ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ 14 የከረዩ ሚችሌ ገዳ አባላት በመንግስት የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በግዳጅ ወደ ጫካ ተወስደው መገደላቸውን እንዲሁም በዚሁ ወራዳ ሀሮ ቀርሳ ቀበሌ ኢፍቱ በተባለ ቦታ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት የ11 ፖሊስ አባላት ሕይወት ማለፉን አካሄድኩት ባለው የምርመራ ሪፖርት ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋ ባደረገገው ሪፖርት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በፖሊስ አባላትና በከረዩ ሚችሌ ገዳ አባላት ኅዳር 21 እና 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በተከታታይ ቀናት በተፈጸመ ጥቃት የሕይወትና የአካል ጉዳት መድረሱንና እንዳረጋገጠ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ አደጋውን ተከትሎ ከታኅሣሥ 7 እስከ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጠቀሰው ቦታ በመገኘትና ተጎጂዎችን፣ የአይን እማኞችን፣ የሟች ቤተሰቦችንና የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በማነጋገር ምርመራ ማካሄዱን አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ምርመራ እንደሚያሳየው ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ፈንታሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ለስራ ሄደው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አከባቢ ወደ መተሃራ ከተማ በመመለስ ላይ የነበሩ የፀጥታ አባላት ላይ በወረዳው ሀሮ ቀርሳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ኢፍቱ በተባለ ቦታ ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት የ11 ፖሊስ አባላት ሕይወት ማለፉንና ቢያንስ 17 ሌሎች የፖሊስ አባላት መቁሰላቸውን መዝግቧል።

የኮሚሽኑ ሪፖርት “ጥቃት ሲፈጽሙ የነበሩት “የኦነግ ሸኔ” አባላት ሲሆኑ ከመካከላቸው የማውቃቸው የአካባቢው ተወላጆች አሉበት፤ ታጣቂዎቹ በተኮሱት ጥይት ፖሊስ ሲወድቅ እልልታ ያሰሙ ነበር” ያሉ የአይን እማኞችን በዋቢነት አስቀምጧል፡፡

የፈንታሌ ወረዳ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል አንዱ ሲሆን በደቡብ ምሥራቅ በአርሲ ዞን፣ በደቡብ ምዕራብ በቦሰት ወረዳ፣ በሰሜን ምዕራብ በአማራ ክልል እንዲሁም በሰሜን ምሥራቅ በአፋር ክልል ይዋሰናል፡፡

ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በፖሊስ አባላት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በግምት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጥቃቱን ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን ለመፈለግ በፈንታሌ ወረዳ ጡጢቲ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ዴዲቲ ካራ ከሚባል የከረዩ ሚችሌ አባገዳዎችና የጅላ አባላት የመኖሪያ ሰፈር የደረሱ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች 39 የጅላ አባላትን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ ኢሰመኮ ከአይን እማኞች መስማቱን በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

በፀጥታ አባላት ቁጥጥር ስር ከዋሉ  የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት መካከል 16  ሰዎች  ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ተወስደው፣ 14ቱ ሰዎች በጥይት ተመተው መገደላቸውን ሪፖርቱ ገልጿል፡፡


የከረዩ አባገዳ ከዲር ሀዋስን ጨምሮ ኦዳ ጫርጨር፣ ቦሩ ፈንታሌ፣ ፈንታሌ ቦሩ፣ ቁምቢ ጉራቻ፣ ቦሩ ፈንታሌ፣ ቡላ ፈንታሌ፣ ሮባ ሀዋስ፣ ቦሩ ጎዳና፣ ጂሎ ደዲኦ፣ ቡላ ፈንታሌ፣ ቡልጋ ቦረኡ፣ ጂሎ ዲዶ እና ቦሩ ጂሎ እና ሌሎችንም ጨምሮ 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት መሬት ላይ እንዲተኙ ተደርገው በጥይት እንደተገደሉና ሁለት ሰዎች ወደ ጫካ ሮጠው እንዳመለጡ የኮሚሽኑ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

የአይን እማኞችን ዋቢ ያደረገው ሪፖርቱ የጸጥታ ሃይሎች 14ቱን ሰዎች ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ከተወሰዱ በኋላ በረድፍ እንዲተኙ ተደርጎ የሚገደሉበት ሰዓት እየደረሰ እንደሆነ እንደተነገራቸውና ከመሞታቸው በፊት ግን ከመካከላቸው ገንዘብ የያዘ ሰው ካለ እንዲሰጧቸው እንደተጠየቁ በመጨረሻም ለእያንዳንዳቸው ገዳይ ተመድቦላቸው ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ የፀጥታና የአካባቢ አስተዳደር ሰዎች ባሉበት፣ ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ በጥይት ተመተው እንደተገደሉ ተገልጿል፡፡

የሟቾችን አስከሬን ለማንሳት ግድያው ወደ ተፈጸመበት ቦታ የሄዱ ሰዎች በቦታው በነበሩ ፖሊሶች እንዳያነሱ በመከልከላቸው፣ አስከሬኖቹ ለበርካታ ሰዓታት ሳይነሱ መቆየታቸውንና በከፊል በዱር እንስሳ የተበሉ ጭምር እንደነበሩ አስከሬኖቹን ያነሱና የቀበሩ ሰዎች መግለጻቸውን የምርመራ ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

በእለቱ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ከተወሰዱት 39 የጅላ አባላት መካከል 23ቱ ወዴት እንደተወሰዱ አለመታወቁንና ከሁለት ሳምንታት በኋላ ጅሎ ቦረዩ የተባለ የጅላ አባል ሕይወቱ አልፎ አስክሬኑ በሞጆ ከተማ ከሚገኝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ለቤተሰብ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ታኅሣሥ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና ለኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በጻፈው ደብዳቤ በምርመራው ግኝቶች ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠይቅም ሁለቱም መስሪያ ቤቶች ሪፖርቱ ይፋ እስከተደረገበት እለት ድረስ ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን አስታውቋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ ይህን የግድያ ወንጀል የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሰዎችን እንዲሁም በፖሊስ አባላት ላይ የግድያና የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል የፈጸሙትን ሰዎች በሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢው የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም “ስለ ጠቅላላ የነገሩ ሁኔታ እውነቱን በመግለጽ፣ ፍትሕ በማረጋገጥና የተጎዱ ሰዎችን በመካስ ላይ የተመሰረተ አስፈላጊ ተግባራትን በማከናወን የማኅበረሰቡን ሰላም እና ደኅንነት እንዲመለስ ማድረግ ይጠበቃል” ብለዋል ። [ዋዜማ ራዲዮ]