ዋዜማ ራዲዮ- በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች እየተካሄደ በነበረ በአንዱ ተቃውሞ ሰልፍ ተሳትፎ ያልነበራቸው መንገደኞች በሰልፈኞች ተማርከው በግዳጅ አመጹን እንዲቀላቀሉ መደረጋቸውን ሰምተናል፡፡ በግዳጅ ብንገባም ለመቃወም እድል ስላገኘን አልተከፋንም ይላሉ።
ከአዲስ አበባ ወደ ሐዋሳ በጉዞ ላይ የነበሩ ተሳፋሪዎች በተቃውሞ ስትናጥ በነበረችው ሻሸመኔ ሲደርሱ በወጣት ሰልፈኞች እንዲቆሙ ከተደረጉ በኋላ ለጥቂት ደቂቃዎች ታግተው መቆየታቸው ተነግሯል፡፡ በኋላም እጃቸውን በተቃውሞ ምልክት አጠላልፈው በሰልፍ ከየአውቶቡሶቻቸው እንዲወርዱ ተደርገዋል፡፡
ተሳፋሪዎቹ ከየአውቶቡሶቻቸው ከወረዱ በኋላም ሁለት እጃቸውን ከጭንቅላታቸው በላይ አስተሳስረው እንዲቆዩ በነዚህ ወጣት ተቃዋሚዎች መታዘዛቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹በዚሁ ሁኔታ ታግተን ከተማውን ሁለት ሦስት ጊዜ እንድንዞር ተደርገናል፡፡ ‹‹ዳውን ዳውን ወያኔ›› የሚለውን የተቃውሞ ዝማሬ እንድንዘምር ተገደናል›› ሲል ከታጋቾቹ መካከል አንዱ የነበረው ወጣት ለዋዜማ ዘጋቢ በስልክ ነግሮታል፡፡
‹‹እኔ ለነገሩ አጋጣሚው በመጠቀም በሥርዓቱ ላይ የነበረኝን ቅሬታ ለመተንፈስ ችያለሁ›› ያለው ይህ የአዲስ አበባ ነዋሪና ተሳፋሪ በአጋጣሚው እምብዛምም ቅር አለመሰኘቱን ይናገራል፡፡ ‹‹ተሳፋሪዎች ሁላችንም ላይ መጠነኛ ፍርሃት የተሰማን ቢሆንም ተቃውሞ አሰምተን በሰላም ወደ አውቶቡሶቻችን እንድንገባ መደረጋችን እፎይታ ተሰምቶናል፡፡›› ይላል፡፡
ከቃሊቲ መናኸሪያ በየዕለቱ በርካታ አውቶቡሶች ወደ አጎራባች ኦሮሚያ ክልሎች የሚተሙ ሲሆን ከሰሞኑ እየተቀጣጠለ የሚገኘውን አመጽ በመስጋት የሕዝብ ማመላለሻ ማኅበራትና የትራንስፖርት አክሲዮኖች ሥራ መስተጓጎሉ ተነግሯል፡፡ እለታዊ ስምሪታቸውን ካቋረጡ አውቶቡሶች መሐል ሰላም ባስ ዋንኛው ነው፡፡