Photo credit Mail and Guardian

ዋዜማ ራዲዮ- ከድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዝ በትላንትናው እለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ተኛ የፀረ ሽብር እና የህገ-መንግስት ጉዳዩች ችሎት ቀርባ በተከሰሰችበት አንቀፅ ጥፋተኛ የተባለችው ላምሮት ከማል በ3 ወር እስራት ተፈረደባት

ተከሳሿ ከዚህ በፊት ተከሳ እንደማታውቅ፣ የልጅ አሳዳጊ መሆኗን እና ከምትኖርበት አካባቢ ሀዘንና ደስታ ላይ ተሳታፊ እንደሆነች የሚገልፅ 3 የቅጣት ማቅለያ እንዳቀረበች በችሎት የተነበበ ሲሆን አቃቤ ህግ በበኩሉ የቅጣት ማክበጃ ያቀረበሲሆን ድርጊቱ የተፈፀመው ለሊት እንደመሆኑ ሟች እርዳታዋን በሚፈልግበት ሰአት እርዳታ ስላላደረገች በቅጣት ማክበጃነት ይያዝልኝ ሲል አቅርቧል ።

የዋዜማ ሪፖርተር እንደዘገበችው ችሎቱም የአቃቤ ህግን የቅጣት ማክበጃ ምክንያታዊነቱን የሚገልፀ ስላልሆነ ውድቅ አድርጌዋለሁ ብሎ በሶስት ወር እስራት እንደትቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል።

በመቀጠልም ችሎቱ ተከሳሿ ላለፉት ዘጠኝ ወር ከአስራ አምስት ቀን በማረሚያ ቤት የቆየች ስለሆነና ከቅጣቷ በላይ ስለታሰረች በነፃ እንድትሰናበትና ተከሳሿ በዋስትና ያስያዘችው ንብረት ካለ ተመላሽ እንዲደረግላት ትእዛዝ ሰጥቷል

ተከሳሿ መስከረም 2 ቀን 2013 ከ ሶስት ተከሳሾች ጋር ክስ የተመሰረተባት ሲሆን በመዝገቡ ተከሰው የነበሩት 1ኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ በሽብር ክስ እድሜ ልክ ፅኑ እስራት፣ 2ኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹ በግድያ ተሳታፊ እና ገድሎ በመዝረፍ ወንጀል18 አመት እስራት እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ አብዲ አለማየሁ ለፖሊስ መረጃ ባለ መስጠት 6ወር ቀላል እስራት ሀምሌ 27 2013 ቀን እንደተፈረደባቸው ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]