ዋዜማ ሬዲዮ- የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል እና ለቆጣጠር የወጣው መመርያ ቁጥር 30/2013 ከመስከረም 25 2013 ዓም ጀምሮ እየተተገበረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡


በርካታ አንቀፆችን በያዘው በዚህ መመርያ የኮቪድ 19 ቫይረስ ስርጭት መከላከያ የሆኑትን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጨንብል (ማስክ) ሳያደርጉ መቀንሳቀስ እና አካላዊ ርቀትን አለመጠበቅ አግባብ ባለው የወንጀል ህግ እንደሚያስቀጡ ተደንግገዋል፡፡


ይህን ተከትሎም በአዲስ አበባ ከተማ ከመጋቢት 17 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓም ባለው ጊዜ ብቻ 167 ሺህ 396 ግለሰቦች መመርያውን ጥሰው መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለዋዜማ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡


ነገር ግን የተወሰደው እርምጃ የማስተማሪያ እና የማስጠንቀቂያ ብቻ ነው ፡፡


“ይሄን ሁሉ ሰው በየጊዜው እንሰር ብንል በቂ የማሰሪያ ስፍራ ካለመኖሩ በተጨማሪ ያን ሁሉ ሰው በአንድ ቦታ ማድረግ ጭራሽ ለበሽታው መስፋፋት ምክኒያት መሆን ነው፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ ማስተማሪያ የሆኑ ቅጣቶችን መቅጣት ነው፡፡፡” ብለዋል ኮማንደር ፋሲካ፡፡


እንዲህ ያለው ማስተማሪያ ቅጣት ሲተገበር ለምን ብለው ውዝግብ በፈጠሩ 68 ግለሰቦች እና የቫይረሱን መከላከያ መንገዶች ፍፁም ችላ ባሉ 26 ተቋማት ላይ ምርመራ ተደርጎባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡


የጤና ሚኒስቴር ትናንት ግንቦት 19 ቀን 2013 ዓም ባወጣው መረጃ መሰረት አሁን ላይ በመላ ሀገሪቱ 270,527 ግለሰቦች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 4,127 ግለሰቦች ህይወታቸው አልፏል፡፡ [ዋዜማ ሬዲዮ]