያተኩር አድርጎታል። ገዥው ፓርቲ ሰፊ ግምገማ በማድረግ (ፓርቲው ከሶስት ሳምንት በኋላ ጉባዔ የማድረግ ዕቅድ አለው) ችግሮቼን አርማለሁ ቢልም የህዝቡ ቁጣና አመፅ ፓርቲውን ወደመሰነጣጠቅ ሊያመሩት ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን የሚገልፁ አሉ።