ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባና አንዳንድ የክልል ከተሞች በነዳጅ ማደያዎች የሚታየው የተሽከርካሪዎች ሰልፍ ከነዳጅ አቅርቦት ዕጥረት ጋር የተያያዘ አለመሆኑንና ይልቁንም መንግስት ከሌላው ጊዜ መጠኑ ከፍ ያለ ነዳጅ ወደ ሀገር ማስገባቱን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አስታወቀ።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ  አቶ ታደሰ ሀይለማሪያም ለዋዜማ በሰጡት መረጃ በጥር 2014 ዓ.ም ብቻ ድሮ ሲመጣ ከነበረው 76 ሚሊዮን ሊትር ከፍ ብሎ ወደ 80 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚል  ወደ አገር ቤት  ገብቷል።

ካላፉት ሁለት ቀናት ጀምሮ በበርካታ ነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ ለመቅዳት የተሰለፉ ረጃጅም የተሸከርካሪ ሰልፎች የታዩ ሲሆን ይህ ሊሆን የቻለው አሽከርካሪዎች ባልተረጋገጠ መረጃ፣ ዕጥረት ሊኖር እንደሚችል በመገመትና የዋጋ ጭማሪ ሊከሰት ይችላል በማሰብ እንደሆነ ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለው ተናግረዋል፡፡ 

መንግስት በየካቲት ወር የሚያደርገው የዋጋ ጭማሪ ባይኖርም ጭማሪ ይደረጋል  በሚል ስጋት የሚታዩት ሰልፎች ከደንበኞች ፍራቻ የመጣ እንጅ በአቅርቦት ረገድ ከዚህ ቀደም ይታይ እንደነበረው በነጋዴዎች ምርት ደብቆ የመያዝና ማደያዎች ተዘግተው አገልግሎት አቁመው አልታዩም ብለዋል፡፡ 

በተወሰኑ ማደያዎች የተለያዩ ሰበቦቸን በማቅረብ የነዳጅ መቅጃዎች እንደተበላሹ በማስመሰል ሰልፍ እንዲፈጠር የሚያደርጉም መኖራቸውን አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ለነዳጅ ኮንትሮባንድ ምንጭ እየሆኑ ያሉት በርካታ የነዳጅ ማዳያዎች  በምስራቅና ደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ በመሆናቸው ከወደብ የመጣው ነዳጅ ወደ እነዚህ አካባቢዎች ተጓጉዞ ወደ ጎረቤት አገራት በህገወጥ መንገድ በውድ ዋጋ እየተሸጠ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከሶማሌ፣ጅቡቲና ኬንያጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ በደቡብና ምስራቅ የአገሪቱ ክፍል በኩል ወጥቶ ወደ ጎረቤት አገራት በውድ ዋጋ መሸጡ በአማራ ክልል ያለውን የነዳጅ ማደያ ቁጥር ውስን እንዲሆን ከማድረጉም በላይ  ወደዚህ አካባቢ የሚላከው የነዳጅ አቅርቦትም ዝቅተኛ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡  

ምንም እንኳ በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው የነዳጅ ማደያ ቁጥር ውስን ቢሆንም ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉትም እንኳ ቢሆን ወደ ደቡብና ምስራቅ አካባቢዎች ያለው እንደሚበዛ አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ 

ከታህሳስ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በቤንዚን ላይ በተደረገ የዋጋ ማስተካከያ በህዳር ወር ሲሸጥበት ከነበረው  25 ብር ከ85 ሳንቲም ዋጋ ጭማሪ በማድረግ በሊትር 31 ብር ከ74 ሳንቲም እንዲሸጥ መወሰኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ 

እንዲሁም ነጭ ናፍጣ 28 ብር ከ94 ሳንቲም፣ ነጭ ጋዝ 28 ብር ከ94 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 23 ብር ከ73 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ 23 ብር ከ29 ሳንቲም እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ 58 ብር ከ77 ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡ 

መንግስት ለዘመናት በነዳጅ ምርቶች ላይ ሲያደርገው የነበረውን ድጎማ ለግል ተሸከርካሪዎች ሊያቆም መሆኑን በቅርቡ በሚንስሮች ምክርቤት በኩል በቀረበ ረቂቅ ህግ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]