FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ምንጩ ያልታወቀ ሀብት በደበቁ 23 የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ በፍትሕ ሚንስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ የወንጀል መርመራ መጀመሩን ዋዜማ ከሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ምንጮቿ ሰምታለች፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በባለሥልጣናቱ ላይ የወንጀል ምርመራ የጀመረው፣ የፌዴራል ስነ ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ያስመዘገቡ የመንግሥት ባለስልጣናትን ሰነድ ሲመረምር ሳይመዘገብ የቀረ ከፍተኛ ሀብት በማግኘቱ ሲሆን፣ ከሀብት ምዝገባ የተደበቀው ሀብት፣ ቤት፣ መኪና እና መሬት (ቦታ) እና የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚገኝበት ዋዜማ ከኮሚሽኑ ሰምታለች፡፡

ኮሚሽኑ ባደረገው የሀብት ምዝገባ ትክክለኛነት ማረጋጋጫ ለሙስና ተጋላጭ ናቸው ባላቸው የመንግሥት ተቋማት ላይ ባካሄደው የማረጋገጥ ሥራ፣ ከፍተኛ ሀብት የደበቁ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲደረግባቸው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስተላልፏል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፣ ለወንጀል መርምራ የተላኩለትን አካላት ዝርዝር ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዳስረከበ መረዳት ችለናል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መዝገቡን ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማስተላለፉን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወደ ምርመራ መግባቱን ዋዜማ ከፍትሕ ሚኒስቴር ምንጮቿ አረጋግጣለች፡፡ የወንጀል ምርመራው የሚካሄደው በፍትሕ ሚንስቴር በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ ውስጥ በሚገኘው የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክተር ጀኔራል ቢሮ ሲሆን፣ የወንጀል ምርመራ ሥራው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ መጀመሩን የዋዜማ ምንጮች ነግረውናል፡፡

የተገኘው ማስረጃ ተራ ሪፖርት ወይም ተራ ጥቆማ ሳይሆን፣ የወንጀል ምርመራ ለመጀመር የሚያስችል በቂ ፍንጭ መሆኑን የገለጹት የፍትህ ሚንስቴር የዋዜማ ምንጮች፣ ጥቆማውን ተከትሎ የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክተር ጀኔራሉ የወንጀል ምርመራውን በጥልቀት እያካሄደ መሆኑን  ጠቁመዋል፡፡

ዋዜማ ከስነ ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ እርከን ላይ የሚገኙ ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ 

ኮሚሽኑ የተደበቁ ሀብቶችን ለመለየት የገቢ ምንጭና ተቀማጭ ገንዘብ ለማረጋገጥ የመንግሥት እና የግል ባንኮችን መረጃዎች የተጠቀመ ሲሆን፣ የተደበቁ የመኪና፣ የቤትና የመሬት መረጃዎችን ደሞ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት እንዳረጋገጠ ታውቋል፡፡ 

ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ምንጩ ያልታወቀ ከፍተኛ ሀብት የደበቁ አካላት ላይ ምርመራ እንዲደረግ እና በተገኘው የምርመራ ውጤት ክስ ተመስርቶባቸው በሕግ እንዲጠየቁ ያደረገው ጥረት፣ በመንግሥት ውሳኔ እንዲቋረጥ በመደረጉ እና የመመርመርና ክስ የመመስረት ሥልጣን ያላቸው ተቋማት ኃላፊነታቸውን ባግባቡ ባለመወጣታቸው በኮሚሽኑ ሥራ ላይ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን የኮሚሽኑ ምንጮች ለዋዜማ አስረድተዋል።

የወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙ ባለሥልጣናትን ስም ዝርዝር ዋዜማ ከምንጮቿ ጠይቃ ነበር። ምንጮቹ ግን የስም ዝርዝሩን መግለጽ በሂደት ላይ በሚገኘው ምርመራ ላይ መስተጓጎል ይፈጥራል በሚል ምክንያት ስም ዝርዝሩን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]